ሐዋርያው ጳውሎስ በሮሜ የጨለማ እስር ልቡን ሊጎዳ እና ጽናቱን ሊፈታተን ከሚችለው አንዱ ገጠመኝ የዴማስ አለምን ወዶ ጳውሎስን ትቶ ወደ ተሰሎንቄ መሄዱ ነው። ዴማስ በአንድ ወቅት ከጳውሎስ ጋር የነበረ የአገልግሎት አጋሩ ነበር። ለዚህም ማረጋገጫ የሚሆነን ሐዋርያው በሌላኛው ደብዳቤው ላይ ዴማስን ከማርቆስ እና ከሉቃስ ጋር አብሮ መጥቀሱ ነው (ፊልሞና 1:24) ። ታዲያ ጳውሎስ በሁለተኛው እስር ላይ እያለ ዴማስ ጳውሎስን ትቶ አለምን ወዶ በጊዜው ትልልቅ ከሚባሉት ከተሞች ተርታ ወደምትመደበው ወደ ተሰሎንቄ ሄዷል። ብዙ መጸሐፍ ቅዱስ አንባቢያን እንደሚስማሙበት ምናልባት ዴማስ ጳውሎስን ትቶ ተሰሎንቄን የመረጠው በገንዘብ ፍቅር ተነድፎ ሊሆን ይችላል። እንዲያ ከሆነ ደግሞ ዴማስ ጳውሎስን ብቻ ሳይሆን ጌታንም ትቶ ነው የሸሸው።
ወዳጆች ሆይ በድሎት እና በነጻነት ዘመን ሳለን የሚከዱን ይጎዱናል። ነገር ግን እንደ ጳውሎስ በመከራ ውስጥ ሳለን የሚከዱን ምን ያህል ልባችንን ይሰብሩታል? ዘመናችንን ከኖርንለት እና ከተሰደድንለት ወንጌል የቅርብ ወዳጆቻችንን መከራን ፈርተው አልያም ገንዘብን ወደው ከእኛም ከጌታም ሲርቁ ማየት ጽናታችንን ይፈታተነዋል። ነገር ግን ሐዋርያው አሁንም ጽኑ ነበር! ስለተረዳው እውነትም ሆነ ስለተቀበለው አገልግሎት አላመቻመቸም። አስቀድሞም እምነቱ በስጋ እና ደም ምክክር ላይ አልተመሰረተም (ገላትያ 1:12) ።
ዛሬ እንደ ሐዋርያው አይነት መከራ አይነት ባይሆንም መከራ ግን አለ። በመከራ ውስጥ ጽናታችን የሚፈተነው አንድም የምናውቃቸው ሰዎች ትተውን ሲሄዱ እኛ ለመልእክታችን እና ለጥሪያችን ታማኝ ስንሆን ነው። ክርስቶስን እናገለግላለን ለምንል ሁሉ ይህ መልዕክት ነው! የቅርብ የአገልግሎት አጋራችን ቢያፈገፍግ እኛ በጽናት አንቆያለን?
ጳውሎስን ከጎኑ ቆሞ ያበረታ እና ያጸና አምላክ (የሐዋርያት ሥራ 23:11) እኛንም ያበርታን ደግም ያጽናን! አሜን
IntroductionDay 1 Day 2Day 3Day 4Day 5Day 6Day 7Day 8