ሐዋርያው ጳውሎስ በሮም እስር ቤት ሆኖ ጽናቱን ከፈተኑት ጉዳዮች መካከል እነዴማስ አለምን ወደው እርሱን መተዋቸው ብቻ አይደለም። በእስያ ያሉት ሁሉ ጳውሎስን መተዋቸው ብቻም አልነበረም። ነገር ግን በግልጽ ጳውሎስን እና የእርሱን ትምህርት የሚቃወሙ ሰዎች ነበሩ። ከእነርሱም መካከል አንጥረኛው እስክንድሮስ በስም ተጠቅሷል (2ኛ ጢሞቴዎስ 4:14)። አንጥረኛው እስክንድሮስ ምናልባት መዳብ በማንጠር ሙያው የታወቀ ሊሆን እንደሚችል ይታመናል። ነገር ግን ሐዋርያው ጳውሎስ ላይ ብዙ ጉዳት አድርሶበታል። አካላዊ ጉዳት ያድርስበት አያድርስበት ግልጽ ባይሆንም ስነልቦናዊ ጉዳት እንዳደረሰበት ግን እርግጥ ይመስላል። ከዚህም በላይ እስክንድሮስ ጳውሎስን እየተከታተለ ይቃወመው እንደነበርም ከክፍሉ መረዳት ይቻላል።
ዛሬ የእኛ እስክንድሮስ ይኖረን ይሆን? ልባችንን በተቃውሞ እያቆሰለ ፤ ስማችንን በመጥፎ እያነሳ ፤ ሰዎችን በእኛ ላይ እያሳመጸበን ያለ የመልዕክታችን ተቃዋሚ ይኖር ይሆን? ተቃዋሚዎች በእርግጥ ጽናታችንን ይፈታተኑታል። ሁሉንም እርግፍ አድርገን እንድንተው ሊጋብዙን ይችላሉ። ወይም ወዳልሆነ የጠብ አቅጣጫ ሊጎትቱን ይችላሉ። ሐዋርያው ጳውሎስ ግን በተቃውሞ ፊት ያውም በእስርቤት ጽኑ ነበር!
ሐዋርያው ያልተፈለገ ምላሽንም ለመስጠት አለፈለገም። ይልቅስ ሁሉንም ለእግዚአብሔር አሳልፎ ሲሰጥ እናነባለን (2ኛ ጢሞቴዎስ 4:14) ። እኛስ ሁሉን ለእግዚአብሔር አሳልፈን ሰጥተን ተልዕኳችንን እና መልዕክታችንን ሳንለውጥ በተቃዋሚዎች ፊት ጸንተን መቆም እንችላለን?
ጳውሎስን ከጎኑ ቆሞ ያበረታ እና ያጸና አምላክ (የሐዋርያት ሥራ 23:11) እኛንም ያበርታን ደግሞም ያጽናን! አሜን!
IntroductionDay 1 Day 2Day 3Day 4Day 5Day 6Day 7Day 8