Monday, 15 July 2024

የፖርኖግራፊ ሱሰኝነት ምልክቶች እና መዘዞቹ

Posted On %PM, %27 %750 %2018 %20:%Jun Written by
የፖርኖግራፊ ሱሰኝነት ምልክቶች እና መዘዞቹ Bence Boros

ከፖርኖግራፊ ሱስ መውጣት ይቻላል!

ክፍል ሁለት - የፖርኖግራፊ ሱሰኝነት ምልክቶች እና መዘዞቹ

በቀደመው ክፍል ላይ ‘ፖርኖግራፊ’ ሰዎችን ሱሰኛ የማድረግ ከፍተኛ አቅም እንዳለው አይተናል። ለዛሬ ደግሞ የሱሰኝነቱን ምልክቶች /Symptoms/ እናያለን።


1. ከፍተኛ ፍላጎት


አንድ ሰው ሱስ ደረጃ ላይ ከደረሰ ለፖርኖግራፊ ከፍተኛ ፍላጎት ይኖረዋል።በውስጡ የማያቋርጥ ፍላጎት ይቀጣጠላል። በማንኛውም ቦታ በማንኛውም ሁኔታ በማንኛውም ሰአት ፖርኖግራፊን መመልከት ይፈልጋል። ከዚህ በተጨማሪ የሚመለከትበትን ጊዜ እየጨመረ ይመጣል። በሳምንት ያይ የነበረ በቀን፤ በቀንም አንዴ ያይ የነበረው ሁለቴ ማየት ከጀመረ፣ በፖርኖግራፊም የሚያጠፋውም ጊዜ እያደገ ከመጣ፤ በሚመለከትበት ጊዜ የሚሰማው መነቃቃት እና ደስታ በሀፍረት፤ ጥፋተኝነት ስሜት እና ፀፀት ሲተካ ነገሩ ሱስ ደረጃ ላይ መድረሱን ይጠቁማል። 


2. ለማቆም አለመፈለግ / አለመቻል


ሱስ ውስጥ የገባ አንድ ሰው ፖርኖግራፊ መመልከቱን ማቆም አይፈልግም። ሱስ እንደሆነና ችግር መሆኑን እንኳን መቀበል አይፈልግም። ይህም የሚሆነው ሱስ ውስጥ ስለገባና ከዛ ህይወት ቢወጣ ሌላ የሚያዝናናው ነገር ሊያገኝ እንደሚችል ስለማያምን ነው። በሌላ መልኩ ደግሞ ለማቆም እየፈለጉ አለመቻልም የሱሰኝነት ማሳያ ነው። እዚህ ጋር አንድ ወንድም በድምጽ ባስቀመጠልኝ መልዕክት ውስጥ “እኔ ከፖርኖግራፊ ሕይወት ለመውጣት ከ100 ጊዜ በላይ ለራሴ ቃል ገብቼ ነበር፤ ነገር ግን ተመልሼ እዛው ሕይወት ውስጥ እገኛለው” ብሎኛል። ይህ ንግግር የሚያሳየው ከባድ የሆነ ሱስ ውስጥ መግባቱን ሲሆን እየተጸየፍነውም የምናደርገው ነገር ሱስ እንደሆነብን ያሳያል። 


3. በሌላ ነገር ደስታ አለማግኘት


አንድ ሰው ወደዚህ ሱስ ውስጥ ከመግባቱ በፊት ያስደስቱት የነበሩትን ነገሮች ለምሳሌ ከቤተሰብና ከወዳጆች ጋር ጊዜ ማሳለፍ፣ ወደ ኃይማኖት ስፍራ መሄድ፣ ስፖርት መስራት፣ ፊልም ማየት፣ የእግር ጉዞ ማድረግ ወ.ዘ.ተ በመተው ደስታውን ሙሉ ለሙሉ በፖርኖግራፊ ላይ ካስቀመጠ ይህ ሰው የፖርኖግራፊ ሱስ ውስጥ እንደገባ ያሳያል።


4. ከተጽኖው ጋር መቀጠል


በፖርኖግራፊ ሱስ የተጠቃ ሰው በሱሱ ምክንያት ብዙ ነገር እንዳጣ እያወቀ ህይወቱ ወደተሳሳተ አቅጣጫ እያመራ መሆኑን እየተረዳ በዛው ከቀጠለ ሱስ ደረጃ ላይ ለመድረሱን ያሳያል።


5. ሚስጥራዊነት

በፖርኖግራፊ ሱስ ውስጥ ያለ ሰው ህይወቱን አጠገቡ ካሉ እና ከሚወዳቸው ሰዎች ሚስጥር ከማረጉ የተነሳ ድብቅ እና ሁለት ገፅታ ያለው ባይተዋር ሰው እንደሆነ ይሰማዋል። ሚስጥሩም እንዳይጋለጥ ያያቸውን ድህረ ገፆች በማጥፋት፤ የት እና ምን ያደርግ እንደነበር ቤተሰቡን እና ጓደኞቹን ሰዎችን ይዋሻል። የሚሰማውንም ሀፍረት ለመሸፈን በማስመሰል ህይወት ውስጥ ይዘፈቃል።

6. ሐላፊነትን አለመወጣት


ብዙ ሰዓታትን በፖርኖግራፊ ከማሳለፍ የተነሳ በአግባቡ ስራን አለማከናወን፤ የቤተሰብ፤ የማህበራዊና መንፈሳዊ ሐላፊነቶችን መወጣት አለመቻል እና ገለልተኝነት ሱስ ደረጃ ላይ መደረሱን ያሳያል። 


7. የፀባይ መቀያየር


በሱስ ውስጥ ያሉ ሰዎች የሚፈልጉትን ባጡ ጊዜ በጣም ብስጩ ፤ ቁጡ እና በጥቂት ነገር የሚናደዱ ይሆናሉ።


ከላይ የጠቀስናቸው ዋና የሚባሉት የሱስ ምልክቶች ሲሆን እነዚህ ምልክቶች የሚታዩባቸው ሰዎች ቆም ብለው ራሳቸውን አይተው ዕርዳታ ካልፈለጉ ለፖርኖግራፊ ሱስ መዘዞች ራሳቸውን ያጋልጣሉ። 

የፖርኖግራፊ መዘዞች


ፖርኖግራፊ መመልከት የሚያስከትለው እጅግ በጣም ብዙ መዘዞች አሉት። ጉዳቶቹም መንፈሳዊ፣ ስነ ልቦናዊና ማህበራዊ ናቸው። እስኪ የተወሰኑትን እንመልከት።


1. ከእግዚአብሔር ይለያል


በክርስቶስ የተጠራነው ንፁህ እና ቅዱሳን (1ጴጥ 1:10 ) እንድንሆን እንደመሆኑ በድብቅ የምንሰራቸው ማናቸውም ኃጥያቶች በመንፈሳዊ ሕይወታችን እንድንደክም ያደርጉናል። በፖርኖግራፊ ሱስ ላለ ሰው መፀለይ፤ ቃሉን ማንበብ እና ከሌሎች ክርስትያኖች ጋር ህብረት ማድረግ ከባድ ይሆናል። በዚህ ሱስ ከተጠቁ ወገኖቼ በተደጋጋሚ ከሰማዋቸው ድምጾች ዋነኛው፤ “መጸለይ አልቻልኩም፤ ቤተ ክርስቲያን መሄድ ከበደኝ፤  ምክንያቱም ፊቴ ላይ የሚመጣው የተመለከትኩት ፖርኖግራፊ ነው” የሚል ነው።  

ሀሳብ ከሌላው ሰው የተደበቀ ስለሆነ ብዙ ትኩረት ባይሰጠውም ተጨባጭ ሀጢያት ከመሆን አያግደውም። ፖርኖግራፊ መመልከት ኃጥያት መሆኑ ግልፅ ነው። ጌታችን ኢየሱስ “ወደ ሴት ያየ ሁሉ የተመኛትም ያን ጊዜ በልቡ ከእርስዋ ጋር አመንዝሮአል” ( ማቴዎስ 5:28) እንዳለ እናስታውስ። እኔ ፖርኖግራፊ አይቼ በፍጹም አልመኝም የሚል ይኖር ይሆን?

አንድ ሰው ፖርኖግራፊ እያየ ሙሉ በሙሉ ለእግዚሐብሄር ተሰጥቻለሁ ማለት አይችልም። ምክንያቱም በማቴ 6:24 ላይ እንደሚናገረው አንድ ሰው ለሁለት ጌቶች ሊገዛ አይችልም። የስጋን ፈቃድ እየፈፀሙ ክርስቶስን ለማምለክ መሞከር ትርፉ ብቸኝነት፤ ተስፋ መቁረጥ እና ውድቀት ነው። ፖርኖግራፊ መንፈሳዊ ሕይወትን የሚያኮላሽ ነው። ሰው መንፈሳዊነቱን ካጣ ደግሞሞ ምንም ነገር ቢያገኝ አይረካም።ፖርኖግራፊ ዋና ነገሮቻችንን ያሳጣናል።


2. ድብርት / ጭንቅት


ፖርኖግራፊ ውስጥ የገባ ሰው ያለበት ሕይወት ትክክል እንዳልሆነ ያውቃል። ስለዚህ ከባድ የሆነ ጭንቀት ይሰማዋል። ብዙ ሰዎች በዚህ ምክንያት ሀፍረት ስለሚሰማቸው በራስ መተማመናቸውን ያጣሉ። ስለዚህ በከባድ የድብርት ስሜት ውስጥ ሆነው ራሳቸውን ከሰው ያገላሉ።


3. አቅምን ይገላል


በዚህ ሱስ የተያዘ ሰው በቀን ውስጥ በትንሹ 3 ሰዓት ፖርኖግራፊ በመመልከት ሊያጠፋ ይችላል። ምን ያህል የከበረ ጊዜውን እንደሚያጠፋም አስተውሉ! ከዚህ በተጨማሪ በዚህ ሱስ መጠቃት ኃላፊነትን ቸል ወደማለት ያደርሳል።  የፈጠራ ችሎታን ይቀንሳል።በፖርኖግራፊ ምክንያት የአፈጻጸም ብቃታቸው ወርዶ ከስራና ከትምህርት የተባረሩ ሰዎች ጥቂቶች አይደሉም። አስደናቂና ዕምቅ ችሎታ ያላቸው ስንቶችን በፖርኖግራፊ ምክንያት አጥተናቸዋል?


4. ላልተፈለገ ተግባር ያጋልጣል


ጥናቶች እንደሚያሳዩት ከሆነ ሕጻናትን ከደፈሩ ሰዎች ብዙዎቹ በፖርኖግራፊ ሱስ የተጠቁ ናቸው።ከዚህ በተጨማሪ ፖርኖግራፊ የሚመለከቱ ሰዎች ከማይመለከቱት ጋር ሲነጻጸሩ በ400% ሴተኛ አዳሪዎች ጋር የመሄድ ዝንባሌ አላቸው። የተመሳሳይ ጾታ ፖርኖግራፊ በመመልከታቸው ብቻ ወደ ግብረ ሰዶማዊነት የገቡ ሰዎች እንዳሉም ለማየት ችያለው።


5. የተሳሳተ አመለካከት


በሱሱ የተጠቁ ሰዎች ስለራሳቸው የተሳሳተ አመለካከት ይኖራቸዋል። ‘እኔ አልጠቅምም ፤እኔ ከንቱ ሰው ነኝ ፤እኔ እግዚአብሔር ይጠላኛል፤ እኔ ከሰው አንሳለው ፤መቼም ከዚህ ህይወት መውጣት ስለማልችል ስኬታማ ትዳር አይኖረኝም፤ የሚሉ አሉታዊና ተስፋ የመቁረጥ አመለካከቶችን ያዳብራሉ። እንዲህ አይነቱ ለራስ የሚሰጥ የወረደ ግምት በቶሎ ካልተቀጨ ከባድ ወደሆነ አዕምሮአዊ እና ስነ ልቦናዊ በሽታ ያመራል። ለራሱ የተሳሳተ አመለካከት ያለው ሰው ስለ ሰዎች ትክክለኛ አመለካከት ሊኖረውም አይችልም። 

ሌላው የተሳሳተ አመለካከት የሚሰጠው ለተቃራኒ ጾታ ነው። እስከ ዛሬ በዚህ ጉዳይ ላይ ያማከርኳቸው ወንድሞችና እህቶች ሁሉም ለማለት በሚያስደፍረኝ ሁኔታ ለተቃራኒ ጾታ ዝቅ ያለ አመለካከት እንዳላቸው ገልጸውልኛል።ብዙውን ጊዜ በፖርኖግራፊ ምስሎች ላይ ሴቶች የወንዶች የወሲብ ፍላጎት አገልጋይ ተደርገው የተሳሉ ሲሆን ፖርኖግራፊ የሚመለከቱ ወንዶችም ልክ እንደዛው ሴቶቹን እንደሚመልከቱ ነግረውኛል። ሴቶች ደግሞ ሁሉም ወንዶች ጨካኝና ለስሜታቸው ብቻ የሚኖሩ እንደሆኑ እንዲያስቡ እንዳደረጋቸው አውርተውኛል።በዚህ የተሳሳተ አመለካከት ምክንያት ጤናማ የሆነ የፍቅር ህይወት ለመጀመር የተቸገሩ ጥቂቶች አይደሉም።


6. ትዳርን ይበጠብጣል


ከሀገር ውጪ የሚኖር አንድ ሰው ደውሎ እንዲህ አለኝ ‘እኔ በፖርኖግራፊ ሱስ ከተጠቃሁ አመት ሆኖኛል። በዚህ ጊዜ ውስጥ ብዙ ችግር ገጥሞኛል። በስራ ሰአቴ ላይ ረጅም ጊዜ የማጠፋው ፖርኖግራፊ በመመልከትና ግለ ወሲብ በመፈጸም በመሆኑ እቤት ስገባ ከባለቤቴ ጋር ግንኙነት የማድረግ ፍላጎት የለኝም” የዚህ ሰው ችግር የብዙዎችም ነው። ‘ፖርኖግራፊ’ የሚመልከቱ ሰዎች በትዳራቸው ያላቸውን እርካታ ያጡታል። የግንኙነት መቃወስም ( Sexual Dysfunction) ሊያጋጥማቸው ይችላል። ይህ ደግሞ ወደ ፍቺ እና የቤተሰብ መበተን እስከማምራት ይደርሳል።

በሚቀጥለው ሳምንት ረቡዕ፣ ከፖርኖግራፊ ሱስ እንዴት መውጣት እንደምንችል እናያለን።


Download the series in PDF (166KB)


በፖርኖግራፊና ግለ ወሲብ/Masturbation/ ሱስ ተይዛቹ የምትጨነቁ ወገኖቻችን በማንኛውም ጊዜ ልንረዳቹ ዝግጁ ነን። በ+251945000005 ላይ በኢትዮጵያ ሰዓት አቆጣጠር ከጠዋቱ 4 ሰዓት ጀምሮ እስከ ምሽቱ 4 ሰዓት ድረስ ይደውሉልን። ከኢትዮጵያ ውጭ ከሆኑ በቫይበር፣ በቴሌግራም፣ በኢሞ፣ በዋትስአፕ እና በላይን ሊያገኙን ይችላሉ።

Last modified on %PM, %05 %593 %2018 %16:%Jul
Ermias Kiros

Ermias Kiros has a bachelors degree in theology and social anthropology, and he is currently doing his Masters in Counseling Psychology. Currently, he works as inspirational public speaker and counselor.

https://www.facebook.com/ermias.kiros.1

ድክመታችሁን ለእግዚአብሔር ስጡት

እንደምን አላችሁ? ጥፋተኛ ብሆንም እነዚህ ቃላት እንደ ጥያቄ ሳይሆን እንደ ሠላምታ ሲቀርቡልኝ ትንሽ ይረብሸኛል። ተጨባጭ መልስ ሳንፈልግ “እንዴት ናችሁ?” ...

Steven Lee - avatar Steven Lee

ጨርሰው ያንብቡ

በህይወቴ ላይ የእግዚአብሔር ፍቃድ ምንድን ነው?

የዚህን መልስ ማወቅ ሁላችንም እንፈልጋለን አይደል? ከዚህ በላይ ውጥረትን ሊፈጥር የሚችል ርዕስ ሊኖር ይችላል? ስለፈጠረን ፣ ደግሞም በሕይወት እያቆየን ስላለ...

Jonathan Parnell - avatar Jonathan Parnell

ጨርሰው ያንብቡ

 

The views and opinions expressed on Daily Injera are solely those of the original authors and our contributors. These views and opinions do not necessarily represent Daily Injera or our Staff.

Newsletter

Subscribe to our newsletter. Don’t miss any article, devotionals or wallpapers.

We do not spam!

You're automatically subscribed to bi-weekly articles and daily devotionals. You can customize your subscription settings here.