በአንድ ወገን ተከራካሪ ጥቅም ላይ ክህደትን ስለመፈጸም (አንቀጽ ፬፻፶፰ ንዑስ አንቀጽ ፩) የኢፌዴሪ የወንጀለኛ መቅጫ ህግ እንዲህ የሚል ፍርድን አስቀምጧል:- "ማንኛውም ጠበቃ፣ ነገረ ፈጅ፣ ወይም የሕግ አማካሪ በፍርድ ቤት ወይም የዳኝነት ስልጣን ባለው አካል ፊት ቀርቦ … የወካዩን ወገን ጥቅም በመሰዋት … ጉዳዩን ያበላሸበት እንደሆነ በቀላል እስራትና በመቀጮ ይቀጣል።"
ከዚህ ህግ መነሻነት እንኳን ጴጥሮስ በክርስቶስ ላይ ክህደትን በመፈጸሙ ቀለል ያለ እስራት እና መቀጮ ይገባው ነበር። ግን ደግሞ የኢፌዴሪ ሕግ እንደሚጠይቀው ስምዖን ጴጥሮስ በፍርድ ቤት ወይም የዳኝነት ስልጣን ባለው አካል ፊት ሳይሆን በገረድ ፊት ነው ኢየሱስን የካደው። ይህ ኢየሱስን ምን ያህል ያሳዝነው ይሆን? ለሶስት አመት ተኩል ሁሉን ትቶ የተከተለውን መምህሩን ደግሞም ጌታውን በገረድ ፊት መካዱ ጌታውን ምን ያህል ያሳዝነው ይሆን!
ከዚህም መነሻነት ይመስላል ከትንሳኤው በኋላም ጴጥሮስ ወደ ቀድሞ አሳ ወደ ማጥመድ ስራው ነው የተመለሰው (ዮሐንስ 21)። ጴጥሮስ በራሱ ላይ የእስር ፍርድ ፈርዶ ነበር ማለት ነው። ጌታው እንደቀድሞ ይቀበለው እንደሆነ አላወቀም ነበር። በተቃራኒው ጌታ ኢየሱስ ለስምዖን ጰየጥሮስ ያልጠበቀውን ነገር ጠየቀው። "የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ ከእነዚህ ሁሉ አብልጠህ ትወደኛለህን?"
ሌላ ዕድል! ሌላ የፍቅር ጥሪ! አንዳንድ ጊዜ ከስህተቶቻችን ብዛት የተነሳ በራሳችን ላይ ፍርድ ፈርደን ከጌታ ለመለየት ደግሞም ዳግም ላለመመለስ ወስነን ሊሆን ይችላል። ጌታ ግን ዛሬም የእንደገና የፍቅር ጥሪ እንዳለው ላስታውሳችሁ እወዳለሁ። ምናልባት በዚህ ጽሁፍ ለስምዖን የጠየቀውን ጥያቄ ለልባችን እየጠየቀ ቢሆንስ "… ከእነዚህ ሁሉ አብልጠህ/ሽ ትወደኛለህ/ኛለሽ?" ይህ የእንደገና የፍቅር ጥሪ ነው!
ስምዖን ጴጥሮስ ይህንን ዕድል ተጠቅሞበታል። "አዎን ጌታ ሆይ አንተ ታውቃለህ!" ብሎ መለሰ። ምናልባት ያለፈው ጊዜ ሁሉም ተሰርዞ እንደገና ለመጀመር ፈልገን ይሆን? ታሪክን መሻር አይቻልም! ከጌታ ከኢየሱስ ጋር ግን አዲስ ታሪክ ለመጻፍ ጊዜው አልረፈደም! ዛሬም በክርስቶስ ፍቅር ተሸንፈን "አዎን ጌታ ሆይ አንተ ታውቃለህ!" ብለን ለእንደገና ጅማሬ ምላሻችንን እንስጥ።
Day 1 Day 2Day 3Day 4Day 5Day 6Day 7Day 8Day 9
