- በመጀመሪያ ደረጃ፤ ባለፉት ንባብ እንዳየነው፣ የቅዱሳት መጻሕፍትን ሙሉ ምክር ስሌት ውስጥ ያስገባ ሊሆን ይገባዋል (Biblical Exposition and Theology)። ምን ያህል ቃሉን በጥልቀት እናውቃለን? ይህ በተለይ የመንፈሳዊነት ጥያቄን መመለስ የእለት-ተለት ሥራችን ለሆንን በተለየ መልክ መቅረብ ያለበት ማሳሰቢያ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ "መንፈሳዊ" ለተባለው ማዕድ ቅመማ-ቅመም አይደለም። ይህ ምን ለማለት ነው፤ አንዳንዴ አቀራረባችን ልክ መጽሐፍ ቅዱስ ጥሬ ሽንኩርትና ድንች ሆኖ፤ እኛ በተለየ ጥበባችን አብስለን ማቅረብ ያለብን ነገር ይመስለናል። ሆኖም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የምናየው መንፈሳዊነት፤ በስሉሱ አምላክ አቀናባሪነት ለሰው ልጆች በዓመታት መካከል ተቁላልቶ የበሰለ ምርጥ ማዕድ ነው። ይህ ማዕድ አያረጅም፤ በዘመናት መካከል ቃናው አይለውጥም፤ ተበላሽቶም አይሸትም። ስለዚህ የመጀመሪያው ጥሪ የመስማት ጥሪ ነው። እግዚአብሔር ያቀረበውን ማዕድ ለሕዝብ የማቅረብ ሃላፊነት ነው። የታማኝነት ጥሪ እንጂ የመጠበብ ጥሪ አይደለም። ከዘይቤው ልውጣና፤ ለቆሮንቶስና ለሮሜ ሰዎች የተጻፉት ደብዳቤዎች ዓላማ ከርስቶስ መሰል መንፈሳዊነት ምን ማለት እንደ ሆነ ለመመለስ ነው። ስለዚህ መፈሳዊነት ምንድር ነው ለሚለው አጥጋቢ መልስ ለማግኘት በመጀመሪያ የሮሜን መጽሐፍ በጥልቀት መመልክትና መገንዘብ ይኖርብናል (ወይም 66ቱንም መጻሕፍት)። ለምሳሌ ሮሜ 6 ላይ “በአዲስ ሕይወት እንድንመላለስ፥ ከሞቱ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ በጥምቀት ከእርሱ ጋር ተቀበርን” የሚለው የመንፈሳዊ ህይወት መልስ ነው።ይህም ማለት ቅዱሳት መጻሕፍት በሙሉ የሚጠይቁትና የሚመልሱት ርዕሰ ጉዳይ የዚህ የመንፈሳዊነት ጥያቄ ነው። ሰለዚህ መንፈሳዊነት ምንድር ነው? ለሚለው ጥያቄ ጥልቅ መጽሐፍ ቅዱሳዊና ነገረ-መልኮታዊ እውቀት አማራጭ የለሽ ነው። በቃሉ ውስጥ የተገለጠውን የእግዚአብሔርን ሙሉ ምክር ለመጨበጥ እና ለመማር ፈቃደኛ ያልሆንን ሁሉ ይህንን መልስ ለመመለስ ገና ብቁ አይደለንም።
- በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ መንፈሳዊነት የዘመኑን ዘመናዊ ጥያቄ በጥልቀትም የተገነዘበ ሊሆን ይገባዋል (Contextualization and Relevance)። እኛ አሁን በመጀመሪያው ክፍለ ዘመን በቆሮንቶስ ከተማ አይደለም የምንኖረው። የአይሁድና የአሕዛብ የእርስበርስ ግንኙነት፤ አብሮ ከአንድ ማዕድ የመብላት ጥያቄ፤ ቀናትን የማክበርና ሰንበታትን የመጠበቅ ጉዳይ እንዲሁም እነዚህ ከወንጌል ጋር ያላቸውን እንደምታ በጥልቀት መዳሰስ ለእኛ በቀጥታ ርባናው (relevance) ጥቂት ነው። ያ ጥያቄ የኛ ጥያቄ ስላልሆነ። ይህ ማለት ግን በቅዱሳት መጻሕፍት ላይ ተጠይቆ ሲመለስ የምናየው ጥያቄ ለጥያቄያችን ረብ-የለሽ (irrelevant) ነው ብሎ ማሰብ ግን ስህተት ነው። ምክኒያቱም እ/ር የእኛን ጥያቄ ሊመልስ የወደደው በእነርሱ ጥያቄ ውስጥ ነውና። ጌታም ሲናገር “ለእናንተም የምነግራችሁ ለሁሉ እላለሁ” (ማር. 13:37) እንዳለው ነው። ለእኛ ለዘመናዊዎቹ ሰዎች የቀረበልን ሕይወት የተሰጠን በጥንታዊው ዓለም ቡሉኮ ውስጥ ነው።
Day 1 Day 2Day 3Day 4Day 5Day 6Day 7Day 8Day 9
