መቼም ሞቱንና ትንሳኤውን አክብረን ስናበቃ ራሳችንን ማሳሰብ ያለብን ብዙ ነገሮች እንዳሉን ይሰማኛል። ከእነዚህ አንዱና ዋነኛ ግን “መንፈሳዊነት ምን ማለት ነው?” የሚለው መሆን አለበት። ይህ ወቅት ሞቱንና ትንሳኤውን ይዘን ሳናሰልስ ወደ ሥራ የምንሔድበት እንጂ፤ ወደ ሌላ ርእሰ-ጉዳይ የምንሸጋገርበት እንዳልሆነ ሁላችንም እናውቃለን። ይህ የሰሞኑ የመስቀልና የትንሳኤ ጉዳይ፣ ሌሎች አንገባጋቢ ጉዳዮቻችንን ወደ ጎን የሚያደርግ ሳይሆን፤ በእያንዳንዱ ጉዳዮቻችን ውስጥ ግን እንደ ጅማት ሊዘረጋ፤ እንደ ደም ስር ሊቀጣጠል፤ እንደ ደም በመላ የክርስትና ሕይወታችንና የቤተክርስቲያን ጉዳዮቻችንን ሊሰራጭ ይገባል። ጭንቅላት የሰውነት ብልቶች ተግባሮቻቸውን እንዲያከናውኑ ሁሉን እንደሚቆጣጠር፣ ይህ የሰሞኑ እውነታ የተግዳሮታችን ሁሉ ዓውድ ይሆን ዘንድ ልባዊ ጸሎቴ ነው። ስለዚህ መንፈሳዊ ሕይወት የመስቀልና የትንሳኤውን እውነታ የሚያንጸባርቅ መሆን አለበት። እንዲህ ከሆነ መንፈሳዊ ህይወት መስቀሉንና ክርስቶስን እንዲሁም በመስቀሉ ሥራ ላይ የተሳተፉት ስሉስ መለኮታዊ አካላትን የሚገልጥ መሆን አለበት። ትዝ አይላችሁም በቆሮንቶስ የነበረው የጸጋ-ሥጦታን አጠቃቀም ያለማወቅ ችግር? ምክኒያቱ? ስሉሱን አምላክ ያለማወቅ ችግር እንደሆነ ጽፎልናል “ስለ መንፈሳዊ ነገርም፥ ወንድሞች ሆይ፥ ታውቁ ዘንድ እወዳለሁ...መንፈስ አንድ ነው...ጌታም አንድ ነው...እግዚኢብሔር [አብ] አንድ ነው" (1 ቆሮ 12:1-6). ” መንፈሳዊ ስጦታ የእግዚአብሔርን ክብርና ማንነት የሚገልጥ ነው እንጂ፣ ይለናል ጳውሎስ፤ የራሳችን እውነታ የምገልጥበት መንፈሳዊ-ልዕልና አይደለም። ይህም ከመንፈሳዊ ህይወት ጀርባ ጥልቅ ነገረ መለኮታዊ እውነታ አለ ማለት ነው።
Day 1 Day 2Day 3Day 4Day 5Day 6Day 7Day 8Day 9
