በመጀመሪያ ስለመንፈሳዊነት ስናስብ ወደ ልባችን የሚመጡ አያሌ መፍትሔያት መልካም እና ሊበረታቱ የተገቡ ቢሆኑም፤ ነገር ግን ይህ ጥያቄ ከግል አስተያየት ያለፈ ሙሉውን የቅዱሳት መጻህፍትን ምክር ያካተተ ሊሆን ይገባል። እንጂ ሽራፊ መልስ ይዞ የመሸምጠጥን ፈተና እምቢ ብለን መግታት ይኖርብናል። ለምን? ምክኒያቱም እንዲህ ዓይነቱ ችኮላ እ/ር በደሙ የዋጃትን ቤት እንደ መንፈሳዊ “ላብራቶሪ” የመጡልንን ሐሳቦች የምንሞካክርባት ሪሰርች-ማዕከል ስለሚያደርጋት ነው። ይህች ቤት የእ/ር ናት፤ ሕይወቷም የተቀየሰላት ከሰማይ ነው። ስለዚህ እንደ ክርስቶስ አንድ አካል ቅዱሱን መጽሐፍ ከፍተን በጋራ በመወያየት ወደ በሰለ መፍትሔ መድረስ አማራጭ የሌለው ነው። ልክ የመንፈሳዊነትን ጥያቄን አለመመለስ ትውልድ አጥፊ መዘዝ እንዳለው ሁሉ፤ ለጥያቄዉም ሙሉና መጽሐፍ ቅዱሳዊ እይታን ያልያዘ መልስም እንዲሁ እጅግ አስከፊ መዘዝ አለው። አንድ ነገር አበክረን ከጅምሩ መናገር ያለብን ነገር፤ የመንፈሳዊነት ጥያቄ መጽሐፍ ቅዱስ ራሱ ከዘፍጥረት እስከ ራእይ ጠይቆ የመለስው ጉዳይ መሆኑን ነው። እግዚአብሔር እኮ ልጁንና መንፈሱን ወደ ምድር የላከበት ዓላማ ይህ የመንፈሳዊነትን ጥያቄ ነው። ይህ በአንድ ቃል መ.ቅ. “ኪዳን” ይለዋል። 'እግዚአብሔር በሕዝቡ መካከል መመላለሱና እርሱ አምላካቸው እነርሱም ደግሞ ሕዝቡ' የመሆን ጥያቄ ነው። ስለዚህ እኔ መልስ ነው ብዬ እንደ አርማ ያነገብኩት መንፈሳዊነት በእግዚአብሔር ቤት እንደመፍትሔ ከመቅረቡና ጉባኤው ምላሽ እንዲሰጥ ከመጠየቁ በፊት፤ በቅዱስ መጻሕፍት ሊፈተሽ፤ ሙሉነቱ ሊለካ፤ በበሰሉ መሪዎች ሊመዘን ደግሞም በቅዱስ ጉባኤ ሊመከርበትና አጥጋቢ መልስ እንደሆነ ከታመነበት ብቻ በፈሪሃ እ/ርና በትህትና ሊተገበር የሚገባው ነገር ነው።
Day 1 Day 2Day 3Day 4Day 5Day 6Day 7Day 8Day 9
