Monday, 15 July 2024

አንቀፅ 17፣ ነፃነት/ባርነት — ከአድዋ - ጎልጎታ

Posted On %AM, %02 %916 %2018 %00:%Mar Written by
አንቀፅ 17፣ ነፃነት/ባርነት — ከአድዋ - ጎልጎታ © Genaye Eshetu

ይህ ታሪክ ከተፈፀመ እነሆ በዛሬዉ 122 ዓመቱን ይዟል። ይህ ቀን ለአሁኗ ኢትዮጵያ ማንነቷን ያስጠበቀችበት፣ ከባርነት ራሷን ነፃ ያደረገችበት ቀን ነው። ከመላው የአለም ኃያላን የተነሳን ከባድ የባርነት በትር በፅኑ ትግል ከጫንቃዋ ያነሳች ብሎም ለመላው የአፍሪካ ሀገራትና ህዝቦች የነፃነት ምክንያት ነበረች።

እስቲ፣ ከምክንያት ጋር ለማየት እንዲረዳን የዚህን ታሪካዊ ስፍራ ስያሜና ለዚህ ታሪካዊ ጦርነት መነሻ የነበረውን ነገር እናንሳ። አድዋ፣ የስሙን ትርጓሜ ከጣልያናዊዉ ኢትዮጲያን ወዳድ ሪቻርድ ፓንክረስት ከተፃፈዉ ፅሁፍ ብንመለከት፣ አድዋ ማለት “Village of the Awa” ወይም “የአዋዎች መኖሪያ” ማለት ሲሆን ይህ ስፍራ ለንግድ ስራ ለረጅም ጊዜያት ምቹ ስፍራ ሆናም አገልግላለች። ብሎም ለነገስታት ዋና መቀመጫቸውና፣ ከተለያዩ የአለም ክፍላት የሚመጡ ሰዎችን መቀበያ ስፍራቸዉም ነበረች። ያላት መልከዓ-ምድራዊ አቀማመጥ ለዚህ ሁሉ ነገር ምቹ ስፍራ አድርጓት ቆይቷል። እንዲሁም፣ ትልቁ የመገበያያ ስፍራም ነበረች። እ.ኤ.አ በ1890 በአውግስጦስ ቢ.ዌይልድ የአድዋን የገበያ ስፍራ ከተመለከተ በኋላ “ሁሉንም የምርት አይነቶች ፈልጎ የማይታጣባት” ሲል ገልፇታል። በቴክኖሎጂዉም ዘርፍ ቢሆን ከአስመራ-አዲስ አበባ የተዘረጋዉ የቴሌግራፍ መስመር ያለፈባት ሲሆን በዚህም ምክንያት ቢሮውን በዚህ ስፍራም ለመክፈት ተችሏል። ብሎም የቴሌግራፍ አገልግሎት ለትግራይ ክልል ያስገኘችም ነበረች። እናም በዚህ ስፍራ ይደረጉ ለነበሩ የልማት ዝርጋታዎች የጣልያን መንግስት የተለያዩ ስራዎችን በዚሁ አካባቢ ላይ ከኢትዮጲያ መንግስት ጋር በመተባበር ሰርቷል። ለአብነትም የቴሌግራፍ ዝርጋታዉን ያከናወኑት ጣልያናውያን ነበሩ። 

ከዚህ ሁሉ በኋላ የዚህን ስፍራ አመቺነት፣ ብሎም ኢትዮጵያን በቅኝ ግዛቷ የመያዝ ፍላጎቷ ተዳምረዉ በነበሩ የተለያዩ የልማት ድርድሮች ዉስጥ ለዚህ ታሪካዊ ጦርነት ምክንያት የነበረው የውጫሌ ስምምነትን ለማድረግ በተዘረዘሩት የህብረ ስምምነት ውል ውስጥ የፀብ መነሻ የሆነን ሃሳብ በጣሊያኖች የተጨመረው። ይህም በ1889 እ.ኤ.አ በብዙ የሀገሬ ሰዎች የምትታወቀዉን የአንቀፅ-17 የኢትዮጵያን ሉዓላዊትነትና ነፃ ሀገርነትን ጥያቄ ዉስጥ ብሎም አደጋ ዉስጥ የከተተ አንቀጽ ነው። የሰዉን ልጅ ገና በፍጥረቱ መጀመሪያ ላይ ከፈጣሪው የተነገረውን ትዕዛዝ ትርጉሙን በመለወጥ ነፃነቱን በባርነት ለወጠበት። ይህንኑ መንገድ ጣሊያን ተጠቀመችበት፤ የጣልያኑን ትርጉም ኢትዮጲያ ከውጭ ሃገራት ጋር የሚኖራትን የውጭዮሽ ግንኙነት በጣሊያን መልካም ፍቃድ ላይ ብቻ የተመሰረተ አድርጎ ማቅረብ ነበር። በዚህ የእጅ አዙር የባርነት ህይወት ላለመያዝ የቆረጡት አባት አርበኞችና መሪዎች በክተት አዋጅ ሀገሬዉን በሙሉ ወደ ጦርነት ጠሩ። በዚያን ዘመን ጣልያን በአድዋ ላይ እጅግ ከፍተኛ የጦር ሰራዊት ከነሙሉ የምግብ ስንቅ ይዘዉ ሰፍረዉ ነበር። በወቅቱ የኢትዮጲያ ጦር በቅጡ እንኳን የተደራጀ ካለመሆኑ በተጨማሪ ከጣልያን ጦር ጋር ውጊያ አድርጎ ድል ማድረግ ደግሞ የማይታሰብ ነገር ነበር። ነገር ግን ጦርነትን አማራጭ የሌለዉ አማራጭ ሆኖ ነበርና ወደ ትጥቅ ትግሉ መግባት አይቀሬ ሆነ። የዚህ ሁሉ ምክንያት ነጻነት ነው፤ ባርነትን ካለመፍቀድ መብትን በሌሎች እጅ አሳልፎ ያለመስጠት ጽኑ ትግል። ነጻነት ለሰዉ ልጅ ህይወትን የሚያስገብር ትልቅ ጥያቄዉ መሆኑን የሚያስረዳን ወቅት ሆኖ ተመልክተናል። አየህ አንባቢዬ ሆይ፣ ጣልያን ብትገዛን ኖሮ እንዲህና እንዲህ ይኖረን ነበር ሊሉህ ይችላሉ፤ ግን ሆድ ቢሞላ ነፃነት ግን ከሆድ ያለፈ የዉስጥህ ሃያል ድምፅ ያላት ጩኸት ነች። ለዚህም ነዉ ከዛሬ 122 ዓመት በፊት በአድዋ ጦርነት ሀገሬ ልጆችዋን የገበረቸዉ። በዚህም ጦርነት ማለትም 1896 እ.ኤ.አ ከማለዳዉ አንስተዉ ረፋድ ላይ ድል በመንሳት ውድ ዋጋ ያላትን ነፃነት ይሏት ነገርን ለትዉልዳቸዉ ብሎም ለመላዉ የአፍሪካ ሀገር በስጦታ መልክ የሰጠችዉ። 

በዚህ ዉስጥ አንድ ነገርን መመልከትም እንችላለን፤ ጣልያንን ያህል ትልቅ ጦር ሀገሬዉ ሁሉ በዘሩ በሃይማኖቱ ሳይከፈል በአንድነት ባይዘምትበት ነፃ ይሏትን ሀገር ሰላም ይሏትን ዉድ ነገር ማስጠበቅ ባልተቻለ ነበር። ለዘመኔ ወጣት ለሆንከዉ ለዚህ ትውልድ ምክሬ በትውልድ መዝገብ ላይ የማይሻር ታሪክ ፅፈህ ማለፍ ትፈልጋለህ? እንግዲያዉስ መከፋፈሉን ትተህ እንደ አንድ ህዝብ በችግርህ ላይ ዝመትበት፤ ድል ያንተ ነዉ። 

ይህን ቀን ሳስብ በታሪክ አጋጣሚ ዉስጥ የ2000 ዓመት ታሪክ ያለዉ ከአድዋም ጦርነት በአይነቱ የሚመሳሰል ለነፃነት የተደረገን አንድ ጦርነት አሰብኩ። ይሄ አሁን የምልህ ጦርነት ግን ከባድ መሳሪያን ያነገበ ህዝብ ከህዝብ ጋር ያደረገዉ አልነበረም እዉነት ነው። የኢትዮጲያ ጦር አቅሙን አይቶ ቢነሳ ቀድሞም ራሱን በገዛ ፍቃዱ ለባርነት ባስገዛ ነበር ነገር ግን ለነፃነታችን ሲባል ባርነትን በደም ዋጋ ተከፍሎለት ማስጠበቅ ተቻለ። ይህ ከ2000 ዘመን በፊት የነበረዉ ጦርነት ከዚህ የሚለየዉ ግን አንድ ሰው ስለ ትውልዶች ነፃነት ሲል የከፈለዉ ዋጋ ነው። አንዱ ስለ ሁሉ የሞተበት። ይህ ሰው አለም ሳይፈጠር ጀምሮ የሰውን ልጅ ከፈጠረው ከፈጣሪዉ (ከአባቱ) ዘንድ የተሰጠውን ነፃነት አጥቶት በባርነት ሲመላለስ ሲኖር እየተመለከተ ይህን አይቶ ማለፍ ያልቻለ ፍቅር ግድ ያለው ነዉ። እንደ ሃገሬ ለባርነት መግዣ ልትውል እንደነበረችዉ ትርጉሟ እንደተቀየረችዉ አንቀፅ 17 ሁሉ በምድር ሁሉ ያለን የሰው ልጅ በትዉልድ መጀመሪያ የነበሩትን አዳምና ሄዋንን በባርነት ሊገዛ የወደደውን የነፍሳቸውን ‘ጣልያን’፣ ከሰሪው እጅ የተሰጠውን ትዕዛዝ እንደ አንቀፅ 17 ትርጉሙን በመቀየር ካታለለ በኋላ ከህግ በታች በማድረግ የሰዉን ልጅና አለሙን ሲመራና ሲያዝ ለአያሌ ዘመናት በኃጥያት ባርነት ሲገዛና ሲያስተዳድር ኖረ። 

ከዚህ ሁሉ በኋላ ይህ ሰዉ ከላይ ከአባቱ ዘንድ ሆኖ ሲባዝን የነበረዉን የሰውን ልጅ ቀድሞ ወደ ነበረበት ክብር ሊመልሰው ወደደ። ከዚህ የሃጢያት ባርነት መውጪያ ብቸኛ መንገዱ እርሱ እንደመሆኑ ፍቅር ግድ ብሎት፣ ስጋን ለብሶ ከነበረዉ ክብር በእጅጉ አንሶ፣ ዛሬ እንደምናስበው የሀገሬ ታሪካዊ ቀን ህዝብን ሁሉ አስተባብሮም ሳይሆን ዋጋ ሊከፍልለት የመጣለት የሰው ልጅ ራሱ ሳይቀበለው ቀድሞ ወደነበረበት ክብራቸዉ ሊመልስ፣ በደሙ ስለኃጥያታቸዉ የሚገባውን ደመወዝ ሊከፍል ነፍሱን አሳልፎ ሰጠ።

ልክ የሃገሬ አርበኞች በአድዋ ተራራ ላይ ባርነትን ወግድ እንዳሉት፣ እንዲሁ ይህ የሰዉ ልጅ ራሱን በጎልጎታ ተራራ ላይ እንደ በግ ታርዶ ስለ ሰዉ ልጅ ሲል በሰዎች ህይወቱን አሳልፎ ሰጠ። ሰው ከላይ ከሰራዉ እጅ የተሰጠውን የቀደመ ክብሩን መለሰለት። ትርጉሙ የተቀየረበትን አንቀፅ መልሶ በደሙ ፃፈዉ። በቅዱስ ዮሃንስ ወንጌል በምዕራፍ 19 ላይ እንዲህ የሚል ቃል እናገኛለን “ኢየሱስንም ይዘዉ ወሰዱት፤ መስቀሉንም ተሸክሞ በዕብራይስጥ ጎልጎታ ወደ ተባለው የራስ ቅል ስፍራ ወደሚሉት ወጣ። በዚያም ሰቀሉት… ኢየሱስም ሆምጣጤዉን ከተቀበለ በኋላ ተፈጸመ አለ”። አዎ ተፈፅሟል፣ አንዳች ሳይቀር የሰውን ልጅ ከኃጥያት ቅኝ ግዛት ዕዳዉን ሙሉ ከፍሎ ነጻነትን እንዲሁ በነፃ ሰጥቶታል።   ይህ ነው ይሉሃል ፍቅር፣ ነፍሱን ስለ ወዳጁ አሳልፎ እስከመስጠት የሚደርስ!!! አየህ አንባቢዬ ነፃነት እንዲህ እጅግ ታላቅ ዋጋ ያላት ነገር ናት። እንኳንስ ይቅርና ለሰው ልጅ፣ ለፈጠረክ ፈጣሪህም ጭምር። ትክክለኛው ነጻነት በአለም የሚገኝ ጊዜያዊ ደስታ ሳይሆን ይህ ነዉ። ለዚህም ነው “በነፃነት ልንኖር ክርስቶስ ነፃ አወጣን” የተባለዉ!!! እኔ አበቃሁ። በዚህ የሀገሬ የድል ቀን ላይ ቆመህ/ሽ ይህን አስብ/ቢ። ነፃነትህን/ሽን ማን ወሰደዉ??? 

ክብረት ይስጥልኝ።

Last modified on %AM, %02 %022 %2018 %02:%Mar
Misgana Kibret

Misgana Kibret, a contributor writer at Daily Injera has BSC in Database Management and currently studies Christian Leadership. Misgana regularly writes on his personal blogs.

misganasview.blogspot.com

ከሮሜ 8:35 ውስጥ ልንማራቸው የምንችለው ሦስት ነገሮች

ከክርስቶስ ፍቅር ማን ይለየናል? መከራ፥ ወይስ ጭንቀት፥ ወይስ ስደት፥ ወይስ ራብ፥ ወይስ ራቁትነት፥ ወይስ ፍርሃት፥ ወይስ ሰይፍ ነውን? (ሮሜ 8፡35) ...

Jonathan Parnell - avatar Jonathan Parnell

ጨርሰው ያንብቡ

የእምነት ጉዳይ ነው

በዚህ በሚታየው እና በሚጨበጠው ቁስ ተኮር እና ስግብግብ ዓለም ውስጥ ስንኖር ለእኛ የሚያሳስቡን ነገሮች ለእግዚአብሔር ከሚያሳስቡት ነገሮች ጋር በፍጹም የተለያ...

Michelle Zombos - avatar Michelle Zombos

ጨርሰው ያንብቡ

 

The views and opinions expressed on Daily Injera are solely those of the original authors and our contributors. These views and opinions do not necessarily represent Daily Injera or our Staff.

Newsletter

Subscribe to our newsletter. Don’t miss any article, devotionals or wallpapers.

We do not spam!

You're automatically subscribed to bi-weekly articles and daily devotionals. You can customize your subscription settings here.