Tuesday, 19 March 2024

ድክመታችሁን ለእግዚአብሔር ስጡት

Posted On %AM, %05 %041 %2017 %03:%May Written by

እንደምን አላችሁ?

ጥፋተኛ ብሆንም እነዚህ ቃላት እንደ ጥያቄ ሳይሆን እንደ ሠላምታ ሲቀርቡልኝ ትንሽ ይረብሸኛል። ተጨባጭ መልስ ሳንፈልግ “እንዴት ናችሁ?” ብሎ መጠየቅ ቀላል ነገር። አንዳንድ ጊዜ ሰዎች ከእርምጃቸው እንኳን ሳያቋርጡ ደህና ነህ? ብለውኝ ያልፋሉ። በእነዚህ ጊዜያት ብቸኛው ተገቢ መልስ “ደህና ነኝ” ነው የሚሆነው ምንም እንኳን ነገሮች ላይሆኑ ቢችሉም። የዚህ አይነቱ ጥልቅ ያልሆነ ሰላምታ ብዙውን የየዕለት መስተጋብራችንን ይሸፍናል። ግንኙነቶቻችንን ብዙ ጊዜ ከላይ ከላይ እንፈጽማለን ነገር ግን ወደ ልባችን ስላለበት ትክክለኛ ሁኔታ ጠልቀን አንገባም።  

ማሕበረሰብ:-  የእውነታ ስፍራ

የክርስቲያኑ ማሕበረሰብ ሰዎች ደካማ ጎናቸውን ግልጽ ከሚያደርጉባቸቸው ቦታዎች እንዱ መሆን አለበት። ከክርስቲያኖች ጋር ስንሰባሰብ የሕይወትን እውነታዎች ከማንደብቅባቸው ጥቂት ጊዜዎች አንዱ መሆን አለበት። ደካማ ጎናችንን ግልጽ ማድረግ ማለት ስለኃጢያታችን ወይንም ስለ ስብራታችን ወይንም ድክመቶቻችን አሊያም ሕይወታችን ስላለበት ውጥንቅጥ እውነተኛ መሆንን ማለት ሊሆን ይችላል። ደካማ ጎንን ግልጽ ማድረግ ባለፈ ጊዜ የነበረን ፀፀት፣ ጭንቀትን፣ ብቸኘነትን፣ ሃዘንን ወይንም በአጠቃላይ ማንኛውንም አይነት ደስታ ወይንም እርካታ ማጣትን ያጠቃልላል። አንዳንዶች ምንአልባት እግዚአብሔርን እየተጠራጠሩ ወይንም እንደ አንድ ባል፣ ሚስት፣ ወላጅ ወይንም ሠራተኛ ያለመብቃት ስሜት እየተሰማቸው ሊሆን ይችላል።

ክርስቲያኖች ግልጽ እና እውነተኛ እንዲሆኑ እየተጠበቀባቸው ግልጽ ሳይሆኑ መቅረታቸው አደገኛ ነው። አንድ ሰው ግን ስለሆነ ጉዳይ እራሱን ቢከፍት እና ሌሎች በደንታ ቢስነት፣ በተለመዱ የክርስቲያን መልሶች፣ በጸጥታ፣ በድንጋጤ፣ በመፀየፍ ቢመልሱለት ተስፋ ያስቆርጠዋል፤ ግልጽነቱንም ሊከለክለው ይችላል። ለተናጋሪውም ሆነ በሕብረቱ ውስጥ ላሉት ለሌሎች ያካፈላቸው ነገር ጠቃሚ እንዳልሆነ ይሰማቸዋል።ሌሎች ይህንን ክስተት እያስታወሱ የእራሳቸውን ደካማ ጎን ላለማካፈል ይወስናሉ። ክርስቲያኖች እንደዚህ ላሉ ክስተቶች እንደሚገባ መመለስ ካልቻሉ ጓደኝነትንና አገልግሎትን ያሻክራል። ይህም ጥሩ ሊባል የሚችል አይነት ነገር ግን ከአንገት በላይ ወደሆኑ ግንኙነቶች ይመራል።

ነፃ የሚያወጣ ደካማ ጎንን መግለጽ ምንድን ነው?

ታዲያ ነፃ የሚያወጣ ደካማ ጎንን መግለጽ ምንድን ነው? ደካማ ጎንን ግልጽ ማድረግ ለጉዳት እራስን ማጋለጥ ነው። በማሕበረሰቡ አውድ ስናየው ደካማ ጎንን ግልጽ ማድረግ ሰዋዊ ባህሪያችንን ከፍቶ ማሳየት ነው። ፍጹማን እንዳልሆንን ማመናችን ነው። ገና እንዳልደረስን ማሳያ ነው። በውድቀት ምክንያት በተበላሸ ዓለም ውስጥ የምንኖር ተሰርተን ያላለቅን የተሰበርን ህዝቦች ነን። መንፈሳዊ ጭንቀት፣ ድካም፣ ካንሰር፣ ሃዘን፣ ሞት፣ ሮሮ፣ የአካል ጉዳት፣ በሽታ፣ ብቸኝነት፣ ሴሰኝነት እና የመሳሰሉት ብዙ ልንጠቅሳቸው የምንችላቸው ነገሮች ይገጥሙናል።  

ታሪካችን ግን በስብራት ማለቅ የለበትም። ነፃ የሚያወጣ ደካማ ጎንን መግለጽ አለ። ይህ አይነቱ ደካማ ጎንን መግለጽ ወደ ሕይወት የሚመራ የክርስቶስን ታላቅ ኃይል እና በቂነት ለማሳየት ድካማችንን የምናካፍልበት ዘወትር ክርስቶስን ወደ መምሰል የሚለውጠን ደካማ ጎንን የመግለጽ አይነት ነው። ደካማ ጎንን መግለጽ መጨረሻችን አይደለም። ነገር ግን ደካማ ጎናችንን መግለጻችን ለብቻችንም ሆነ ከሌሎች ጋር በአንድነት ኢየሱስ በቂ እንደሆነ ሊጠቁመን ይገባል። በኢየሱስ እና በመስቀሉ ሥራ ባገኘነው ነፃነት ላይ ተስፋ ያደርጋል።  

እግዚአብሔር ትልቅ የሚለውን ሥራ ለመሥራት በደካማ ሰዎች ይጠቀማል

ጳውሎስ የቆሮንቶስን ሰዎች የአካባቢው ጠቢባን፣ ኃያላን፣ ወይን ባላባቶች እንዳልነበሩ ነገር ግን በተቃራኒው ሞኝ የተባሉትን ደካሞች ዝቅ ያሉትን እና የተናቁትን እንደመረጣቸው ያስታውሳቸዋል (1 ቆሮንቶስ 1፡26-31)። እዚህ ጋር ጭብጡ ታላላቅ አላማዎቹን ለማስፈጸም እግዚአብሔር ሆን ብሎ ደካማዎችን እንደሚጠቀም ነው። እግዚአብሔር ይህንን የሚያደርግበት ምክንያት “ሥጋን የለበሰ ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት እንዳይመካ” (1 ቆሮንቶስ 1፡29) ነው። ክብሩ ለእግዚአብሔር ብቻ ነው።

እግዚአብሔር አላማውን ለማስፈፀም ኃያላንን ተጽእኖ ፈጣሪዎችን ወይንም ባህልን የሚገለባብጡትና የሚያንቀሳቅሱት አያስፈልጉትም። ነገር ግን ክርስቶስ ክብሩን ይወስድ ዘንድ ደካማ፣ ትሁት እና ሞኝ ወደሚባሉት በመሄድ ተዕዕኖ ማሳደርን ይሰጣቸዋል። እግዚአብሔር ሆን ብሎ ደካማዎችን ለታላቅ አላማው ይመርጣል። ደካማዎች እንደሆንን ስናምን በፊታችን ላይ ያደረግነውን ጭምብል እንዳይወልቅ ከመጠበቅ እናቆምና ነፃነትን፣ ፈውስን እና ላሉብን ችግሮች መፍትሄን ወደሚሰጠው ወደ እግዚአብሄር መልካምነት እና ብቃት እንመለከታለን።

ግልጽ ለሆነው ደካማ ጎናችን ነፃነትን ማምጣት

በቅርቡ አንድ ጓደኛዬ በአነስተኛ ቡድናቸው ውስጥ በአንድ ዓመት ውስጥ ብቻ ስለገጠማቸው የአንድ ሰው ወላጅ ሞት፣ ወንጀል፣ ከሱስ ካር የተያያዘ ክስ፣ ሥነ ልቦናዊ ችግር፣ በተመሳሳይ ፆታ መሳብ፣ የትዳር መቃቃር፣ የሥራ መቀየር እና አካል ጉዳት አጫወተኝ። ነገር ግን በየትኛውም ጉዳይ ላይ ጊዜ በማጥፋት አልዘገዩም። ፀለዩ፤ የእግዚአብሔር ቃል አጠኑ፤ እርስ በእርስ ተበረታቱ እናም እግዚአብሔር ማን እንደሆነ ሥራውን አስታወሱ። እንደ ማገገሚያ ጣቢያ አልሆኑም። ሰምተው ብቻ አላለቀሱም። ሰምተው ሲጨርሱ በአንድ ላይ ወደ እግዚአብሔር ተመለከቱ። በእነዚያ አስቸጋሪ ሁኔታዎቸ ውስጥ ሲያልፉ ልባቸውን እና አዕምሮአቸውን በ መጽሐፍ ቅዱስ እውነት እና ተስፋ ሞልተው ነበር።

ግልጽ ለሆነው ደካማ ጎናችን ነፃነትን ማምጣት ማለት እራሳችንን የምንከፍተው በሁኔታችን ለመዋጥ ሳይሆን አይኖቻችንን በጋራ ወደ እግዚአብሔር እንድናነሳ ነው። በአንድነት ወደ ሰጠን ተስፋዎች መመልከት እንችላለን። መጽናናትን፣ ጥበብን፣ እርዳታን እና እምነትን እንዲሰጠን በአንድነት ወደ እርሱ እንጮሀለን። አንዳንድ ጊዜ ለብቻችን ለመጸለይ ስለምንደክም አብረን ለመጸለይ እንድንችል እርስ በእርስ እንማማለን። ድካማችን እና ግልጽ የሆነው ደካማ ጎናችን እግዚአብሔር ላይ ጥገኛ እንደሆንን እና እርሱ በቂ እንደሆነ ያስታውሰናል። እግዚአብሔር በጥያቄ በተሞላንባቸው ጊዜያት ሊደርስልን እና  ከጊዜ ወደጊዜ ጸጋውን ስንፈልግ የበለጠ ደግሞ ከሌሎች ጋር ስናደርገው ደስ ይለዋል ጸጋውንም ያበዛልናል።  

አቋራጭ መንገድ የለም

ይሄን በማህበረሰባችን እና በግንኙነቶቻችን የሚሰራበት መንገድ ጥበብ ይጠየቃል። ቀላል እና ቀጥተኛ አይደለም። ቀጥተኛ መልስ የማይኖራቸው ብዙ ከባባድ ነገሮች ውስጥ ልናልፍ እንችላለን። ወንጌልን ስንተገብር ልክ ካንሰርን ለማከም የቁስል ፕላስተር እንደሚለጥፍ ሰው ሳይሆን ልክ በሰውነታችን ሁሉ መድኃኒቱ እንዲዳረስ እንደሚያደርግ ኬሞቴራፒ ህክምና ሁሉ የወንጌል እውነት እና የመንፈሱ ኃይል በመንፈሳዊ ደም ስሮቻችን ገብተው እንዲሞሉን እናደርጋለን። በሕይወት ለሚገጥሙ ችግሮች አቋራጭ እና ቀላል የሚሆኑ መፍትሄዎች በጣም ጥቂት ናቸው። ነገር ግን ኃያል ወደ ሆነው፣ ወደሚምረው፣ ፍቅር እና በቂ ወደሆነው በቀራኒዮ በልጁ ወደወደደን አባት መመልከት እንችላለን።

ነፃ የሚያወጣ ደካማ ጎንን መግለጽ ደካማ ጎናችንን፣ ስብራታችንን እና ኃጢያታችንን አያጋልጥም። ነገር ግን እግዚአብሔር ምን ያህል መልካም፣ በቂ፣ ቸር እና የማይለዋወጥ እንደሆነ ያጎላል። እርሱ እንደሚያስፈልገን እንድናውቅ የሚያደርገን ጸጋው ነው። በእርሱ ላይ እንድንደገፍ እና ከኃጢያት በመራቅ ፍቅሩን እንድናስብ የሚያደርገን ጸጋው ነው።  

የእግዚአብሔር ጸጋ በእኛ ላይ እንዲገለጥ ድካማችንን መቀበል እንችላለን። ይሄ ሁላችንም በየዕለቱ ልናስታውሰው የሚገባ ነገር ነው። እግዚአብሔር በቂ ነው። እግዚአብሔር መልካም ነው። እግዚአብሔር ይወዳችኋል። ኢየሱስ ክርስቶስ መቼም አይተዋችሁም፤ ደግሞም አይለቃችሁም። ምንም ያህል ደካሞች ወይንም ደካማ ጎናችን የተጋለጠብን ብንሆን ጸጋው ለእኛ በቂ ወደሆነው ኃይሉ በድካማችን ወደሚገለጠው ክርስቶስ መመልከት እንችላለን (2 ቆሮንቶስ 12፡9)።

 

Originally Posted at DesiringGod.org, Translated by Joshua Terefe


 

Last modified on %PM, %06 %799 %2017 %21:%May
Steven Lee

Steven Lee Steven Lee (@5tevenLee) is the pastor of small groups and community outreach at College Church in Wheaton, Illinois where he lives with his wife Stephanie and their four children. He is a graduate of Bethlehem College & Seminary.

https://twitter.com/5tevenLee

ከሮሜ 8:35 ውስጥ ልንማራቸው የምንችለው ሦስት ነገሮች

ከክርስቶስ ፍቅር ማን ይለየናል? መከራ፥ ወይስ ጭንቀት፥ ወይስ ስደት፥ ወይስ ራብ፥ ወይስ ራቁትነት፥ ወይስ ፍርሃት፥ ወይስ ሰይፍ ነውን? (ሮሜ 8፡35) ...

Jonathan Parnell - avatar Jonathan Parnell

ጨርሰው ያንብቡ

ፖርኖግራፊ ምንድን ነው?

ከፓርኖግራፊ ሱስ መውጣት ይቻላል! ክፍል አንድ - ፖርኖግራፊ ምንድን ነው?  በአንድ ወቅት ‘ጉግል’ አለም ላይ አብዝተው ወሲብ (Sex) የሚለውን ቃል ፈል...

Ermias Kiros - avatar Ermias Kiros

ጨርሰው ያንብቡ

 

The views and opinions expressed on Daily Injera are solely those of the original authors and our contributors. These views and opinions do not necessarily represent Daily Injera or our Staff.

Newsletter

Subscribe to our newsletter. Don’t miss any article, devotionals or wallpapers.

We do not spam!

You're automatically subscribed to bi-weekly articles and daily devotionals. You can customize your subscription settings here.