Monday, 15 July 2024

እኛም ደግሞ የበደሉንን ይቅር እንደምንል በደላችንን ይቅር በለን

Posted On %AM, %11 %041 %2016 %03:%Oct Written by

ማቴዎስ 6፡14-15 “ለሰዎች ኃጢአታቸውን ይቅር ብትሉ፥ የሰማዩ አባታችሁ እናንተን ደግሞ ይቅር ይላችኋልና፤ ለሰዎች ግን ኃጢአታቸውን ይቅር ባትሉ፥ አባታችሁም ኃጢአታችሁን ይቅር አይላችሁም”።

ማርቆስ 11፡25-26 “ለጸሎትም በቆማችሁ ጊዜ፥ በሰማያት ያለው አባታችሁ ደግሞ ኃጢአታችሁን ይቅር እንዲላችሁ፥ በማንም ላይ አንዳች ቢኖርባችሁ ይቅር በሉት። እናንተ ግን ይቅር ባትሉ በሰማያት ያለው አባታችሁም ኃጢአታችሁን ይቅር አይላችሁም”።

ማቴዎስ 18፡34-35 “ጌታውም ተቈጣና ዕዳውን ሁሉ እስኪከፍለው ድረስ ለሚሣቅዩት አሳልፎ ሰጠው። ከእናንተ እያንዳንዱ ወንድሙን ከልቡ ይቅር ካላለ፥ እንዲሁ ደግሞ የሰማዩ አባቴ ያደርግባችኋል።

በእግዚአብሔር መንግስት ውስጥ ይቅር የማይሉ ሰዎች የሉም። ግን ታዲያ ማን ሊድን ይችላል? ይህ በእግዚአብሔር ዘንድ እንጂ በሰው ዘንድ አይቻልም (ማርቆስ 10፡27)። እግዚአብሔር ታዲያ እዚህ ባለ ሕይወታችን ይቅር ከማለት የማንጎድል ፍጹማን ሰዎች ያደርገናል? በሕይወታችን ውስጥ በማንኛውም ጊዜ ላይ ለሚደርስብን ማንኛውም ስድብ ወይንም ጉዳት መልሳችን ለአፍታ እንኳን ቢሆን ቁጣ ወይንም ቂም እና ራስን መጣል ወደማይሆንበት ሁኔታ በቅጽበት ያመጣናል?

የይቅርታ መሠረት 

ይህንን ለመመለስ እንደዚህ ብለን እንጠይቅ እስቲ፤  ኢየሱስ ይቅርታን ከባህሪዎች ሁሉ በልዩነት ከደቀ መዛሙርቱ የሚፈልገው ነገር ነበር? ማለትም የእግዚአብሔር ይቅርታ የሚወሰንበት ብቸኛው ባህሪ ነው? አይደለም! እንዳንጠፋ ካስፈለገ ሁሉም የኢየሱስ ትዕዛዛት መፈጸም አለባቸው። ሰውን ከእግዚአብሔር የሚያቆራርጠው እንዲሁ ይቅር የማይል መንፈስ ሳይሆን ኃጢያት ነው። “ቀኝ ዓይንህም ብታሰናክልህ አውጥተህ ከአንተ ጣላት አሊያም አባታችሁ ኃጢያታችሁን ይቅር አይላችሁም" (ማቴዎስ 5፡29)። "ወንድማችሁን ጨርቃም ብትሉት አባታችሁ ኃጢያታችሁን ይቅር አይላችሁም" (ማቴዎስ 5፡22)። "ጠላቶቻችሁን ባትወድዱ በሰማይ ያለው አባታችሁ ኃጢያታችሁን ይቅር አይላችሁም" (ማቴዎስ 5፡44) "በእኔም ከሚያምኑ ከነዚህ ከታናናሾቹ አንዱን የሚያሰናክል አባቴ ይቅር አይለውም" (ማቴዎስ 18፡6)። በእያንዳንዱ የኢየሱስ ትዕዛዝ ላይ “ይህን ባታደርጉ ወደ መንግስተ ሰማይ አትገቡም” የሚለው ምሳሌ አለ። ይሄ አባቴ ይቅር አይላችሁም ከማለት ጋር አንድ አይነት ነው (ማቴዎስ 7፡21-23)።

ስለዚህ “ይቅር እንድትባሉ እናንተም ይቅር በሉ” የሚለው ትዕዛዝ ኢየሱስ ከሚፈልጋቸው ምግባሮች ውስጥ አንዱ ነው እንጂ ብቸኛው አይደለም። ብቸኛው ሳይሆን አንዱ ህግ ነው። ኢየሱስ በዮሐንስ 8፡34 ላይ እንደሚለው “እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ኃጢአት የሚያደርግ ሁሉ የኃጢአት ባርያ ነው”። ወይንም ዮሐንስ በመጀመሪያው መልዕክቱ እንደጻፈው “እርሱም ኃጢአትን ሊያስወግድ እንደ ተገለጠ ታውቃላችሁ፥ በእርሱም ኃጢአት የለም። በእርሱ የሚኖር ሁሉ ኃጢአትን አያደርግም። ኃጢአትን የሚያደርግ ሁሉ አላየውም አላወቀውምም. . . ከእግዚአብሔር የተወለደ ሁሉ ኃጢአትን አያደርግም፥ ዘሩ በእርሱ ይኖራልና ከእግዚአብሔርም ተወልዶአልና ኃጢአትን ሊያደርግ አይችልም።" (1 ዮሐንስ 3፡5 ፣ 9 ፤ ንጽጽር 3፡14 ፣ 16 ፤ 4፡7 ፣ 8 ፣ 12 ፣ 16) ወይንም ጳውሎስ እንደጻፈው የሥጋ ሥራም የተገለጠ ነው እርሱም . . . ጥል፥ ክርክር፥ ቅንዓት፥ ቁጣ . . . ይህንም የሚመስል ነው። እንደዚህ ያሉትን የሚያደርጉ የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም። (ገላትያ 5፡19-21 ፤ ንጽጽር 1ቆሮንቶስ 6፡10 ፤ ሮሜ 8፡13)። የዕብራዊው ጸሐፊም እንደጻፈው “ከሰው ሁሉ ጋር ሰላምን ተከታተሉ ትቀደሱም ዘንድ ፈልጉ፥ ያለ እርሱ ጌታን ሊያይ የሚችል የለምና” (ዕብራውያን 12፡14 ንጽጽር 10፡26 ጀምሮ ፤ 6፡4 ጀምሮ )። ስለዚህ ኢየሱስ “ለሰዎች ግን ኃጢአታቸውን ይቅር ባትሉ፥ አባታችሁም ኃጢአታችሁን ይቅር አይላችሁም” ሲል ሙሉ የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት ከሚሉት የተለየ ነገር እየተናገረ አይደለም።

እዚህ ጋር የሚጋጭ ነገር የለም?

ያለ እርሱ ልንድንበት የማንችለው ከኃጢያት ንጹህ እንድንሆን የሚጠብቅ የፍጹምነት መስፈርት ነው? እንደዚያስ ከሆነ “በደላችንን ይቅር በለን” የሚለውስ ልመና ምን የሚል ትርጉም ይኖረዋል? ወይንም “በኃጢያታችን ብንናዘዝ” (1 ዮሐንስ 1፡9) የሚለውስ ምክር ምን የሚል ትርጉም ይኖረዋል? ደቀ መዛሙርት የሚባሉት ሁሉ ኃጢያትን አድርገው የማያውቁ ቢሆኑ ኖሮ ለምን “ኃጢአታችንንም ይቅር በለን” (ሉቃስ 11፡4) ብለው እንዲጸልዩ ትዕዛዝን ይሰጣቸዋል?   

ወደፊት ልንፈጽማቸው የሚችሉት “በደል” እና “ኃጢያቶች” በኢየሱስ አተያየት እነማን ናቸው? ይቅር ከማለት ውጪ ያሉትን ኃጢያቶች ማለቱ ነው? አይደለም። ኃጢያትን እንደዚያ አድርጎ አልከፋፈለም። ይሁን እንጂ ይቅርታን ልንጠይቅበት የሚገባ አንዱ “በደላችን” ይቅር የማይልን መንፈስ ወይንም ይቅርታ ከማድረግ ስለመጉደላችን ነው። ግን “በደላችንን” በሚለው ፈንታ “ይቅርታ ለማድረግ አለመቻላችን” በሚለው ብንተካው ምን እንደሚሆን አስተውሉ። ይህንን ይመስላል:- “እኛም ደግሞ የበደሉንን ይቅር እንደምንል “ይቅርታ ለማድረግ መጉደላችንን” (አንድ የተወሰነ ዕዳ ነው ይሄ) ይቅር በል”። ይሄ ግን እርስ በእርሱ የሚጋጭ ሀሳብ ነው። “እኛም ደግሞ የበደሉንን ይቅር እንደምንል” የሚለው በእርግጥም ይቅር እንደምንል ሲያሳይ “ይቅርታ ለማድረግ አለመቻላችንን” የሚለው ልመናቸን ግን ይቅርታ አለማድረጋችንን ያሳያል። እረስ በእርስ ለተፈጠረው ተቃርኖ መፍትሄ የሚሆንልን ነጥብ “እኛም ደግሞ የበደሉንን ይቅር እንደምንል” የሚለው ሀረግ በደቀ መዛሙርቱ ዘንድ ይቅር የማይል መንፈስ በላያቸው ላይ ሠልጥኖ እንዳልነበረ ማሳያ እንዳልሆነ ነው። ኢየሱስ በደላችን ይቅር እንዲባልልን እንድንጸልይ ካዘዘ አንዱ በደላችን ደግሞ ይቅርታ ከማድረግ መጉደላችን ከሆነ “እኛም ደግሞ የበደሉንን ይቅር እንደምንል” የሚለው ሀረግ ፈጽሞ ይቅር የሚል መንፈስ ብቻ ነው ከእግዚአብሔር ዘንድ ይቅርታ ማግኘት የሚችለው በሚል ፍቺ መጠቅለል የለበትም።

ታዲያ ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ሌሎችን ይቅር እንደሚሉ ይቅር እንዲባሉ እንዲጸልዩ ሲነግራቸው እንደሚከተለው እንድጸልይ አስቦ አይደለምን:- “አባት ሆይ ዛሬ ለአበበ ይቅርታ ከማድረግ ስለመጉደሌ ይቅር በለኝ፣ክፉ በተናገረኝ ጊዜ ተበሳጭቼ እና በእኔነት ተይዤ ንዴቴን ስለገለጽሁበት ቀኑን ሙሉ ደግሞ ቂም ይዤ እንዴት አድርጌ ዋጋውን እንደምሰጠው ሳምሰለስል እስከዛሬ የበደለኝንም ስቆጥር ዋልኩ። ለእኔ ያለህን ቋሚ ምህረት ባሳሰብከኝ ጊዜ ግን ህሊናዬ ወቀሰኝ። ስለዚህ ወደ እርሱ ሄጄ ይቅርታ ጠየቅሁት (ማርቆስ 11፡25) ከእንግዲህ ወዲህ ቂሙን ቋጥሬ መቆየት አልሻም። ከእራስ ወዳድ ቁጣዎቼ ነጻ አውጥተኸኛልና ዛሬ አበበን ይቅር ከማለት ስለጎደልሁ ይቅር እንድትለኝና እንዲህ ካለ ፈተና ውስጥ ደግሜ እንዳልወድቅ ጠብቀኝ።”

በሌላ አገላለጽ “እኛም ደግሞ የበደሉንን ይቅር እንደምንል በደላችንን ይቅር በለን” የሚለው ያለፈው ይቅር ያለማለት መንፈስ ደግሞ ቢነሳ ጠፍተናል ማለት አይደለም። ግን ምን ማለት ነው በአንድ ሰው ላይ ቂሙን አጥብቆ የሚይዝ ወደ እግዚአብሔር ምህረትን ፍለጋ ለመቅረብ እንኳን አያስብ ማለት ነው።

እግዚአብሔር እንደልባችን እምነት ነው የሚያስተናግደን:-  የተደረጉብንን በደሎች እያሰላን ቁጣን በልባችን ማከማቸት መልካም መስሎ ቢሰማን ከእግዚአብሔር ይቅርታ መጠየቃችንን ግብዝነት አድርጎ ነው የሚቆጥረው። ምክንያቱም መጥፎ እንደሆነ የምናምነውን ነገር እየጠየቅነው ስላለ። ድርጊታችሁ እንደሚያሳየው እናንተ አሳንሳችሁ በምታስቡት መንገድ እግዚአብሔር እንዲሰራ መጠየቃችሁና መጠቀሚያችሁ እንዲሆን ለማድረግ ማሞከር አስፈሪ ነገር ነው። 

በጸጋ እርዳታ የሆነ ይቅርታ

ይቅር ማለት የእግዚአብሔርን ይቅርታ የምናገኝበት ሥራ አይደለም። በእግዚአብሔር ምህረት ከረካ እና እልፍ እዳችን (ማቴዎስ 18፡24) በመሰረዙ ምክንያት በደስታ ከተሞላ ልብ የሚፈስ ነው። ይህ በሰው ዘንድ አይቻልም በእግዚአብሔር ዘንድ ግን ሁሉ ይቻላል። መልካም ፍሬ የማያደርግ ዛፍ ሁሉ ይቆረጣል ወደ እሳትም ይጣላል (ማቴዎስ 7፡19)። ነገር ግን ጸንቶ የቆመው ተክል ጸንቶ የቆመው እግዚአብሔር ስለተከለው ነው (ማቴዎስ 15፡13)። ማንም በእግዚአብሔር ፊት እራሱ ባመጣው መልካም ሥራ ሊመካ አይችልም (ሉቃስ 17፡10) በእግዚአብሔር ፊት እንድንቆም የሚያደርገን በጥንቃቄ ህግን ሁሉ መጠበቃችን ሳይሆን የመንፈስ ደሀ መሆናችን እና በእግዚአብሔር ምህረት ላይ ሙሉ በሙሉ መደገፋችን ነው (ሉቃስ 18፡9-14 ፤ ማቴዎስ 5፡3)። 

በእግዚአብሔር ምህረት ከላይ ዳግም የተወለደ ማንም ሰው ፈጽሞ እንደድረው መሆን እንደማይችል ይህ ነገር እርግጥ ነው። “የእግዚአብሔር ዘር በእርሱ ይኖራልና” (1 ዮሐንስ 3፡9) እንደቀድሞው በኃጢያት መኖር አይችልም። በእግዚአብሔር መንፈስ ስለሚመራ (ሮሜ 8፡14 ፤ ገላትያ 5፡18) እንደ መንፈስ ፈቃድ እንጂ እንደ ሥጋ ፈቃድ አይመላለስም (ሮሜ 8፡4)። እግዚአብሔር ስለ በጎ ፈቃዱ መፈለግንም ማድረግንም  እየሠራ ነው (ፊሊጲስዩስ 2፡13)። “ከልባችን ይቅር ስንል” የመንፈስ ፍሬ ነው (ገላትያ 5፡22)። ከክርስቶስ ጋር ተሰቅለናል፤ እኛም አሁን ሕያው ሆነን አንኖርም ክርስቶስ ግን በእኛ ይኖራል (ገላትያ 2፡20)። አዲስ ፍጥረቶች ነን (ገላትያ 6፡15)። አዲስ የመሆናችንም ምልክቱ ፍጹም መሆናችን ሳይሆን ዘወትር ይቅር ለማለት ማዘንበላችን እና እኛ የተውነውን ኃጢያት እግዚአብሔር እንዳይቆጥረው መለመናችን ነው።

 

Originally Posted at DesiringGod.org, Translated by Joshua Terefe


 

Last modified on %PM, %10 %887 %2016 %23:%Dec
John Piper

John Piper is founder and teacher of desiringGod.org and chancellor of Bethlehem College & Seminary. For 33 years, he served as pastor of Bethlehem Baptist Church, Minneapolis, Minnesota. He is author of more than 50 books, including A Peculiar Glory.

twitter.com/JohnPiper

ደስታችሁ ያረፈው በክርስቶስ ጽድቅ ላይ ነው

እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር እንደሆነ መቶ በመቶ ብታምኑ ምን የሚሆን ይመስላችኋል? እንደተቀበላችሁ ብቻ ሳይሆን በክርስቶስ ማንነት እና ሥራ ምክንያት ሙሉ ለሙሉ...

David Mathis - avatar David Mathis

ጨርሰው ያንብቡ

ሃሳባችሁን እንደ ውቅያኖስ ሰፊ በሆነው በእግዚአብሔር ሉአላዊነት…

አንዳንድ ጊዜ ሃሳባችንን እንደ ውቅያኖስ ሰፊ በሆነው በእግዚአብሔር ሉአላዊነት ውስጥ ልንጨምር ያስፈልገናል። ወደ ውስጥ በሰመጥን ቁጥር ክብደቱ ሊሰማን ይገባል...

John Piper - avatar John Piper

ጨርሰው ያንብቡ

 

The views and opinions expressed on Daily Injera are solely those of the original authors and our contributors. These views and opinions do not necessarily represent Daily Injera or our Staff.

Newsletter

Subscribe to our newsletter. Don’t miss any article, devotionals or wallpapers.

We do not spam!

You're automatically subscribed to bi-weekly articles and daily devotionals. You can customize your subscription settings here.