ሐዋርያው ጳውሎስ ምንም እንኳ ክርስቶስ ራሱ የመሰረታት እና አለት ሆኖ ያጸናትና ያቆማትን ቤተ ክርስቲያን ሲያገለግል የኖረ ቢሆንም የወደ ፊቱን የቤተ ክርስቲያን ሁኔታ ሲያስብ ግን ጥሩ ነገር አልታየውም ነበር። ይልቅስ ብዙዎች ‹ትክክለኛ የሆነውን ትምህርት የማይቀበሉበት ዘመን› እንደሚመጣ አይቶ በእምነት ልጁ የሆነውን ጢሞቴዎስን ሲያስጠነቅቀው እናነባለን (2ኛ ጢሞቴዎስ 4:3) ። ሐዋርያው በመጨረሻዎቹ ቀናት የተጋፈጠው በጊዜው ከነበረው ክህደት እና ተቃውሞ ጋር ብቻ ሳይሆን ገና ከእርሱ ዘመን በኋላ ሊመጣ ካለው አስፈሪ ክህደት ጋርም ነበር።
መጽሐፍ ቅዱስ ቀጣዩ ዘመን ጥሩ ነው ብሎ ተስፋ አይሰጠንም። አለም በክፋቷ እየቀጠለች ፤ ብዙዎች ከእውነት እየራቁ እና ወደ ክህደት እያመሩ እንደሚመጡ አመልክቶናል (2ኛ ጢሞቴዎስ 3:1-9)። ይህንን አስፈሪ የወደፊት ሁኔታ እያሰበን ዛሬ ላይ ወንጌሉን ለመስበክ እና በእውነተኛ ከክርስቲያናዊ ኑሮ ለመገኘት ጽናቱ ያለን ስንቶቻችን ነን?
ሐዋርያው ጳውሎስ ምንም እንኳ የወደፊቱ የዓለም እና የቤተክርስቲያን ሁኔታ አስጊ እንደሆነ ልቡ ቢያውቅም ከዚያ በበለጠ ሁኔታ የኢየሱስ ክርስቶስን መገለጥ(2ኛ ጢሞቴዎስ 4:1) የሚጠባበቅ እና የሚናፍቅ ስለነበረ ደግሞም የክፋቱ እና የክህደቱ መብዛት በሙሉ የጌታን መምጫ መቅረብ አመላካች እንደሆነ ስለተረዳ በጽናት እምነቱን ጠብቆ ጉዞውን ፈጽሟል።
ስለ አለም ሁኔታ ምን ይታየናል? ስለ ቤተ ክርስቲያንስ? እለት እለት የምንሰማቸው ዜናዎች አስጨናቂ እና አስጊ አይደሉምን? ይህ የወደፊት ሁኔታ ከፊታችን እንዳለ በማወቅ ዛሬ ላይ ጸንተን ከወንጌሉ የተጣበቅን ስንቶቻችን ነን?
ጳውሎስን ከጎኑ ቆሞ ያበረታ እና ያጸና አምላክ (የሐዋርያት ሥራ 23፡11) እኛንም ያበርታን ደግሞም ያጽናን! አሜን!
IntroductionDay 1 Day 2Day 3Day 4Day 5Day 6Day 7Day 8