Tuesday, 22 October 2024

እየሻከረ እና እየቀዘቀዘ ያለው የሶሻል ሚድያ የክርስቲያኖች ሕብረት (የወቅቱ አሳዛኝ ጉዳይ!)

Posted On %PM, %24 %799 %2018 %21:%Apr Written by

‹‹እላችኋለሁም ብዙዎች ከምሥራቅና ከምዕራብ ይመጣሉ ከአብርሃምና ከይስሃቅ ከያዕቆብም ጋር በመንግስተ ሰማያት ይቀመጣሉ።›› ማቴ 8፡10-11

ብዙም አልቆየም… በአንድ አጋጣሚ ካገኘሁት ከአንድ ጋናዊ ኢ-አማኝ (ኤቲስት) ጋር ስለ ሃይማኖት ስንጫወት ‹‹የሃይማኖት ሰዎች ስለ ፍቅር ብዙ ያወራሉ። በተግባር ሲመጣ ግን ፍጹም እንደሚናገሩት አይደሉም። ከእነርሱ በሃሳብ ፣ በአመለካከት እና በአኗኗር ዘይቤ ከሚለዩት ጋር ሕብረት ማድረግ አይችሉም›› አለኝ። የዚህ ጋናዊ ምልከታ ሚዛኑን ያልጠበቀ ቢሆንም ይህ ምልከታ የሚገልጸን የሃይማኖት ሰዎችም አንጠፋም። ይህ እውነት ከሆነ ደግሞ እኛ ሃይማኖተኞች ከሌሎች ተሸለን አለመገኘታችን እጅግ ያሳፍራል!

ቆየት ካሉ ክርስቲያን የዩኒቨርሲቲ ወዳጆቼ መካከል ከሆኑ የሐይማኖት ተከታዮች ጋር ሕብረት ማድረግ ፣ መግባባት እና መተዋወቅ የማይወድ እና እጅግ የሚጠላ ወንድም ነበረ። እንዲሁ እኔም ብሆን ሌሎች ‹ክርስቲያን ነን› ብለን ራሳችንን የምንጠራ ሁላችን በዚህ ብንፈተሽ በአመለካከት እና በሃሳብ ከእኛ ከሚለዩት ጋር ሕብረት ፍላጎት ማድረግ ላይኖረን ይችላል።

ከዚህም በላይ በዚህ ጊዜ አሳሳቢው እና አንገብጋቢው ጉዳይ ግን እኛው ክርስቲያኖች እርስበርስ ያለን የመቀባበል ችግር ነው። አሁን አሁን የማህበራዊ ሚድያው የመሰዳደቢያ ፤ መንፈሳዊ ጽሁፎች ጥላቻን መግለጫ እንዲሁም የተለያዩ ምስሎች ደግሞ የመነቃቀፍያ እና የመጣያ መድረኮች ሆነዋል። ልብ በሉልኝ ይህ ሁሉ የሚሆነው ግን ‹ክርስቲያን ነን› ብለን ራሳችንን በሰየምን ሰዎች መካከል ነው። ከጊዜ ወደጊዜ ከእኛ በአመለካከት እና በአኗኗር ዘይቤ የሚለዩትን ክርስቲያኖችን እንኳ መቀበሉ እየከበደን መጥቷል። ይህ እጅግ ያሳዝናል!

በዚህ ጽሁፍ መጸሐፍ ቅዱስ በተለይ በክርስቲያኖች መካከል ሊኖር የሚገባን ሕብረት እንዴት እንደሚገልጸው ከክርስቶስ ንግግር በመነሳት እናያለን። በዚህም እግዚአብሔር ብዙ እንደሚያስተምረን እና ከእኛ በሀሳብ ፣ በአመለካከት ፣ በዘር ፣ በቋንቋ የሚለይን ክርስቲያን ለመቀበል ድፍረቱን እና መነሳሳቱን እንደምናገኝ እምነቴ ነው!

ከምስራቅ… ከምዕራብ

‹‹ኢየሱስም ሰምቶ ተደነቀና ለተከተሉት እንዲህ አለ። እውነት እላችኋለሁ በእስራኤል እንኳ እንዲህ ያለ ትልቅ እምነት አላገኘሁም። እላችኋለሁም ብዙዎች ከምሥራቅና ከምዕራብ ይመጣሉ ከአብርሃምና ከይስሃቅ ከያዕቆብም ጋር በመንግስተ ሰማያት ይቀመጣሉ።›› ማቴ 8፡10-11

ጌታ ኢየሱስ ይህንን የተነናገረው ሮማዊው የመቶ አለቃ ብላቴናውን እንዲፈውስለት በጠየቀው መሰረት ጌታ ኢየሱስ በመቶ አለቃው እምነት ተገርሞ ከፈወሰለት በኋላ ነበር። በዚህ ጌታ ኢየሱስ ለደቀመዛሙርቱ አንድ እውነታ ያስጨብጣቸዋል ‹‹ብዙዎች ከምስራቅ እና ከምዕራብ ይመጣሉ… በመንግስተ ሰማያት ይቀማጣሉ።›› 

ደግሞም በሌላ ስፍራ፡-

‹‹ከምሥራቅና ከምዕራብም ከሰሜንና ከደቡብም ይመጣሉ፤ በእግዚአብሔር መንግስት ማዕድም ይቀመጣሉ›› ሉቃ 13፡29

ተመሳሳይ በሆነው የሉቃስ ዘገባም ከተለያዩ ስፍራዎች ሰዎች በአንድነት በመንግሰተ ሰማይ ለማዕድ እንደሚቀመጡ እናያለን። መንግስተ ሰማይ ከምሥራቅ እና ከምዕራብ ጽንፍ በሚመጡ ክርስቲያኖች እንደምትሞላ ከቅዱስ ቃሉ እናነባለን። ይህንን የእግዚአብሔርን መንግስት ሰዎችን የመሸከም አቅም ለመረዳት በምስራቅ እና በምዕራብ ሰዎች መካከል ያለውን ልዩነት መረዳት አለብን። ለመሆኑ በምስራቅ እና በምዕራብ የሚኖሩ ክርስቲያኖች መካከል ያሉት ልዩነቶች ምን ምን ናቸው? እስቲ የአሁኑን ዘመን ነባራዊ እውነታን ብቻ በመውሰድ በእነዚህ ክርስቲያኖች መካከል ያሉትን ሶስት መሰረታዊ ልዩነቶች አብረን እንመልከት። እነዚህ ታዲያ ከአለም አቀፍ እስከ ሃገር ደረጃ እውነታዎች ናቸው።

1. የአከባቢ (ጂኦግራፊ) ልዩነት

በምሥራቅ እና በምዕራብ መካከል ያለው የመጀመሪያ ልዩነት የ ቦታ ልዩነት ነው። ‹ምሥራቅ› እና ‹ምዕራብ› የሚሉት ቃላቶች ከቦታ አንጻር የተቃኙ ናቸው። ስለዚህም ጌታ ኢየሱስ በንግግሩ መንግስተ ሰማይ የቦታ ስብጥር የሚታይባት እንደምትሆን እገለጸ ነው። የአንድ ክልል ፣ አንድ ስፍራ ፣ አንድ አከባቢ ወይም የአንድ ሃገር ሰዎች ብቻ አይደለችም።

አንዳንድ ጊዜ አንዳንድ ክርስቲያኖች ክርስትናን የእኛ ሃገር ብቻ ስናደርገው እንታያለን። ከዚህም መነሻ ከእኛ አካባቢ ያልሆነ ክርስቲያንን መቀበል ራሱ ይከብደናል። ይህንን በግልጽ ባናሳይ እንኳን እንደምንም እግዚአብሔርን የእኛ ብቻ ስናደርግ እንታያለን። ይህ ፍጹም ትክክል አይደለም! እውነታው ክርስትና የእስራኤላውያን (መካከለኛው ምስራቅ) ብቻ እንዳልሆነ ሁሉ የኢትዮጵያ ብቻ (አፍሪቃ) ብቻም አይደለም! ዛሬ ዛሬ ግን ምስራቃውያን ምዕራባውያንን መቀበል ሲከብዳቸው እናያለን።

ይህ ብቻም አይደለም የእኛ አካባቢ የተቀደሰ የሌላውን ደግሞ የረከሰ ለማድረግም እንጣጣራለን። ‹‹ቅድስት…›› ብለን ለአካባቢያችን መጠሪያ እንሰጣለን። ምሥራቁም ምዕራቡም በአብ ፊት አንድ እንደሆነ ዘንግተናል!

በእኛው ሃገር ውስጥ እራሱ የምስራቅ የሃገራችን ክፍል ክርስቲያኖች ከምዕራቡ የሃገራችን ክፍል ክርስቲያኖች ጋር ፣ የሰሜኖቹ ከደቡቡ ጋር ሲቃረኑ እና ሲለያዩ ይታያል። በፍቅር መቀባበል ያስፈልጋል! ቃሉን መከተል ያስፈልጋል!

ጌታ ኢየሱስ የተናገረው እኛ በማሕበራዊ ሚድያ እና በተለያዩ ስፍራዎች እያሳየነው ካለው ፍጹም ተቃራኒ ነው። ጌታ ኢየሱስ በተለያየ በአከባቢ የሚኖሩ ክርስቲያኖች መቀባበል ሲኖራቸው የመንግስቱን ስዕል ከላይ ባየነው ክፍል አሳይቶናል። እኛስ ከእኛ በአከባቢ የሚለይን ክርስቲያን እንቀበላለን ወይስ ክርስትናን የእኛ ሃገር እና ክልል ብቻ አድርገን እንወስዳለን?

2. የቆዳ ቀለም (የዘር) ልዩነት

ቀጣዩ በምሥራቅ እና በምዕራብ መካከል የምናገኘው ልዩነት ደግሞ የዘር ፣ የቀለም ልዩነት ነው። ይህ እጅግ አንገብጋቢ እና ሰሞነኛው ጉዳይ ነው። ዛሬ ዛሬ ሁለት የተለያየ የቆዳ ቀለም ያላቸው ክርስቲያኖች በማዕድ መቀመጥ አቅቷቸዋል። ይህ እንደቀደሙት ዘመናት ከነጩ ወደ ጥቁሩ ላይ የሚደረግ ተጽዕኖ ብቻ አይደለም። ከሁለቱም ወገን ክርስቲያኖች ጽንፍ ይዘው ቤተ ክርስቲያን የለዩበት ጊዜ ነው። ‹‹የጥቁሮች›› የሚባል አብያተክርስቲያናት እንዳሉ የምናውቅ ስንቶቻችን እንሆን?

ከዚህ በላይ እጅግ አሳሳቢ የሆነው ሌላው ጉዳይ ግን በእኛው ሃገር በዘር በሚለያዩ ክርስቲኖች መካከል እየታየ ያለው መቀባበል ችግር ነው። እጅግ በሚያሳዝን መልኩ ብዙዎች ከእነርሱ ቋንቋ ውጭ የሚናገርን ሌላ ኢትዮጵያዊ ክርስቲያንን እንኳን መቀበል ከብዷቸው ከዚያ ይልቅ ክርስትናን የራሳቸው ዘር ብቻ አድረገውት ስመለከት ልብ ይሰብራል። ጌታ ኢየሱስ የነገረን ግን ሰዎች ‹‹ከምሥራቅና ከምዕራብም ከሰሜንና ከደቡብም›› እንደሚመጡ ነው።

በምስራቅ እና በምዕራብ ክርስቲያኖች መካከል የዘር እና የቆዳ ልዩነት መኖሩን አንክድም። አንዳንዶች ጥቁር ናቸው። አንዳንዶች ነጮች ናቸው። ሌሎች ቡናማ ናቸው። ሁሉም ግን የእግዚአብሔር ልጆች ናቸው። ሁሉም ግን አንድ ቀን ከአብርሃም ፣ ከይስሃቅና ከያዕቆብ ጋር በመንግስተሰማይ በማዕድ ይቀመጣሉ!

እኛስ ከእኛ የተለየ ቋንቋ የሚናገረውን ፣ በቆዳ ቀለም ከእኛ የሚለየውን ደግሞም በዘር በቅርብ የማይዛመደንን ክርስቲያን በክርስቶስ እንደተወደደ ወንድም እንቆጥራለን ወይስ ጎራ ለይተን ሌላኛው ወንድማች ላይ አድማ እናስነሳለን? እግዚአብሔር ማስተዋሉን ይስጠን!

3. የአመለካከት ልዩነት

በምሥራቅ እና በምዕራብ ሰዎች መካከል ካሉት ልዩነቶች ሌላኛው ደግሞ የአመለካከት ልዩነት ነው። ታሪክ እንደሚያሳየው ምዕራባውያን (አውሮጳ እና አሜሪካ) አብዛኛውን ጊዜ ለአመክንዮ (logic) እና እውቀት ወይም ሳይነስ ከፍተኛ ስፍራን ይሰጣሉ። ምስራቃውያን (አፍሪካ ፣ መካከለኛው መስራቅ እና ኢስያ) ደግሞ አብዛኛውን ጊዜ ለማይታየው አለም (መንፈሳዊው አለም) እና ለልምምድ (experience) ከፍተኛ ስፍራን ይሰጣሉ። ምዕራባውያን እውቀት ላይ ሲያተኩሩ ምስራቃውያን በአብዛኛው ጊዜ ስሜት ላይ እናተኩራለን። ይህ ጽንፍ ገሃድ የወጣ እና አሁንም ድረስ የቀጠለ ነው።

ይህ ልዩነት በክርስትናውም ላይ ጥላ አጥልቷል። አብዛኛው የምዕራባውያን ክርስቲያኖች በዕውቀት ላይ የተመሰረቱ ናቸው። እኛ ምስራቃውያን ደግሞ ‹መንፈሳውያን› ነን። እነርሱ (ምዕራባውያን ክርስቲያኖች) አንድን ክስተት በአመከንዮ ሲያብራሩ እኛ ደግሞ ተአምራትንና እና ልዕለ ተፈጥሮ የሆነ ሃይልን መሰረት አድረገን ልናብራራ እንሞክራለን። ይህ በምስራቅ እና በምዕራብ ክርስቲያኖች መካከል ያለው ልዩነት በግርድፉ ነው።

ይህ ልዩነት ከጊዜ ወደጊዜ ግን ወደ ሃገራችንም ዘልቋል። በሃገራችን ክርስቲያኖች መካከልም ተመሳሳይ የአመለካከት ልዩነቶች አሉ። በእኛው ሃገር ክርስቲያኖች መካከል የምሥራቅ እና የምዕራብ ጽንፍ ይታያል። ከዚህም የተነሳ በቅርብ ጊዜያት ውግዘት በዝቷል።

አንዱ ጽንፍ አንዱን ጽንፍ ሲያወግዝ ደግሞም ሲኮንን ብሎም በአደባባይ ወንድማማችነቱን ሲክድ እየሰማን ነው። አብዛኛው የማህበራዊ ሚድያ ክርክር እና ጸብ የሚደረገው በአመለካከት በተለያዩ ክርስቲያኖች መካከል ሆኖአል። ይህ እጅግ ያሳዝናል።

እኔ ምሥራቅ እና ምዕራብን የማስታረቅ አቅሙም እውቀቱም የለኝም! መጸሐፍ ቅዱስ ሁሉም ሰው አንድ አመለካከት ይኑረው አይለንም። ነገር ግን እርስበርሳችን በፍቅር እንድንቀባበል ያዘናል። አሁን እያጣን ያለው በፍቅር መቀባበልን ነው።

አንድን ክርስቲያን በፍቅር ለመቀበል የግድ ከእኛ የዘር ሃረግ ወይም ከእኛ አከባቢ የመጣ መሆን የለበትም። አንድ ክርስቲያንን እንደወንድም ለመቀበል የግድ የእኔን አስተሳሰብ ማራመድ አይጠበቅበትም። የአመለካከት ልዩነቶች ይጠበቃሉ። ነገር ግን የክርስቶስ ፍቅር ይህንንም ያልፋል!

ስንቶቻችን በአመለካከት ከእኛ ከሚለየው ክርስቲያን ጋር ሕብረት እናደርጋለን? ስንቶች ከአጥር ወጥተን ወንድምን ከመተቸት እና ከማሸማቀቅ አልፈን ማዕድን መቁረስ ችለናል? ስንቶቻችን ወንድምን ‹ስሁት› እና ‹መናፍቅ› ከማለት አልፈን ስለእርሱ ጸልየን እናውቃለን?

ምስራቅ እና ምዕራብ በፍቅር መቀባበል ይችላሉ!

ዛሬም አመለካከትን ለመቀየር ጊዜው አልረፈደም! መግቢያዬ ላይ የጠቀስሁላችሁ የዩኒቨርሲቲ ወዳጄም አስተሳሰቡን ቀይሮ ከራሱ አጥር ውጭ ያሉትን ሰዎች ለመቀበል አቅም አግኝቷል። እኛም ወንድማችንን መቀበል ችግር እንዳለብን ካወቅን ዛሬ ቃሉ እንደሚለው ለመኖር በመወሰን ነጻ መውጣት አንችላለን። ከእኛ የሚለዩትን በፍቅር መቀበል እንችላለን!

ከዚህ በፊት በማሕበራዊ ሚድያ በጸብ አጫሪ ፣ በትችት በተሞሉ እና ስድብን በጠገቡ ንግግሮቻችን የምንታወቅ ከሆነ ዛሬ በመባረክ ፣ በመውደድ ፣ ሌላው ውስጥ ያለውን መልካም ነገር ፈልጎ በማድነቅ ከምንም በላይ ደግሞ በክርስቶስ በሆነ ሕብረት መታወቅ አንችላለን!

በመጨረሻም አንድ ማዕድ ፣ አንድ ጠረጴዛ ፣ አንድ ሕብረት ፣ አንድ ጌታ እንዳለን አንዘንጋ! በክርስቶስ ኢየሱስ አምኖ የዳነ ሁሉ ወደ ልጁ ሕብረት ተጠርቷል። ምስራቅ እና ምዕራብ ምንም እንኳ የማይገናኙ ሁለት ጽንፍ ቢሆኑም ክርስቶስ በመሃል ሲገባ አንድ ይሆናሉ። በክርስቲያች ሕብረት ክርስቶስ ሁልጊዜም አለ። ክርስቶስ ደግሞ አንድ ነው ፤ አልተከፈለም! (1ኛ ቆሮ 1፡13)

በክርስቶስ አንድነት ከእኛ የሚለዩትን ለፍቅር ሕብረት እንጋብዝ! ከአብርሃም ከይስሃቅ ከያዕቆብ ጋር በማዕዱ ፣ በመንግስቱ ያገናኘን! አሜን!

Last modified on %PM, %25 %585 %2018 %16:%Apr
Naol Befkadu

Naol Befkadu Kebede (BTh, student of MA in Ministry and Medical Doctorate student at AAU) is the founder and contributor of Lechristian Blog, an online ministry that aims to redeem cultures for the glory of God and to inspire and encourage believers for the completion Great Commission. Naol has authored an Amharic book titled "ተነሺ ፤ አብሪ" (2015) that motivates young believers for a meaningful and radical life. 

lechristian.blogspot.com

የተስፋ ክምሮች

አጥብቃችሁ በፈለጋችሁት ጊዜ ልታገኙት የምትችሉት የተስፋ መጠን እጅግ ድንቅ ነው። ተስፋ ደግሞ በሕይወታችን እጅግ አስፈላጊ የሆነ ኃይል ነው። ከእግዚአብሔር የ...

John Piper - avatar John Piper

ጨርሰው ያንብቡ

እኛም ደግሞ የበደሉንን ይቅር እንደምንል በደላችንን ይቅር በለን

ማቴዎስ 6፡14-15 “ለሰዎች ኃጢአታቸውን ይቅር ብትሉ፥ የሰማዩ አባታችሁ እናንተን ደግሞ ይቅር ይላችኋልና፤ ለሰዎች ግን ኃጢአታቸውን ይቅር ባትሉ፥ አባታችሁም...

John Piper - avatar John Piper

ጨርሰው ያንብቡ

 

The views and opinions expressed on Daily Injera are solely those of the original authors and our contributors. These views and opinions do not necessarily represent Daily Injera or our Staff.

Newsletter

Subscribe to our newsletter. Don’t miss any article, devotionals or wallpapers.

We do not spam!

You're automatically subscribed to bi-weekly articles and daily devotionals. You can customize your subscription settings here.