Monday, 15 July 2024

የተሰራችሁት ወደ እግዚአብሔር ለሚያዘነብል ሕይወት ነው

Posted On %AM, %11 %041 %2016 %03:%Oct Written by

እግዚአብሔራዊ ሕይወት ወደ እግዚአብሔር በማዘንበል የሚኖር ነው። ፊታችንን ከእርሱ ሳይሆን ወደእርሱ ነው የምናዞረው። መገኘቱን ማስተዋላችንን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየወደድነው እንሄዳለን። እናስታውሰዋለን፤ አንረሳውም። በቀኑ መጨረሻ ላይ ተስፋችንን በእርሱ ላይ እንጥላለን። ከሞት እንደሚያድነን ብቻ ሳይሆን በሚቀጥለው ሰዓት እንኳን በእርግጥ እንደሚረዳን በእርሱ እንታመናለን።

በሀሳባችን ሁሉ ታላቅ የሆነውን ዋጋውን እናስባለን። በግንኙነቶቻችን እና መስተጋብሮቻችን መሀል የተናገራቸው ነገሮች ትዝ ይሉናል። ተስፋዎቹ እና ማስጠንቀቂያዎቹ በአዕምሮአችን ውስጥ የሚሰሙን ድምጾች ናቸው። ልጁ በምድር ላይ የሄደበት መንገድ በምናባችን ደጋግሞ የሚጫወተው ምስል ነው። በምናባችን መድረክ ላይ የሚራመዱትና ልናደንቃቸው የምንወድ ጀግኖቻችን ደግሞ እርሱን የመሰሉትን ነው። 

በዞርንበት ሁሉ የእግዚአብሔርን የጥበብ ሥራ እናያለን። የመለኮት ጥላዎች ቁም ነገር እና ደስታን ባዘሉ ትምህርቶች ይንሳፈፋሉ። የምድርን ክስተቶች እያየን የእርሱን አቅርቦት እናስተውላለን። እያንዳንዱ እቃ ፣ እያንዳንዱ ሰው ፣ እያንዳንዱ ሀሳብ ፣ እያንዳንዱ አማራጭ ከእግዚአብሔር ጋር ከሚኖረው ግንኙነት አንፃር ነው የሚታየው።

በእምነት ብቻ በሆነው ጽድቅ ላይ ቆመን እግዚአብሔርን በነገር ሁሉ ለማስደሰት እናልማለን። ስሜታችንን ከስሜቱ ጋር ፣ ሀሳባችንን ከ ሃሳቡ ጋር ፣ ቃሎቻችንን ከቃሉ ጋር እና ሥራችንን ከሥራው ጋር ለማስማማት አላማችን ነው። ለእርሱ ለሚኖሩት ሊሰጣቸው ያለውን ሽልማት ለማብዛት እናልማለን። ከእርሱ ጋር ያለንን የሕብረት ደስታ ያለምንም ሀፍረት አሁንም ሆነ ለዘላለም እንፈልገዋለን። እርሱ ታላቅ ሸልማታችን ነው።

ለእግዚአብሔር የምንከፋፍለው ጊዜ የለንም። እሁድ ጠዋት ለእግዚአብሔር ንቃተ ህሊና እንደነበረን ሰኞ ማታም እንዲሁ ነው። ሥራችን ቢሆን የእረፍት ጊዜያችን አልያም መዝናናት እና ማሕበራዊ ድህረ ገጽ አጠቃቀማችን በሚያንፀው የእግዚአብሔር ህልውና የሚኖሩ ናቸው፡፡እግዚአብሔር የሌለበት ባዶ ቦታ በሕይወታችን ውስጥ የለንም። እያንዳንዱ ጊዜ እና ድርጊት ከእግዚአብሔር የሆነ በእግዚአብሔር የሆነ ለእግዚአብሔር የሆነ ነው። ይሄ ነው ወደ እግዚአብሔር ያዘነበለ ሕይወት።

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እግዚአብሔር ወደእዚህ ሕይወት ጠርቶናል። የሕይወታችን ሙሉው በእግዚአብሔር የተሞላ እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሁሉም ስፍራ ይነግረናል። በሕይወታችን ውስጥ እግዚአብሔር የተወሰነውን ክፍል ብቻ የሚይዝበት እና የሙሉ ሕይወታችን ድምቀት እና መዓዛ አለመሆኑን መጽሐፍ ቅዱስ ሞኝነት ይለዋል። ልባችሁን እና ጆሯችሁን ወደ ወደ እግዚአብሔር ያዘነበለ ሕይወት ጥሪ አዘንብሉ።

 • ወደ እግዚአብሔር ያዘነበለ ሕይወት ሁሉንም ስለ እግዚአብሔር ክብር ማድረግ ነው።
እንግዲህ የምትበሉ ወይም የምትጠጡ ብትሆኑ ወይም ማናቸውን ነገር ብታደርጉ ሁሉን ለእግዚአብሔር ክብር አድርጉት። (1 ቆሮንቶስ 10፡31)
 • ወደ እግዚአብሔር ያዘነበለ ሕይወት ሁሉንም የምናደርገውን ነገር ሁሉ በኢየሱስ ስም ማድረግ ነው።
“በቃል ቢሆን ወይም በሥራ የምታደርጉትን ሁሉ በጌታ በኢየሱስ ስም አድርጉት” (ቆላስይስ 3፡17)።
 • ወደ እግዚአብሔር ያዘነበለ ሕይወት እግዚአብሔርን ስለ ሁሉ ማመስገን ነው።

“ሁልጊዜ ስለ ሁሉ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አምላካችንንና አባታችንን ስለ ሁሉ አመስግኑ” (ኤፌሶን 5፡20)።

 • ወደ እግዚአብሔር ያዘነበለ ሕይወት ሁል ጊዜ በእግዚአብሔር ፊት መሄድ ነው።

“ነፍሴን ከሞት፥ እግሮቼን ከመውደቅ አድነሃልና፥ በሕያዋን ብርሃን እግዚአብሔርን ደስ አሰኘው ዘንድ” (መዝሙር 56፡13)።

 • ወደ እግዚአብሔር ያዘነበለ ሕይወት በእግዚአብሔር ፊት ሐሤት ማድረግ ነው።

“ጻድቃንም ደስ ይበላቸው፥ በእግዚአብሔርም ፊት ሐሤት ያድርጉ፥ በደስታም ደስ ይበላቸው” (መዝሙር 68፡3)።

 • ወደ እግዚአብሔር ያዘነበለ ሕይወት  በእግዚአብሔር ፊት አገልግሎትን ማድረግ ነው።

“ይህን አሳስባቸው፥ በቃልም እንዳይጣሉ በእግዚአብሔር ፊት ምከራቸው፥ ይህ ምንም የማይረባ የሚሰሙትንም የሚያፈርስ ነውና” (2 ጢሞቴዎስ 2፡14)።

 • ወደ እግዚአብሔር ያዘነበለ ሕይወት በእግዚአብሔር ዘንድ በድፍረት መሆን ነው

“ወዳጆች ሆይ፥ ልባችንስ ባይፈርድብን በእግዚአብሔር ዘንድ ድፍረት አለን” (1 ዮሐንስ 3፡21)

 • ወደ እግዚአብሔር ያዘነበለ ሕይወት እግዚአብሔር እንዲታደገን ዓይኖቻችንን ወደ እግዚአብሔር ማቅናት ነው። 

“እርሱ እግሮቼን ከወጥመድ ያወጣቸዋልና ዓይኖቼ ሁልጊዜ ወደ እግዚአብሔር ናቸው” (መዝሙር 25፡15)

“አቤቱ ጌታ፥ ዓይኖቼ ወደ አንተ ናቸውና በአንተ ታመንሁ፥ ነፍሴን አታውጣት” (መዝሙር 141፡8) 

 • ወደ እግዚአብሔር ያዘነበለ ሕይወት እግዚአብሔር አይቶ ዋጋን እንደሚሰጥ በማስተዋል መስጠት ፣ መጸለይ እና መጾም ነው።

“አንተ ግን ምጽዋት ስታደርግ ምጽዋትህ በስውር እንዲሆን ቀኝህ የምትሠራውን ግራህ አትወቅ፤ በስውር የሚያይ አባትህም በግልጥ ይከፍልሃል” (ማቴዎስ 6፡3-4)

“አንተ ግን ስትጸልይ፥ ወደ እልፍኝህ ግባ መዝጊያህንም ዘግተህ በስውር ላለው አባትህ ጸልይ፤ በስውር የሚያይ አባትህም በግልጥ ይከፍልሃል” (ማቴዎስ 6፡6)

አንተ ግን ስትጦም፥ በስውር ላለው አባትህ እንጂ እንደ ጦመኛ ለሰዎች እንዳትታይ ራስህን ተቀባ ፊትህንም ታጠብ፤ በስውር የሚያይ አባትህም በግልጥ ይከፍልሃል" (ማቴዎስ 6፡17-18)

 • ወደ እግዚአብሔር ያዘነበለ ሕይወት የእግዚአብሔርን ጊዜውን የጠበቀ እርዳታ መጠባበቅ ነው።

“እንግዲህ ምሕረትን እንድንቀበል በሚያስፈልገንም ጊዜ የሚረዳንን ጸጋ እንድናገኝ ወደ ጸጋው ዙፋን በእምነት እንቅረብ” (ዕብራውያን 4፡16)

“እግዚአብሔር ልቡ በእርሱ ዘንድ ፍጹም የሆነውን ያጸና ዘንድ ዓይኖቹ በምድር ሁሉ” (2 ቆሮንቶስ 16፡9)

“ሰዎች ከጥንት ጀምሮ ለሚጠብቁህ ከምትሠራላቸው ከአንተ በቀር ሌላ አምላክን አልሰሙም በጆሮአቸውም አልተቀበሉም ዓይንም አላየችም (ኢሳያስ 64፡4)

“. . . እግዚአብሔር በቅንነት የሚሄዱትን ከመልካም ነገር አያሳጣቸውም” (መዝሙር 84፡11)

 • ወደ እግዚአብሔር ያዘነበለ ሕይወት ጥሪአችንን ከእግዚአብሔር ጋር ማድረግ ነው

ወንድሞች ሆይ፥ እያንዳንዱ በተጠራበት እንደዚሁ ሆኖ በእግዚአብሔር ዘንድ ይኑር” (1 ቆሮንቶስ 7፡24)

 • ወደ እግዚአብሔር ያዘነበለ ሕይወት አለቃችን እግዚአብሔር እንደሆነ ሆኖ መሥራት ነው

ለሰው ሳይሆን ለጌታ እንደምታደርጉ፥ የምታደርጉትን ሁሉ በትጋት አድርጉት። ከጌታ የርስትን ብድራት እንድትቀበሉ ታውቃላችሁናየምታገለግሉት ጌታ ክርስቶስ ነውና (ቆላስይስ 3፡23-24)

 • ወደ እግዚአብሔር ያዘነበለ ሕይወት በሁሉ ነገር ኢየሱስን ለማስደሰት ያለመ ነው፡፡

“ስለዚህ ደግሞ ብናድር ወይም ተለይተን ብንሆን እርሱን ደስ የምናሰኝ ልንሆን እንቀናለን” (2 ቆሮንቶስ 5፡9)።

“ለጌታ ደስ የሚያሰኘውን መርምሩ” (ኤፌሶን 5፡10)

 • ወደ እግዚአብሔር ያዘነበለ ሕይወት ለኢየሱስ እንደሚገባ ሆኖ መኖርን ዘወትር መሻት ነው

“በበጎ ሥራ ሁሉ ፍሬ እያፈራችሁ በእግዚአብሔርም እውቀት እያደጋችሁ ከደስታም ጋር በሁሉ ለመጽናትና ለመታገሥ እንደ ክብሩ ጉልበት መጠን በኃይል ሁሉ እየበረታችሁ፥ በቅዱሳንም ርስት በብርሃን እንድንካፈል ያበቃንን አብን እያመሰገናችሁ፥ በነገር ሁሉ ደስ ልታሰኙ ጌታ እንደሚገባ ትመላለሱ ዘንድ እንለምናለን” (ቆላስይስ 1፡10-12)

 • ወደ እግዚአብሔር ያዘነበለ ሕይወት ቀሪ ሕይወትን ለእግዚአብሔር አላማ እንደ እንደተሠራ ማመን ነው።

ከእንግዲህ ወዲህ በሥጋ ልትኖሩ በቀረላችሁ ዘመን እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ እንጂ እንደ ሰው ምኞት አትኑሩ (1 ጴጥሮስ 4፡2)

 • ወደ እግዚአብሔር ያዘነበለ ሕይወት ለእግዚአብሔር ይኖራል

“እኔ ለእግዚአብሔር ሕያው ሆኜ እኖር ዘንድ በሕግ በኩል ለሕግ ሞቼ ነበርና” (ገላትያ 2፡19)

“ከእኛ አንድ ስንኳ ለራሱ የሚኖር የለምና፥ ለራሱም የሚሞት የለም፤ በሕይወት ሆነን ብንኖር ለጌታ እንኖራለንና፥ ብንሞትም ለጌታ እንሞታለን። እንግዲህ በሕይወት ሆነን ብንኖር ወይም ብንሞት የጌታ ነን” (ሮሜ 14፡7-8)

 • ወደ እግዚአብሔር ያዘነበለ ሕይወት እግዚአብሔርን ሳያቋርጥ ያናግራል

“ሳታቋርጡ ጸልዩ” (1 ተሰሎንቄ 5፡17)

 • በሞት ምክንያት ሊያበቃ አይችልም

“ምሕረትህ ከሕይወት ይሻላልና ከንፈሮቼ ያመሰግኑሃል” (መዝሙር 63፡3)

ጥሪ

ወደ እዚህ ወደ እግዚአብሔር ያዘነበለ ሕይወት እጋብዛችኋለሁ። እግዚአብሔር የሕይወታችን ጥግ ላይ ተቀምጦ እንደ ክርስቲያን ለመኖር መጣራችን አሳዛኝ ነው። በትንሸዬ ውሃ ውስጥ ሊኖር እንደሚሞክር አሳ ወይንም መብረር ሲገባት እየተራመደች ለመደሰት እንደምትሞክር ወፍ እናንተም እግዚአብሔርን ዳር ላይ አድርጋችሁ እናንተ መሀል ለመሆን አልተፈጠራችሁም። የተፈጠራችሁት እግዚአብሔርን የሁሉ ነገር መሀል ለማድረግ ነው። ወደ እዚህ ወደ እግዚአብሔር ያዘነበለ ሕይወት ሙሉ በሙሉ እንድትመጡ እጋብዛችኋለሁ። ነፃነት ያለው እዚህ ብቻ ነው።

 

Originally Posted at DesiringGod.org, Translated by Joshua Terefe


 

Last modified on %PM, %10 %821 %2016 %21:%Dec
John Piper

John Piper is founder and teacher of desiringGod.org and chancellor of Bethlehem College & Seminary. For 33 years, he served as pastor of Bethlehem Baptist Church, Minneapolis, Minnesota. He is author of more than 50 books, including A Peculiar Glory.

twitter.com/JohnPiper

ፀሀይ ግባት እና ወጀብ

“እግዚአብሔር ለክብሩ የተከላቸው የጽድቅ ዛፎች እንዲባሉ ለጽዮን አልቃሾች አደርግላቸው ዘንድ፥ በአመድ ፋንታ አክሊልን፥ በልቅሶም ፋንታ የደስታን ዘይት፥ በኀዘ...

Michelle Zombos - avatar Michelle Zombos

ጨርሰው ያንብቡ

አሮጌው እኔ አዲስ ሲሆን

አቤቱ፥ ንጹሕ ልብን ፍጠርልኝ፥ የቀናውንም መንፈስ በውስጤ አድስ። ከፊትህ አትጣለኝ፥ ቅዱስ መንፈስህንም ከእኔ ላይ አትውሰድብኝ። የማዳንህን ደስታ ስጠኝ፥ በእ...

Marshall Segal - avatar Marshall Segal

ጨርሰው ያንብቡ

 

The views and opinions expressed on Daily Injera are solely those of the original authors and our contributors. These views and opinions do not necessarily represent Daily Injera or our Staff.

Newsletter

Subscribe to our newsletter. Don’t miss any article, devotionals or wallpapers.

We do not spam!

You're automatically subscribed to bi-weekly articles and daily devotionals. You can customize your subscription settings here.