Monday, 15 July 2024

የ"ዋቄፈና" እምነት ምንድን ነው? የዋቄፈና እምነት ተከታዮችን በወንጌል ለመድረስ ምን ያስፈልጋል?

Posted On %PM, %29 %870 %2018 %22:%Sep Written by
የ"ዋቄፈና" እምነት ምንድን ነው? የዋቄፈና እምነት ተከታዮችን በወንጌል ለመድረስ ምን ያስፈልጋል? Philipp Schütz

"ይሄ ደሞ ምንድን ነው?" አልኩት በእጄ የሆራ አርሰዲ ዙሪያ ረግረጉን ይዞ የበቀለውን ሳር ቀንጥሼ ውሃው ውስጥ እየነከርኩ። ስለማደርገው ነገር ምንም አልገባኝም። ነገር ግን ይህንን ስርዓት በመፈጸም ከብዙ ሺህ ሰዎች ጋር ተቀላቅያለሁ። ከብዙ ሺህ ሰዎች መካከል ደግሞ ይህንን ስርዓት ከልቡ የሚያከብር ወላጅ አባቴ አለ። አይን አይኔን እያየ ጥያቄዬን ካደመጠ በኋላ "ይህ በኦሮሞ ባህል መሰረት ለምድራችን ለምነት ፈጣሪን የምንማጸንበት ስርአት ነው። ውሃውና ሳሩ የሚወክሉትም ይህንን ነው። ከዚህም በላይ በአባቶች ጸሎት የተመረቀ ውሃ ነው። ለእኛ እንደጸበል ነው" አለኝ።

ወላጅ አባቴ የእድሜውን አብዛኛውን ያሳለፈው በዋቄፈና እምነት ውስጥ ነበር። ስለዋቄፈና እምነት በቤተሰብ ውስጥ ብዙ እየተነገረኝ አድጊያለሁ። አድጌም እኔም በጥቂቱ የእምነቱን ስርአት እና ምንነት ማስተዋል ችያለሁ። በክርስትና ሕይወት ዳግም እስከተወለድሁበት ጊዜ ድረስ በእናቴ በኩል የኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት እንዲሁም በአባቴ በኩል ደግሞ የዋቄፈና እምነት በሕይወቴ ላይ ተፅዕኖ አድርገዋል።

የዋቄፈና ተጽዕኖ በእኔ ላይ ብቻ ሳይሆን በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ጭምር ነው። የፊታችን እሁድ መስከረም 20 እጅግ በጣም ብዙ ህዝብ የሚሳተፍበት አመታዊው የኢሬቻ በአል ቀን ነው። ይህ ኢሬቻ በአል ቀን ታዲያ የዋቄፈና እምነት አንዱ እና ዋነኛው መገለጫው ነው። በዚህም ምክንያት የዋቄፈና ተጽዕኖ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊም ጭምር ነው ቢባል ማጋነን አይደለም።

"ዋቄፈና" ምንድነው?

የዋቄፈና እምነት በኢትዮጵያ እንዲሁም አንዳንድ መረጃዎች እንደሚያሳዩት በአፍሪካ ዋና ዋና ሃገር በቀል ኃይማኖቶች ከሚባሉት መካከል አንዱ ነው1። ይህ እምነት ከኦሮሞ ህዝብ ባህል እና ታሪክ ጋር ለረጅም ዘመናት የተቆራኘ እምነት ነው። እንደ ፈረንጆቹ አቆጣጠር በ2007 በተደረገው የሕዝብ እና ቤቶች ቆጠራ ከኦሮሞ ሕዝብ ወደ 3.3 በመቶ የሚደርሰው ህዝብ የዚህ እምነት ተከታይ ነበር 2። በአሁኑ ጊዜ ይሄ ቁጥር ወደ 3 በመቶ ዝቅ እንዳለ ይነገራል። አንዳንዶች ደግሞ አብዛኛው ህዝብ ባህላዊውን ሃይማኖት (ዋቄፈናን) ከእስልምና ጋር ወይንም ከክርስትና ጋር ቀይጦ ነው የሚያመልከው ይላሉ። ሁለቱም መረጃዎች የሚያስኬዱ ይመስላሉ።

ወደ እምነቱ ምንነት ስንመጣ "ዋቄፈና" የሚለው ቃል "ፈጣሪን ማምለክ" የሚል ትርጓሜ አለው። "ዋቃ" ማለት አምላክ ማለት ነው። 

የ "ዋቄፈና" አምላክ / "ዋቃ"

ቀደም ብለን እንደየነው "ዋቃ" ማለት አምላክ ማለት ነው። ልዩ ስም አይደለም የወል ስም ነው። ኦሮሞ ክርስትያኖችም ቢሆኑ ይህንኑ ቃል ተወሰው አምላካቸውን ለመጥራት ይጠቀሙበታል። በዋቄፈና እምነት መሰረት "ዋቃ" የሚከተሉት ባህሪያት እንዳሉት ይነገራል-

• በቁጥር አንድ ነው! (የዋቄፈና እምነት በአንድ አምላክ ነው የሚያምነው)

• ያልተፈጠረ ነገር ግን የሁሉ ፈጣሪ የሆነ ነው

 ከሁሉ በፊት እርሱ ነው፤

 ዋቃ ሁሉን ይይወዳል

 ሁሉን ይችላል

 ሁሉን ያውቃል

 በሁሉ ቦታ ይገኛል

 ንጹህ/ቅዱስ ነው

 የእውነት ምንጭ እና ወዳጅ ነው

 ክፋትን ፣ ወንጀልን ፣ ሐጢአትንና ሃሰትን አይታገስም

 በማንም አይመሰልም! ስለዚህም በዋቄፈና እምነት ፍጡርን (ምስልን ፣ ዛፍን ፣ ወንዝን፣ ተራራን ) መመሰል የተከለከለ ነው3

የዋቄፈና እምነት የራሱ የሆነ የእምነት መጸሐፍ ባይኖረውም እንኳ በተከታዮቹ ዘንድ ከላይ የተዘረዘሩት የዋቃ ባህርያት በሙሉ ይታወቃሉ። ከዚህ በተረፈ የዋቄፈና እምነት በጸሎት የሚያምን ሲሆን ዋቃ በየትኛውም ቦታ ተከታዮቹን ጸሎት እንደሚሰማም እምነቱ ያስተምራል። ይህ ብቻም አይደለም በአንዳንድ የዋቄፈና አማኞች ማሕበረሰብ ዘንድ ደግሞ ዋቃ ጸሎትን መስማት ብቻ ሳይሆን ከዚም አልፎ በ"ቃሉ" (ሲነበብ "ሉ" ይጠብቃል) አልፎ ይናገራል የሚል እምነት አለ። "ቃሉ" የሚባሉት ሰዎች እንደ ካህን ወይም ቄስ ሆነው ያገለግላሉ። ጸሎትን ወደ ፈጣሪ ሲያደርሱ የፈጣሪን መልእክት ደግሞ ለእምነቱ ሰዎች ያደርሳሉ ተብሎ ይታመንባቸዋል4። ከዚህም በላይ እንደ ኃይማኖት መሪ ተደርገውም ይቆጠራሉ። ይህም ማለት በክርስትና ቄስ እንደምንለው በዋቄፈና ደግሞ "ቃሉ" እንላለን ማለት ነው።

የዋቄፈና እምነት አመታዊ የምስጋና እና ቡራኬ ቀን (ኢሬቻ) አለው። ኢሬቻ ማለት "ምስጋና" ማለት ነው። አብዛኛውን ጊዜ የመስቀል በዓል በዋለ በቀጣዩ እሁድ የሚደረገው የኢሬቻ በአል በተለያዩ ቦታዎች የሚደረግ ሲሆን አባገዳው እና ሌሎች የእምነቱ አባቶች በተገኙበት ሕዝቡ በጨለማ የሚመሰለውን ክረምቱን ላሳለፈውን ለአምላኩ በአንድነት ምስጋናውን ያቀርባል ፣ ስለመጪውም ዘመን ልምላሜ እና ሰላም አምላኩን ይለምናል እንዲሁም በአባቶች መሪነት ለሕዝቡ ቡራኬ ይደረጋል።

ታዲያ ይህ ኢሬቻ ቀን ሃይማኖታዊ ብቻ ሳይሆን ባህላዊም ይዘት ስላለው ክርስትያኑም ሙስሊሙም ኦሮሞ በአንድነት ከዋቄፈታው ጋር አብሮ የሚያከብረው ቀን ነው። ይህ ታዲያ በክርስትያኖች ዘንድ አንዳንድ ጥያቄን ከዚህ በፊት ሲያስነሳ የነበረ አሁንም ድረስ ሃሳብ ለመስጠት ጥንቃቄን የሚሻ እንደሆነ የሚነገርበት ጉዳይ ነው።

የዋቄፈና እምነት በእግዚአብሔር ቃል ሲመዘን

የዋቄፈና እምነት ምንም እንኳ "ባህላዊ እምነቶች" ከሚባሉት ተርታ የሚሰለፍና የራሱ የእምነት መፀሐፍ የሌለው ቢሆንም ዋና ዋና የሚባሉት የእምነቱ መሰረቶች ከክርስትና አስተምህሮ ጋር እጅግ ይቀራረባሉ። በክርስትና እና በዋቄፈና መካከል ባለው መመሳሰል እጅግ ከሚገረሙ መካከል አንዱ እኔ ነኝ። ይህንን መመሳሰል በሚቀጥለው ሰንጠረዥ መመልከት እንችላለን።

Waaqeffannaa Vs Christianity 

በክርስትና እና በዋቄፈና መካከል ያለው መመሳሰል እንዲህ እያለ ይቀጥላል። ይህም "… ስለእግዚአብሔር ሊታወቅ የሚችለው ግልጽ ነው። ምክንያቱም እግዚአብሔር ለእነርሱ ግልጽ አድርጎታል። ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ የማይታየው የእግዚአብሔር ባሕርይ ይኸውም ዘላለማዊ ኀይሉና መለኮትነቱ፣ ከፍጥረቱም በግልጽ ይታያል" (ሮሜ 1:19-20) የሚለው የመጸሐፍ ቅዱስ ሃሳብ እውነት እንደሆነ ያረጋግጥልናል። ምክንያቱም ዋቄፈና ፍጥረትን በመመልከት ብቻ የፈጣሪን ባህሪይ ማወቅ ችሏልና። የእግዚአብሔር ባህሪያት በዋቄፈና እምነት ውስጥ በትክክል መገለጣቸውን መካድ አይቻልም።

ሆኖም ግን ዋቄፈና ሙሉ የሆነውን የእግዚአብሔርን ለሰው ልጆች ያለውን እቅድ እና የማዳን ሃሳብ የያዘውን መገለጥ አላሟላም። በዋቄፈና ለኃጢአት ስርየት ልመና፣ ለክፉ ስራ ማካካሻ ደግሞ መልካም ስራ ነው። ነገር ግን የኃጢአት ስርየት እንደተደረገ የሚያስረዳ ምንም ማረጋገጫ የለም። ምክንያቱም ሰዎች እንጂ ወደ አምላክ የሚለምኑት አምላክ ምንም ስለማይናገር።

ስለዚህም ምንም እንኳ አንድ የዋቄፈና እምነት ተከታይ እጅግ በጣም እግዚአብሔርን ለማወቅ የቀረበ መገለጥ አለው ብለን ብናምንም የመዳንን እውነት ጨብጧል ብለን ግን አናምንም። መጽሐፍ "የጌታን ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናል" (ሮሜ 10:13) ደግሞም "ኢየሱስ ጌታ እንደሆነ በአፍህ ብትመሰክር እግዚአብሔር ከሙታን እንደስነሳውም በልብህ ብታምን ትድናለህ" (ሮሜ 10:10) ነው የሚለው። ሰው ለመዳን የማካካሻ ስራ ወይንም ልመና ማቅረብ ሳይሆን በቀራኒዮ መስቀል ላይ የተሰራውን የጌታ የኢየሱስን ሞት ለሰው ልጆች እንደሆነ ማመን አለበት። ዋቄፈና ይህ መገለጥ ይጎድለዋል። 

ስለዚህ በዋቄፈና በዋናነት የመገለጥ ጉድለት እንጂ ልክ እንደ እስልምና ወይንም ሌሎች ኃይማኖቶች የስህተት አስተምህሮን አናገኝም። ሆኖም ምንም እንኳ ጥሩ የሚባል ትምህርት እግዚአብሔር ቢኖረውም ለመዳን የሚያበቃ ግን አይደለም።

የ"ቃሉ" ማንነት

የዋቄፈና እምነት ካህናት ተብለው የሚታመኑት "ቃሉ" (ሲነበብ "ሉ" ይጠብቃል) የተባሉት ሰዎች ማንነት ሌላ ጥያቄ እንድናነሳ ያስገድደናል። "ቃሉ" በእምነቱ ሰዎች ዘንድ እጅግ በጣም የሚፈሩ እና የሚከበሩ ሲሆኑ በአምላክ እና በሰው መሐልም መካከለኞች ናቸው ተብሎ ታመንባቸዋል። ቀድሞ የዋቄፈና እምነት ተከታዮች የነበሩ ኋላ ወደ ክርሰትና የተቀየሩ ሰዎች እንደሚመሰክሩት ከሆነ እነዚህ ሰዎች ("ቃሉ") ግንኙነታቸው ከእግዚአብሔር ጋር ሳይሆን ከሌሎች መናፍስት ጋር ሊሆን እንደሚችል የተለያዩ ፍንጮች አሉ።

መቼም የባህላዊ እምነት ነገር ሆነና ነገሩ በዋቄፈናም በተለያዩ የአፍሪካ ባህል እምነቶች ዘንድ የሚስተዋለው ችግር አለ። እነዚህ "ቃሉ" የተባሉት ሰዎች ምንም እንኳ በከተሜው ተከታዮች ዘንድ አሁን እየተረሱ ቢሆንም አሁንም ድረስ በገጠር አከባቢ ባሉ የእምነቱ ተከታዮች ዘንድ እንደ አዋቂ ተቆጥረውና ተከብረው እንዳሉ መረጃዎች አሉኝ። ይህም ለዋቄፈና አማኞች እንድናዝን ያስገድደናል። "ቃሊቻ" የሚለው ቃል የተገኘው "ቃሉ" ከሚለው እንደሆነም ይነገራል። ታዲያ የ"ቃሉ"ን አገልግሎት የሚጠቀሙ የዋቄፈና እምነት ተከታዮች ባለማወቅ ከክፉ/አጋንንት/ መንፈስ አሰራር ጋር በ"ቃሉ" አማካይነት ግንኙነት እያደረጉ እንደሆነ ማወቁ ደግሞ እጅግ ያሳዝናል።

ዋቄፈና አና ሆራ አርሰዲ

የዋቄፈና እምነት ተከታዮች ዋቃን ለማመስገን በአመት አንድ ጊዜ በሕብረት በመሰብሰብ የምስጋና እና የቡራኬ ቀን ያሳልፋሉ። ይህ በአል ኢሬቻ ሲባል በደመቀ ሁኔታ በየአመቱ በቢሾፍቱ ከተማ በሆራ ሃይቅ (ሆራ አርሰዲ) ዙርያ ይደረጋል። ኢሬቻ በሌሎች ቦታዎችም ይደረጋል ነገር ግን ደማቁ እና አሁን አሁን እንደውም በሚልዮን የሚቆጠር ሕዝብ እንደሚካፈልበት የሚነገርለት የቢሾፍቱ ሆራ አርሰዲ ኢሬቻ በአል ነው።

አስቀድሜ እንደገለጽሁት የኢሬቻ በአል ላይ ብዙ ጊዜ ተገኝቼ አውቃለሁ። በዓሉ የሁሉ ፈጣሪ የሆነ አምላክ የሚመሰገንበት እንደሆነም አውቃለሁ። በተለይ ካደግሁ በኋላ ግን አንዳንድ በኢሬቻ ላይ አያቸው የነበሩ ነገሮች ስለ ኢሬቻ ጥያቄ እንዳስነሳ አስገድደውኛል።

ክርስቲያን ኦሮሞ እና ኢሬቻ

ዋቄፈና እምነት አስቀድመን እንዳየነው አምላክን በምንም ነገር አይመስልም። አምላክ የማይታይ ነገር ግን በሁሉ ስፍራ የሚገኝ እንደሆነ ይታመንበታል። ሆኖም ግን በኢሬቻ በአል ላይ አንዳንድ በሌሎች ባህላዊ ሃይሞኖቶች እንደምንመለከተው ከጥንቆላ ጋር የሚያያዙ/የሚመስሉ/ ነገሮችን አይቻለሁ። "ኦዳ" የተሰኘውንና የኦሮሞ ሕዝብ ምልክት ተደርጎ የሚቆጠረውን ዛፍ ግንድ በቅቤ የመቀባት እና መሰል ወጣ ያሉ ልምምዶችን አስተውያለሁ። የዋቄፈና አምነት በአንድ በኩል ፈጣሪ በምንም እንደማይመሰል ሲገልጽ በሌላ በኩል ደግሞ እንዲህ አይነቱ ከጥንቆላ አሰራር ጋር የተቀራረበ ልምምዶችን መያዙ ጠንቀቅ ብለን እንድንመለከተው ያስገድደናል። እነዚህ ልምምዶች ስለኢሬቻ ያለኝን አመለካከት ዝቅ እንዲል ያስገድዱኛል። ይህንን አይነቱን ነገር በተረዱ ጊዜ ኢሬቻ በአል ላይ መሳተፍ ያቆሙ የኦርቶዶክስና የፕሮቴስታንት ተከታዮችን አውቃለሁ።

የኢሬቻን በአል መካፈል የሚሹ ክርስትያኖችም በአሉ የኦሮሞን ባህል ስለሚያንጸባርቅ እንደሚካፈሉ ይገልጻሉ። ይህ መልካም ሆኖ ሳለ የበዓሉ አላማ ግን በዋናነት ፈጣሪን ማመስገን ነው፤ ወይንም መንፈሳዊ ትርጉም ነው ያለው። ስለዚህ ይህንን መንፈሳዊ ትርጉም ክርስትያኖች መጋፈጥ ይችላሉ? ምክንያቱም የኦሮሞን ባህል እንደኦሮሞነት ማክብር እና መካፈል መልካም ቢሆንም እንደ ክርሰቲያን ደግሞ ነገሮችን መመርመር እና መፈተን ይበልጥ አስፈላጊ ነው። ስለዚህም ክርስቲያን ኦሮሞ ኢሬቻን በአል ከመካፈሉ በፊት አስቀድሞ የመንፈሳዊ ሕይወቱን መመርመር አለበት ባይ ነኝ። በአከባቢው በአል ብቻ ሳይሆን ተጓዳኝ የክፉ መናፍስት አሰራር እንዳለ ተረድቶ እርሱን ሁሉ ተቋቁሞ ቀኑን ማሳለፍ እንዳለበት አስቀድሞ ማወቅ አለበት። ባህላዊን ብቻ ሳይሆን መንፈሳዊ ዝግጅትንም እየተካፈለ እንዳለ መረዳት አለበት። "መንፈስን ሁሉ አትመኑ፤ ነገር ግን መናፍስት ከእግዚአብሔር መሆናቸውን መርምሩ" (1ኛ ዩሐ 4፡1)

ይህ ብቻም አይደለም ምንም እንኳ የአባቶቹ ቡራኬ መልካም ቢሆንም የእምነቱ አባቶች ግን እንደጻድቃን መቆጠር የለባቸውም። ክርስቲያን ኦሮሞ ይህንን ጥንቃቄ ማድረግ አለበት። የእምነቱን አባቶች እንደ ልዩ ነገር በመቁጠር "ልመናቸው ካላገኘኝ ስኬት ይርቀኛል" በሚል ፍራቻ ወደ ኢሬቻ መሄድ የለበትም። ክርስቲያን የመጨረሻው ትልቅ የተባለውን ባርኮት በክርስቶስ ኢየሱስ በሰማያዊ ስፍራ አግኝቷል (ኤፌ 1፡3)። ስለዚህ እምነት አባቶቹን በእድሜ እንደገፉ አባቶች ምርቃት ብቻ ነው መውሰድ ያለበት።

በመጨረሻም የእሬቻን በዓል ለማክበር የሚሄዱ ክርስቲያን ኦሮሞዎች ጽንፍ ከወጣ ባህላዊነት ራሳቸውን መጠበቅ አለባቸው ባይነኝ። በባህል አስፈላጊነት እና ባህልን መቀበል እንዳለብን አምናለሁ። እንደውም ይህንኑ ባህል ለወንጌል መጠቀሚያ ማድረግ እንደሚቻልም እረዳለሁ። ነገር ግን ባህላዊነትን አልደግፍም። ባህላዊነት ማለት በባህል መታሰር ፣ በባህል መታወር ማለት ነው። በባህል ማታሰር ደግሞ ወደ ጠባብ አስተሳሰብ እና ዘረኝነት ሊያመራ ይችላል። ክርስቲያን ኦሮሞ ከዚህ ራሱን ጠብቆ ባህሉን በመቀበል ለእግዚአብሔር ክብር ማድረግ ይገባዋል። ኢሬቻም በዚሁ መልኩ መታየት እና መቃኘት አለበት።

ባህላዊ ሃይማኖቶች በአንድ በኩል ባህላዊነትን ሲያራምዱ በሌላ በኩል አጉል እምነትን ሊያራምዱ ይችላሉ። ዋቄፈናም ለእንደዚህ አይነት ልምምድ የተጋለጠ ነው። ስለዚህ ለክርስቲያን ኦሮሞዎች ጥንቃቄ ሲያስፈልግ ለዋቄፈና እምነት ተከታዮች ደግሞ እውነተኛውን የመዳንን መገለጥ የሚሰጠውን ወንጌል ይዘን ልንደርስላቸው ይገባል።

እናስ እንዴት እንድረሳቸው?

በመጨረሻም እንዴት እንደምንደርሳቸው እንይ። ከብዙ ዋቄፈና እምነት ሰዎች ጋር ቁጭ ብዬ የማውራቱን እድል አግኝቼ ነበር። አብዛኛውን ጊዜ በወንጌል ምስክርነት ምክንያት። ከውይይት ጊዜያቶቼ የተማርኳቸውና ለዋቄፈና እምነት ተከታዮች ወንጌልን ለማድረስ ቢደረጉ ብዬ የምመክራቸው እንዲህ ባጭሩ ላስቀምጣቸው፡-

 ቋንቋ ወሳኝ ነው! ቢቻል ወንጌልን የሚመሰክረው ሰው የኦሮሚኛን ቋንቋ መናገር የሚችል ይሁን፣

 የዋቄፈናን እምነት ከማድነቅ እና ከክርስትና ጋር ከሚያመሳስለው እውነቶች መነሳት (ከጋራ መሰረት መጀመር)፣

 የዋቄፈናን ጉድለት መረዳት። የዋቄፈና ትልቁ ጉድለት ኢየሱስ ነው። ስለዚህ ኢየሱስን "አዳኝ" በሚለው አውድ ማስተዋወቅ፣

 ዋቄፈናዎች ቀለል ያለ ኑሮን ይወዳሉ። አምላክ በሁሉ ቦታ እንዳለ ስለሚረዱ ቤተ ክርስቲያን መሄድ ፣ መጸሐፍ ቅዱስ ማንበብ ቶሎ አይረዱም ስለዚህ አለማቻኮል፣

 በተረፈ ባሉበት አካባቢ እንዲጸልዩ ማበረታታ እና ጸሎታቸው እንዳያቋርጡ መምከር ብሎም መከታተል።

እነዚህ የዋቄፈና እምነት ተከታዮችን ለመድረስ እንደሚረዱ አምናለሁ!

ማጠቃለያ

የዋቄፈና እምነት ተከታዮችን መድረስ አለብን! ለመድረስ እምነታቸውን እንወቅ ፣ የሚያስፈልገውን መስዋዕትም እንክፈል። "የጌታን ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናል" እንደተባለ የጌታን ስም በእምነት ጠርተው እንዲድኑ የተነቃቁ ቋንቋውንና ባህሉን የሚያውቁ መልዕክተኞች ይነሱ! አሜን!


ማጣቀሻ

1. Mulugeta Jaleta Gobenooromo; Indigenous Religion: Anthropological Understanding of Waaqeffanna-Nature Link, With Highlight on Livelihood in Guji Zone, Adola Redde and Girja Districts, A thesis  submitted to the department of Social Anthropology, College of Social Science Addis Ababa University, June 2017, p.4

2. Census (PDF), Ethiopia, 2007 

3. 4. Workinesh Kelbessa, Traditional Oromo Attitudes towards the Environment, Social Science Research Report Series, no. 19, page 22, 26

Last modified on %PM, %29 %912 %2018 %23:%Sep
Naol Befkadu

Naol Befkadu Kebede (BTh, student of MA in Ministry and Medical Doctorate student at AAU) is the founder and contributor of Lechristian Blog, an online ministry that aims to redeem cultures for the glory of God and to inspire and encourage believers for the completion Great Commission. Naol has authored an Amharic book titled "ተነሺ ፤ አብሪ" (2015) that motivates young believers for a meaningful and radical life. 

lechristian.blogspot.com

መጽሐፍ ቅዱስን ለማንበብ አራት ጸሎቶች

መጽሐፍ ቅዱሳችንን ልናነብብ ስንከፍት ለብቻችንን አይደለንም ። መንፈስ ቅዱስ ለክርስቶስ ክብር ሲል ልባችንን ሊያነሳሳ አዕምሮአችንን ሊያበራ ሕይወታችንን ሊቀይ...

David Mathis - avatar David Mathis

ጨርሰው ያንብቡ

ከታላቁ የወንጌል ሰባኪ ዶ/ር ቢሊ ግራሃም (1918-2018) ሕ…

ታዋቂው አሜሪካዊ የወንጌል ሰባኪ ዊልያም ፍራንክሊን ግራሃም ወይም በአጭሩ ቢሊ ግራሃም በ99 አመታቸው ዜና እረፍታቸው በትላንትናው ዕለት (የካቲት 14) ማለዳ...

Naol Befkadu - avatar Naol Befkadu

ጨርሰው ያንብቡ

 

The views and opinions expressed on Daily Injera are solely those of the original authors and our contributors. These views and opinions do not necessarily represent Daily Injera or our Staff.

Newsletter

Subscribe to our newsletter. Don’t miss any article, devotionals or wallpapers.

We do not spam!

You're automatically subscribed to bi-weekly articles and daily devotionals. You can customize your subscription settings here.