Tuesday, 19 March 2024

የእግዚአብሔርን የጸጋ ግምጃ ቤት ክፈቱ

Posted On %AM, %11 %041 %2016 %03:%Oct Written by

ያጣችሁት ነገር ላይ ዓይንን እንደመጣል እምነትን የሚያደክም ነገር የለም። 

እንደተረዳሁት ከሆነ ዓይኖቼን በቁሳዊ ማጣቶቼ ላይ ፣ በሌሉኝ ጥንካሬዎች እና በሌሉኝ ድክመቶች ላይ ባደረግሁ ጊዜ ያለማመን ሸክም ይከብድብኝና ሩጫዬን ከባድ ያደርግብኛል (ዕብራዊያን 12፡1)። 

እጥረትን ማየት ፍርኃትን ያቀጣጥልና ተስፋችንን ሙጥጥ አድርጎ ይጨርሰዋል። እጥረት ክፍያን ለመክፈል፣ ፍላጎትን ለማሟላት፣ ስብከትን ለመስበክ፣ ትዳርን ለማስተካከል፣ ልጆችን ለመምራት፣ ኃጢያትን ለማሸነፍ ወይንም ድካማችንን ለመቋቋም በቂ የሆነ ነገር የለንም ይለናል። በእይታችን እጥረት እያለ ልበ ሙሉ ውሳኔ መወሰን አንችልም።

በሌላ እጅ ደግሞ መትረፍረፍን ስናይ ያበረታታን እና በተስፋ ይሞላናል። መትረፍረፍ ማለት ለሚያስፈልገን ነገሮች ሁሉ ከበቂ በላይ አለ ማለት ነው። መትረፍረፍ ደግሞ አስፍተን እንድናልም እና በልግስነት ለሌሎች እንድንዘረጋ ያደርገናል።

ምንም እጥረት የለባችሁም

ለእራሳችን ብንተወው የሚያስፈሩ እጥረቶች አሉብን። በዚህች ምድር ላይ ያለ እግዚአብሔር ተስፋ ቢስ ለመሆን በቂ ምክንያት አለን (ኤፌሶን 2፡12)።

የምሥራቹ ግን ክርስቲያን ከሆናችሁ ምንም እጥረት የለባችሁም። ምንም። ክርስቶስ ሊለካ የማይችለውን የኃጢያታችሁን ዕዳ ብቻ ሳይሆን የከፈለላችሁ (ቆላስይስ 2፡14) ሁሉንም ነገር ደግሞ ገዝቶላችኋል (ሮሜ 8፡32)። ሁሉንም ነገር! ያላችሁ የማያልቅ አንድ ማድጋ ዘይት አቅርቦተ እግዚአብሔር ነው (1 ነገሥት 17፡14)። የባንክ አካውንታችሁ ስባችሁ ልትጨርሱት ከምትችሉት በላይ ነው።

ይሄ ልምምዳችን ሆኖ የማያውቅ ከሆነ ይህንን ድንቅ እውነታ ልክ ነው ለማለት እንቸገራለን። ይሄ የተጋነነ የብልጽግና ወንጌል አስተሳሰብ አይደለም። ይሄንን ነው መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ እና ማብራሪያ በማያስፈልገው መልኩ እዚህ ባለን ሕይወት እንድንለማመደው የሚጠይቀን:- 

"አምላኬም እንደ ባለ ጠግነቱ መጠን በክብር በክርስቶስ ኢየሱስ የሚያስፈልጋችሁን ሁሉ ይሞላባችኋል" (ፊሊጵስዩስ 4፡19)

"እግዚአብሔር፥ ሁልጊዜ በነገር ሁሉ ብቃትን ሁሉ አግኝታችሁ ለበጎ ሥራ ሁሉ ትበዙ ዘንድ፥ ጸጋን ሁሉ ሊያበዛላችሁ ይችላል"   (2 ቆሮንቶስ 9፡8-9)።

የሚያስደንቁ ተስፋዎች ናቸው። ላለመታመም ግን ተስፋ አይደለም (ፊሊጵስዩስ 2፡25-27) ወይንም ደግሞ ለተጋነነ ሀብት (ፊሊጵስዩስ 4፡12)። ነገር ግን ለበጎ ሥራ ሁሉ ትበዙ ዘንድ “ልግስናን ሁሉ እንድታሳዩ በሁሉ ነገር ባለ ጠጎች እንድትሆኑ” እግዚአብሔር የሚያስፈልገንን ነገር ሁሉ ያዘጋጃል (2 ቆሮንቶስ 9፡11)።

የግምጃው ቤት ቁልፍ

እነዚህ የአቅርቦተ-እግዚአብሔር ተስፋዎች ግልጽ እና ማብራሪያ የማያስፈልጋቸው አይደሉም። ነገር ግን እንዲሁ የሚገኙ አይደሉም። ማግኛው መንገድ ደግሞ እምነት ነው (ማቴዎስ 17፡20፤ ዮሐንስ 11፡40፤ ያዕቆብ 1፡5-7)። የአቅርቦተ እግዚአብሔርን ግምጃ ቤት በመክፈት የእግዚአብሔርን የማያልቅ ባንክ የምንደርስበት መንገድ እምነታችንን በማለማመድ ነው። እነዚህ ተስፋዎች ላይ ድርጊት ካልወሰድን እንደተዘጉ ይቀራሉ።

አለማመን እጥረት ነው ብለን ምናስበውን እንድናይ እና ልባችንን እንዲዝል ያደርጋል። አለማመን ግምጃ ቤቱ ውስጥ ምንም ይኖራል ብሎ ስለማያምን አይከፍተውም። አለማመን ለሚያስፈልገው ነገር አቅርቦት አለ ብሎ ስለማያምን አያወጣቸውም።

አለማመን ከእውነተኛ አስተምህሮ ጋር በቀላሉ ተስማምቶ ሊኖር ይችላል። ከእነዚህ ተስፋዎች እውነተኛነት ጋር ልንስማማ እንችል ይሆናል ነገር ግን ድርጊት ወስደን እስካልተጠቀምንባቸው ድረስ ምንም አይጠቅሙንም። ምክንያቱም የእውነት ስላላመናቸው ነው።

በእነዚህ ተስፋዎች ውስጥ እግዚአብሔር የተትረፈረፈ አቅርቦቱን ያሳየናል። እምነት ይህን ግምጃ ቤት የምንከፍትበት ቁልፍ ነው። እግዚአብሔር የተትረፈረፈ ጸጋውን እንድናገኝ ይፈልጋል። ነገር ግን እምነትን ይፈልጋል ምክንያቱም “ያለ እምነትም ደስ ማሰኘት አይቻልም . . . [ነገር ግን] እንዳለ ለሚፈልጉት ዋጋን ይሰጣል።" (ዕብራዊያን 11፡6)

የእጥረትን ክለሳ አቁሙ

እንደ እኔ ከሆናችሁ የዚህን ጊዜ “አውቃለሁ! ነገር ግን በቂ እምነት እንደሌለኝ መናገርህ የተሻለ እንዲኖረኝ እየረዳኝ እይደለም። የበለጠ እጥረቴን እያሳየኝ እና የበለጠ እንደተሸነፍኩ እንዲሰማኝ እያደረገ ነው! የበለጠ እምነት እንዴት ሊኖረኝ እንደሚችል አሳየኝ”  እያላችሁ ሊሆን ይችላል።

እንግዲያውስ ጥሩ! እምነት የጎደለን ደቀ መዛሙርት (ሉቃስ 12፡28) መሆን ሲሰለቸን እርምጃን ለመውሰድ ዝግጁ ነን ማለት ነው።

ለውጥ የሚጀምረው የእጥረት ክለሳችንን ስናቆም ነው። የቁሳ ቁስ፣ የጥበብ፣ የኃይል፣ የእምነታችንንም እጥረት መመልከት ማቆም አለብን። እጥረታችን እምነትን ይቀንሳል። ለዚህ ነው ሰይጣን የሚወቅሳችሁ፣ ክስረታችሁን የሚያሳያችሁ እናም ስለእራሳችሁ በተቻላችሁ መጠን እንድታስቡ ያበረታታችኋል። ኢየሱስን እና የእናንተ ስላደረገላችሁ የተትረፈረፈ ጸጋ እንድታዩ አይፈልግም።

አስቀድማችሁ መንግሥቱን ፈልጉ

ነገር ግን ወደ ኢየሱስ ብንመለከት እምነታችንን እንዴት እንደምንጨምር ያሳየናል። መጀመሪያ እንደዚህ ይላል:-

"እናንተም የምትበሉትን የምትጠጡትንም አትፈልጉ፥ አታወላውሉም ይህንስ ሁሉ በዓለም ያሉ አሕዛብ ይፈልጉታል የእናንተም አባት ይህ እንዲያስፈልጋችሁ ያውቃ። ዳሩ ግን መንግሥቱን ፈልጉ ይህም ሁሉ ይጨመርላችኋል።" (ሉቃስ 12፡29-31)

እግዚአብሔር የዚህን አለም እጥረት ሳይሆን ወደ አባታችን መንግሥት መመልከት አለብን። መንግሥቱን ቀዳሚ ነገራችን ካደረግን የሚያስፈልገንን ነገር በሙሉ እርሱ ያሟላል። ምን አይነት ቅድሚያ ነገሮች? እግዚአብሔርን ጠይቁና ወደ መጽሐፍ ቅዱስ ተመልከቱ። እርሱ ግልጽ ያደርግላችኋል።


ቀጥሎም ኢየሱስ እንደዚህ ይላል፡-

"አንተ ታናሽ መንጋ፥ መንግሥትን ሊሰጣችሁ የአባታችሁ በጎ ፈቃድ ነውና አትፍሩ። ያላችሁን ሽጡ ምጽዋትም ስጡ፤ ሌባ በማይቀርብበት ብልም በማያጠፋበት በሰማያት የማያልቅ መዝገብ የሚሆኑትን የማያረጁትንም ኮረጆዎች ለራሳችሁ አድርጉ፤ መዝገባችሁ ባለበት ልባችሁ ደግሞ በዚያ ይሆናልና።"(ሉቃስ 12፡32-34)

ኢየሱስ ደህንነታችንን ከምንጠብቅባቸው ጣዖቶቻችን በማላቀቅ እምነታችንን እንድናለማምድ ይነግረናል። ኢየሱስ ተስፋውን እንድንፈትን እና እንዳንፈራ ግድ ይለናል። አባታችን መንግሥቱን እና በውስጡ ያሉትን መዝገቦች ሊሰጠን ደስተኛ ነው!


የእጥረታችሁን ሸክም

• እጥረትን ባለመመልከት፣

• ይልቅ አሁን የእናንተ ወደሆነው ወደበዛው የጸጋ ምንጫችሁ እና የማያቋርጥ መትረፍረፍ በመመልከት፣

• የአባታችሁን መንግሥት ቅድሚያ በመፈለግ ፣

• የውሸት የሆኑትን ጥበቃዎቻችንን በማስወገድ በለጋስነት በመስጠት፣

ከላያችሁ ላይ አስወግዱ።

የእግዚአብሔር ተስፋ ይህንን ብናደርግ እርሱ ሲሰራ እንደምናየው እምነታችንም እንደሚያድግ ነው።

 

Originally Posted at DesiringGod.org, Translated by Joshua Terefe


 

Last modified on %PM, %10 %870 %2016 %22:%Dec
Jon Bloom

Jon Bloom serves as author, board chair, and co-founder of Desiring God. He is author of three books, Not by Sight, Things Not Seen, and Don’t Follow Your Heart. He and his wife live in the Twin Cities with their five children.

https://twitter.com/Bloom_Jon

የተስፋ ነፀብራቆች ሁኑ

“ስለዚህ እናንተ ደግሞ እንደምታደርጉ፥ እርስ በርሳችሁ ተመካከሩ አንዱም አንዱም ሌላውን ያንጸው” (1 ተሰሎንቄ 5፡11)። “ትውልዱም የቆጵሮስ ሰው የነበረ ...

Jon Bloom - avatar Jon Bloom

ጨርሰው ያንብቡ

የእግዚአብሔር ሞራላዊ (ግብረ ገባዊ) እና ሉአላዊ ፍቃዶች

የእግዚአብሔርን ሞራላዊ (ግብረ ገባዊ) እና ሉአላዊ ፍቃዶች መለየት እንድትችሉ ልረዳችሁ እፈልጋለሁ። ቀጥሎ ባሉት ሁለት ሃሳቦች መሀከል ያለውን ተቃርኖ መረዳት...

John Piper - avatar John Piper

ጨርሰው ያንብቡ

 

The views and opinions expressed on Daily Injera are solely those of the original authors and our contributors. These views and opinions do not necessarily represent Daily Injera or our Staff.

Newsletter

Subscribe to our newsletter. Don’t miss any article, devotionals or wallpapers.

We do not spam!

You're automatically subscribed to bi-weekly articles and daily devotionals. You can customize your subscription settings here.