Tuesday, 19 March 2024

የክርስቶስ ጠባሳዎች

Posted On %AM, %08 %916 %2018 %00:%Apr Written by
“እጆቼን እና እግሮቼን ተመልከቱ፡እኔው ራሴ ነኝ ደግሞም ንኩኝ እና እዩ ይህንንም ብሎ እጆቹን እና እግሮቹን አሳያቸው” ሉቃ 24፡39

በዚህ የፋሲካ ወቅት አንድ ጥያቄ በአዕምሮዬ ይመላለሳል። ይህም ክርስቶስ በእጆቹ በእግሮቹ እና በጎኑም ያሉትን የዳኑ የቁስል ምልክቶች፣ ከሙታን ከተነሳ በኋላ በአካሉ ላይ እንዲኖሩ ለምን እንደመረጠ ነው። ከሙታን የተነሳው ይህ አዲስ ሰውነት በአምላክነት ክብሩ በዙፋኑም ላይ ይህን የአንድ ቀን ትዝታን ያዘለ ጠባሳ ሁሌ አብሮት እንዲኖር ለምንስ መረጠ?

ብዙዎቻችን በሰውነታችን ላይ ቢያንስ አንድ ጠባሳ አለን፤ ምናልባት በልጅነታችን የወደቅንበት፤ ከሰው ተጣልተን የተፈነከትንበ ወይም የቀዶ ጥገና ህክምና ያደረግንበት ሊሆን ይችላል።አብዛኛው እነዚህ ጠባሳዎች አካላችን ያለፈበት የህመም ጊዜ ትውስታዎች የመዳናችንም ምልክቶች ናቸው አልፎ አልፎ ደግሞ መልካም ሰዎች አሉ፤ ከራሳቸው ህመም አልፈው የሌላውን ሊሽከሙ የአካል ክፍላቸውን በመለገስ ጠባሳን በአካላቸው ላይ ያኖራሉ። 

ክርስቶስ የእኛን ህመም ለመሽከም ሙሉ አካሉን ሰጠ። እኛን ለመዋጀት ሞትን የህይወቱ አላማ አድርጎ ወደ ምድር ወረደ፤ የቀጠረለትም ቀን ሲደርስ ጀርባውን ለግርፋት እጅ እና እግሩን በሚስማር ለመቸንከር፣ ለመስቀልም ግርፋት አሳልፎ ሰጠ። 

“በእርግጥ እርሱ ደዌያችንን ወሰደ፤ ህመማችንንም ተሽከመ ስለ መተላለፋችንም ተዋጋ፣ ስለበደላችንም ደቀቀ” ኢሳ 3፡ 4-5

ታዲያ ክርስቶስ አምላክ ሆኖ ሳለ፣ አዲስም ሰውነት ለብሶ ሞትን ድል ሲነሳ ለምንስ በእጆቹ እና በእግሮቹ በጎኑም ያሉ ጠባሳዎች አብረውት እንዲቀሩ ወደደ? ይህ እኮ አምላክ በቀላሉ ሊያጠፋው የሚችለው ነገር አይደለምን? የመከራው የስቃዩንም ትዝታ ለብሶ ሊኖር ለምንስ አስፈለገው?

1. የክርስቶስ ጠባሳዎችለደቀ መዛሙርቱ ከሞት የመነሳቱ ማረጋገጫ ናቸው

“በዚያኑ እለት በሳምንቱ መጀመሪያ ቀን በምሽት ደቀ መዛሙርቱ አይሁድን በመፍራት በሮችን ቆልፈው ተሰብስበው ሳለ ኢየሱስ መጣና በመካከላቸው ቆሞ ‘ሰላም ለእናንተ ይሁን’ አላቸው። ይህን ብሎ እጆቹን ጎኑን አሳያቸው።’  ዮሐ 20፡19-20

ኢየሱስ ከሰላምታ ባለፈ የእጆቹን እና የጎኑን ጠባሳ ለሐዋሪያቱ አንክሮት ሰጥቶ እንዳሳያቸው ይህ ክፍል ያሳየናል።

ኢየሱስ ለሐዋሪያቱ በተገለጠ ጊዜ ሐዋሪያው ቶማስ አብሮዋቸው አልነበረም። ሌሎቹም ደቀ መዛሙርት ‘ጌታን አየነው እኮ!’ ሲሉት ቶማስ ይህ እንዴት ይሆናል ብሎም ተጠራጥሮ ነበር።

“በምስማር የተቸነከሩ የእጆቹን ምልክቶች ካላየሁ፤ምስማሮቹ በነበሩበት ቦታ ጣቴን ካላደረሁ፤ በጎኑም እጄን ካላስገባሁ አላምንም አለ።ከሳምንት በሃላ ደቀ መዛሙርቱ በቤት ውስጥ ሆነው ሳለ ቶማስም ከእነርሱ ጋር ነበር በሮቹም ተቆልፈው ነበር ኢየሱስ መጥቶ በመካከላቸው ቆመና ‘ሰላም ለእናንተ ይሁን’ አላቸው። ከዚያም ቶማስን “ጣትህን ወደዚህ አምጣ፤ እጆቼን ተመልከት፤እጅህን ዘርጋ እና በጎኔ አስገባ፤ አትጠራጠር፤እመን አለው። ቶማስም ጌታዬ አምላኬ አለው!’  ዮሐ 20፤21-29

ክርስቶስ ለተጠራጣሪው ቶማስ ጠባሳዎቹን በማሳየት መቶም እንዲነካው በመጋበዝ ከሙታን መነሳቱን አይቶ እንዲያምን አገዘው። በዚህ ክፍል ላይ ቶማስ ክርስቶስ ያለውን ነገር እንዳደረገ ባይነግረንም ‘ጌታዬ አምላኬ’ ብሎ ክርስቶስን እንዳመለከ እናያለን።

2. አምላክ ሰው ለመሆኑ ምስክር ናቸው

ክርስቶስ አዲስ አካልን ለብሶ ሞትን ድል ነስቶ ሲነሳ አንዲት ጠባሳ የሌለበት አካል ቢይዝ በእርግጥ ለእኛም አይምሮ ለመረዳት የበለጠ የተመቸ ይሆን ነበር።በአንፃሩ ደግሞ ሞትን ድል ለመንሳቱ የሰው ልጅን ሃጢአት እና ህመም ለመሽከሙ የህማማቱ ትኩስ ቁስል የእሁድ የፋሲካ ጠባሳ መሆኑ ለተከፈለልንን ትልቅ ዋጋ ምስክር ነው።

የክርስቶስ ጠባሳዎች አምላክ ስጋወደሙን መልበሱን፣ በስቅላት ለመሞቱ እና ሞትን ድል የመንሳቱ ምልክት ናቸው። አምላክም በምድር ላይ ለነበረው ግዜ ለሰውም የከፈለው ዋጋ የዘላለም ማስታወሻ የትንሳሄውም ማረጋገጫ ናቸው።

3.  የክርስቶስ ቁስል የእኛ ደስታችን ነው

“ደቀ መዛሙርቱም ጌታን ባዩት ግዜ እጅግ ደስ አላቸው።”   ዮሐ 20፤19  

ዮሐንስ ሐዋሪያቱ የክርስቶስ እጆች እና ጎኑን ሲያዩት ደሰ እንዳላቸው ይነግረናል። ቁስሎቹም የደስታ ምንጭ ሆነውላቸዋል። ይህ የሚከብድ አባባል ቢሆንም እነዚህ ጠባሳዎች ትላንት ክርስቶስ ለነበረው ሕመም እና ስቃይ ሐዋሪያቱም ለተሰማቸው ሀዘን ባዶነት እና ተስፋ መቁረጥ ልዩ ማስታወሻ ናቸው። የጌታችንን ሐዘን በማሰብ መልሰው ሀዘን አይቀመጡም፤ደረታቸውንም አይደቁም ምክንያቱም እርሱ ጌታቸው አሁን በፊታቸው ሁሉን ድል ነስቶ ቆሟል። ሐዘናቸውንም በደስታ ቀይርዋል። 

እኛም ዛሬ ላይ ሆነን ክርስቶስ በመስቀል ላይ ለሃጢያታችን የከፈለውን ዋጋ ስናስብ በሙሉዕ አክብሮት በሙሉዕ ስግደትና አምልኮ አምላካችን ፊት በመቅረብ ነው። የሃጥያታችንን ቅጣት ሁሉ በመስቀሉ ላይ ተከፍሏልና ከአምልኮ እና ምስጋና ባሻገር ልንጨምር የምንችለው ወይም ለሃጢያታችን ብለን የምንከፍለው ቅጣት የለም።

4. በአምላክ የእጅ መዳፍ ተቀርፀናል

“እናት የምታጠባውን ልጆን ልትረሳ ትችላለችን? ለወለደችውስ ልጅ አትራራለትምን? ምናልባት እርሳ ትረሳ ይሆናል እኔ ግን አልረሳሽም።እነሆ በእጄ መዳፍ ቀርጬሻለሁ።” ኢሳ 49:15-16

ልጅ እያለሁ ይህን ክፍል ሳነብ እግዚአብሔር በእጁ መዳፍ ላይ በማይለቅ ብዕር ስሜን እንደፃፈው አስብ ነበር። ኋላ ግን በእጄ መዳፍ ቀርጬሻለሁ ሲል ስሜን ከማስታወስ እጅግ ያለፈ ነገር እንደሆነ ተረድቻለሁ።ኢየሱስ በእጁ መዳፍ ላይ ስለእኔ ሃጢአት የከፈለውን ዋጋ ያዘሉ ቅርፆች ናቸው ለካስ ያሉት? እኔ በዚች ምድር ባላኝ ህይወት ስዝል ስደክም እና ስወድቅ የሚያነሱኝ እጆቹ ለእኔ የሚገባውን ቅጣት የከፈለበትን ደረስኝ የያዙ ናቸው።በአብም ዘንድ ስለእኔ ሲማልድ ለሃጢአቴ ለከፈለው ዋጋ መታያዎች ናቸው። 

5. የቆሰለው አዳኛችን ዛሬም በታላቅ ክብሩ በሰማያት አለ፤እኛም አንድ ቀን እናየዋለን

“ከዚያም ተመለከትሁ የብዙ መላዕክትም ድምፅ ሰማሁ ቁጥራቸው ሺህ ግዜ ሺህ እልፍ ግዜ እልፍ ግዜ ነበር፤ እርሱም ከዙፋኑ በሕያዋን ፍጡራን በሽማግሌዎቹም ዙሪያ ከበው ነበር፤በታላቅ ድምፅም እንዲህ ብለው ዘመሩ፤

ለታረደው በግ ሃይል እና ባለፀግነት 

ጥበብ እና ብርታት

ክብር እና ሞገስ ምስጋናም

ሊቀበል ይገባዋል።”

ስለእኛ የቆሰለው ኢየሱስ የታረደው በግ ዛሬም በዙፋኑ ላይ በምስጋና ተከብዋል።

“ለወደደን ከሃጢያታችንን በደሙ ነፃ ላወጣን አምላኩን እና አባቱን እንድናገለግል መንግስትና ካህናት ላደረገን ለእርሱ ክብር እና ሃይል ከዘለዖለም እስከ ዘለዖለም ይሁን አሜን

እነሆ አምላካችን ይመጣል

የወጉት እንክዋ ሳይቀሩ

ዐይን ሁሉ ያየዋል።”

ዮሐ ራዕይ 1፡ 5-7

አምላካችን ዳግም ይመጣል! አልያም እኛ ወደ እርሱ እንሄዳለን።በአይናችን ስለእኛ የተወጉትን እጆቹን እግሮቹን እና ጎኑን እናየዋለን!   

ማራናታ! አሜን ጌታ ሆይ ቶሎ ና!

Last modified on %PM, %09 %668 %2018 %18:%Apr
Genaye Eshetu

Genaye Eshetu is a Creative Communicator. She did her BA in Language and Literature and her Masters in Journalism and Communication. She aspires to combine and use various communications means, especially media, which is the global language of this generation, for creative evangelism.

genaye.com

በርባን እና እኔ

ህዝቡ ሁሉ የኢየሱስን መሰቀል ይጠይቃል። በትረካው ውስጥ ማንን አያችሁ?

David Mathis - avatar David Mathis

ጨርሰው ያንብቡ

ኢየሱስ ቢሆን ምን አያደርግም ነበር? (ወቅታዊውን የሃገራችን ሁ…

አሁን ሃገራችን ስላለችበት ሁኔታ ሳስብ አንድ ነገር ትዝ አለኝ። ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ የኖረበት ዘመን (የመጀመርያው ክፍለዘመን) ላደገበት የአይሁድ ማህበረሰ...

Naol Befkadu - avatar Naol Befkadu

ጨርሰው ያንብቡ

 

The views and opinions expressed on Daily Injera are solely those of the original authors and our contributors. These views and opinions do not necessarily represent Daily Injera or our Staff.

Newsletter

Subscribe to our newsletter. Don’t miss any article, devotionals or wallpapers.

We do not spam!

You're automatically subscribed to bi-weekly articles and daily devotionals. You can customize your subscription settings here.