ሐዋርያው ጳውሎስ በዴማስ ብቻ አይደለም የተተወው። በእስያ አውራጃ ያሉት ሁሉ ትተውት ነበር። እነዚህ "በእስያ አውራጃ ያሉት ሁሉ" ተብለው የተጠቀሱት ምናልባት ሐዋርያው ራሱ ወንጌል የሰበከላቸው እና ያስተማራቸው ሊሆኑ እንደሚችሉ ይታመናል። እነዚህ ሰዎች በመልካም ጊዜ ሐዋርያውን ሲያበረታቱ የነበሩ ሊሆኑ ይችላሉ። አሁን በጨለማ እስር ቤት ውስጥ ሲሆን ግን ሁሉም ተውት? የጳውሎስ ጽናት ምን ያህል ይፈተናል?!
ዛሬ ምንድነው ሰዎች ሁሉ ትተውን ብቻችንን እየተጋፈጥነው ያለው ጉዳይ? ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ስም እና ስለክርስትና ሕይወት እየተገለልን እና እየተሸፈብን እውነት ከእኛ ጋር የሌለች እስኪመስል ድረስ ሆነን ይሆን? ለእኛ የሐዋርያው ጳውሎስ የመጨረሻ ቀናት እጅግ ትምህርት ይሆኑናል! ጳውሎስ ምንም እንኳ በእሲያ አውራጃ ያሉት ቢተውትም እርሱ ግን ያመነውን እውነት ይዞ እስከመጨረሻው ድረስ በጽናት ተጉዟል!
አንድ የእግዚአብሔር ሰው እንዳሉት ይህ ዘመን ሰዎች ‹በአይናቸው የሚያስቡበት እና በስሜታቸው የሚያዩበት› ዘመን ነው። ብዙ ተከታይ ያለው የትኛውም ነገር እውነተኛ እንደሆነ ይታሰባል። ስሜትን የሚያስደስተውን የትኛውንም ነገር ለማየት ሰዎች ሁሉ ወደ አንድ ቦታ የሚጎርፉበት ጊዜ ነው። በዚህ ጊዜ ስለ ክርስቶስ ስም እና ስለ ጨዋ ክርስቲያናዊ ሕይወት የሚሰደብ እና የሚገፋ ሁሉ በብዙዎች ዘንድ እንደሞኝ ተቆጥሮ ይተዋል። ታዲያ ‹አለም ሁሉ እኔን ቢቃወመኝ ፤ እኔ ብቻዬን አለም እቃወማለሁ› የማለቱ አቅም ይኖረን ይሆን? ›
ጳውሎስን ከጎኑ ቆሞ ያበረታ እና ያጸና አምላክ (የሐዋርያት ሥራ 23:11) እኛንም ያበርታን ደግሞም ያጽናን! አሜን!
IntroductionDay 1 Day 2Day 3Day 4Day 5Day 6Day 7Day 8