Thursday, 25 April 2024

ከፖርኖግራፊ ሱስ እንዴት መውጣት ይቻላል?

Posted On %PM, %04 %794 %2018 %21:%Jul Written by
ከፖርኖግራፊ ሱስ እንዴት መውጣት ይቻላል? Michail Sapiton

ከፖርኖግራፊ ሱስ መውጣት ይቻላል!

ክፍል 3 - ከፖርኖግራፊ ሱስ እንዴት መውጣት ይቻላል?

በዚህ ተከታታይ ፅሁፍ የመጀመሪያ ክፍል ላይ ‘ፖርኖግራፊ’ ሰዎችን ሱሰኛ የማድረግ ከፍተኛ አቅም እንዳለው፣ በሁለተኛው ደግሞ የሱሰኝነቱን ምልክቶች /Symptoms/ አይተናል።በዚህ የመጨረሻ ክፍል ደግሞ እንዴት ከዚህ ሱስ እንዴት መውጣት እንደምንችል እናያለን።

መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ፖርኖግራፊ ምን ይላል? 

በመጽሐፍ ቅዱስ ስለ ወሲብ ብዙ የተፃፉ ክፍሎች ቢኖሩትም ስለፖርኖግራፊ ይህ ነው ተብሎ በግልፅ የተፃፈ ነገር አናገኝም። ሆኖም ግን ክርስትና በአካል ከሚደረጉ ሃጢያቶች ከመራቅ ባለፈ የአይምሮ ንፅህናን የመጠበቅ ጉዳይ እንደሆነ ያትትልናል።  በዘፀአት 20 :17 ላይ “የባልንጀራህን ሚስት አትመኝ” ሲል ሆነ፤  ክርስቶስ በማቴዎስ 5:27 -29 “ሴትን በምኞት አይን የተመለከተ ሁሉ በልቡ ከእርሷ ጋር አመንዝሯል’’ ሲል፤ እንዲሁም በተለያዩ የአዲስ ኪዳን ክፍሎች የስጋ ምኞት ‘ነፍስንም የሚወጋ’ ሀጢያት (1ጴጥ 2:11 ) ተብሎ ሲጠቀስ እነዚህን ክፍሎች ከፖርኖግራፊ ጋር አያይዘን ልንማርባቸው እንችላለን። የስጋም ምኞት ኃጢያትን እንደምትወልድ ፤  ሀጢያትም ሞትን እንደሚወልድ ይናገራል። (ያቆ 1:14-15)  የፖርኖግራፊ ዋና ግብ የስጋን ምኞት መፍጠር ሲሆን ያም ሀጢያትን ይወልዳል፤ ሀጢያት ደግሞ ሞትን! 

ፖርኖግራፊ በክፉ የጠላት ሃሳብ የተመረዘ የሰው የሃሳብ ውጤት ነው። ጠላት ዲያቢሎስ ሁሌም ቢሆን ለጦርነት የሚጠቀመው መሳሪያ ሀሳብን ነው። ጥንት ሔዋንና አዳምን ከገነት ያስኮበለላቸው በተመረዘና ሐሳብ ነው።
“እባብም ለሴቲቱ አላት፦ ሞትን አትሞቱም፤ ከእርስዋ በበላችሁ ቀን ዓይኖቻችሁ እንዲከፈቱ እንደ እግዚአብሔርም መልካምንና ክፉን የምታውቁ እንድትሆኑ እግዚአብሔር ስለሚያውቅ ነው እንጂ። ሴቲቱም ዛፉ ለመብላት ያማረ እንደ ሆነ፥ ለዓይንም እንደሚያስጎመጅ፥ ለጥበብም መልካም እንደ ሆነ አየች፤ ከፍሬውም ወሰደችና በላች፤ ለባልዋም ደግሞ ሰጠችው እርሱም ከእርስዋ ጋር በላ” ( ዘፍ3:4:5 ) ዲያብሎስ አሁንም እየተዋጋን እና  እየጣለን ያለው ሄዋንን በጣለበት መሣሪያ ይህም በተመረዘ ሃሳብ ነው። አሁን ላለንበት ዘመን ደግሞ በኢንተርኔት፣ በዘፈን፣ በፊልም፣ በመጽሐፍ፣ በጌም በመሳሰሉት ይህን ሀሳብ  እያቀበለን ነው። ወዳጄ መምሕር ነቢዩ ተስፋ እንዳለው “በዚህ ዘመን የሰይጣን ተቀዳሚ አላማ ኃጥያትን ተደራሽ ማድረግ ነው”።

መጽሐፍ ቅዱስ አዕምሮአችንን በላይ ባሉ ነገሮች ላይ እንድናደርግ ያዘናል። (ቆላ 3:2 ) በስጋ ስላለው ነገር ከማሰብ ይልቅ መንፈሳዊውን ነገር እንድናስብም ያሳስበናል። (ሮሜ 8:8) ፖርኖግራፊን የሚመለከት ሰው አይምሮውን በስጋ ምኞት ላይ እንጂ በእግዚሐብሄር ሀሳብ ላይ ሊያደርግ አይችልም።  የአንድ ክርስቲያን ግብ መሆን ያለበት በአዕምሮ መታደስ መለወጥ ነው። (ሮሜ 12:2) የክርስቲያን ሰውነት የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያ ቤተመቅደስ እንደመሆኑ ማናቸውንም በስጋ የሚደረግ ሀጢያት ማስወገድ ይኖርበታል። ( 1 ቆሮ 5:9-11፤  ገላ 5:19-21 ፤ኤፍ 5 1-5 ፤ቆላ 3:5- 6 ፤ ዕብ 12:15-17)  ስለዚህ የተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች እንደምናየው በፖርኖግራፊ ሱስ የተያዘ ሰው በንስሃ እስካልተመለሰ ከእግዚአብሄር እንደተለየና የእግዚአብሄርንም ርስት እንደማይወርስ ማየት እንችላለን።   

በዚህ ዘመን የሰይጣን ተቀዳሚ አላማ ኃጥያትን ተደራሽ ማድረግ ነው

ክርስትያን እና ፖርኖግራፊ

ማንኛውም ክርስቲያን እግዚአብሄር ኃጢያትን ጨምሮ ማናቸውንም ነገር ማሸነፍ እንደሚችል፤ ሁሉን ቻይ እንደሆነ እና ክርስቶስም ማናቸውንም ፈተና ልንቋቋም የምንችልበት ፀጋ እንደሰጠን ቢያምንም በፖርኖግራፊ ሱስ እየታገለ ያለ ክርስትያን ግን ይህን እውነት መጠራጠር ይጀምራል። ከብዙ ፀሎት፣ ለእግዚሐብሄር እና ለራስ ከሚደረግ ከብዙ ቃለ መሀላ፤ ጥረት እና ትግል በኋላ ራሱን በሱስ ውስጥ መልሶ ወድቆ ሊያገኘው ይችላል።  በእርግጥ እግዚሐብሄር አለ! በእርግጥ እግዚሐብሄር ሁሉን ቻይ ነው! ሆኖም ግን እኛ እንደምንፈልገው ነፃ መውጣት በአንዴ ላይሆን ይችላል። በዚህ ሱስም ውስጥ ያሉ ክርስትያኖችም ከዚህ አንፃር በቤተ ክርስትያን ካለው መገፋት እና ሀፍረት የተነሳ መፍትሄን ከመፈለግ ያፈገፍጋሉ። ይህም ግለሰብ በቤተክርስትያን አገልግሎት ወይም መሪነት ቦታ ካለ ነገሮችን የበለጠ የተወሳሰቡ ይሆናሉ። ሰው ችግሩን አምኖ የሚመጣው ይምጣ ብሎ እርዳታን መፈለግ ግን በሱሱ ዘልቆ ከሚመጣው ጉዳት አይብስም። በኋላ እግዚአብሄር ፍርድ ፊት ከመቅረብ ዛሬ ላይ በሰው ፍርድ ውስጥ ማለፉ የተሻለ ነው። 

ከፖርኖግራፊ ሱስ መውጫ መንገዶች 

ፖርኖግራፊ የሞራል ችግር ውድቀት ተብሎ በአብዛኛው ቢታይም ከዛ ባለፈ በዋነኝነት ከአዕምሮ ጋር የተያያዘ ችግር ነው። ስለ ፖርኖግራፊ ስንነጋገር ከላይ እንደተጠቀሰው አይምሮአችን እንዴት እንደሚሰራ መረዳቱ አስፋላጊ ነው። ለምሳሌ አንዲት እናት ልጅዋን በደረትዋ አስደግፋ በምታጠባበት ጊዜ አይምሮዋ ‘ኦክሲቶሲን’ የሚል ‘ኒውሮኬሚካል’ ይፈጥራል። ይህም ኬሚካል አንዲት እናት በውስጣዊ ስሜትዋ ከልጅዋ ጋር እንድትተሳሰር የሚያደርግ ሲሆን፤ በወሲብ ጊዜ ሰውነታችን የሚኖረው የኬሚካል ሁደትም ይህን ይመስላል። ፈጣሪ በሰውነታችን የሚለቀቀውን ይህን የኬሚካል ሁደት በባለትዳሮች መካከል የሚደረግ ወሲብን ተከትሎ ስሜታዊ ትስስር የመፍጠር አላማ ቢኖረውም፤ ከትዳር ውጭ በሆነ በተለያየ ወሲባዊ ድርጊት ውስጥ አሉታዊ ተፅዕኖ ይኖረዋል ።  ሰዎች ፖርኖግራፊ በሚጠቀሙበት ጊዜ የሚለቀቁት እነዚሁ የ’ኦክሲቶሲን’ ‘ኬሚካሎች’ ተመልካቹ ከሚመለከተው ምስል ጋር ስሜታዊ ትስስር እንዲኖረው ያደርጋል። በግለ ወሲብ ሱስም ውስጥ ያሉ ሰዎችም በእነዚህ ኬሚካሎች ከራሳቸው ጋር ትስስር ይፈጥራሉ።  በተደጋጋሚ የሚደረግ ማናቸውም ነገር በአይምሮ ላይ እንዳላቸው ተፅህኖ ሁሉ ፖርኖግራፊም የአይምሮአችንን ቅርፅ በመቀየር በፖርኖግራፊ እስራት ውስጥ መውደቅ ያስከትላል። ስለዚህ ስለፖርኖግራፊ እስራት መውጫ መንገዶች ስናወራ ወደ ሱሱ ሊመሩ የሚችሉ ነገሮችን፤ ተያያዥ ባህሪዎችን እና አመለካከቶችን አብረን ማንሳት ይኖርብናል። ከሁሉ ቀዳሚው ነገር ከላይ እንደጠቀስነው ችግሩ እንዳለ ማመን ነው። 

እንግዲህ ከፖርኖግራፊ ሱስ ለመውጣት የምትፈልጉ ወገኖች ከዚህ ቀጥሎ የቀረቡትን ተግባራዊ ነጥቦች ብትከተሉ ከእግዚአብሔር ፀጋ ጋር 100% ልትወጡ እንደምትችሉ አረጋግጥላቹሃለው። ይሄን ጽሁፍ ስታነቡ ወረቀትና እስኪብርቶ ይዛችሁ ለተቀመጡት ጥያቄውች በጽሁፍ መልስ እየሰጣቹ እለፉ። 

1. እግዚአብሔር እንደሚወዳቹ አውቃችሁ ንሰሐ ግቡ

በዚህ ሱስ ውስጥ የገቡ ሰዎች እግዚአብሔር እንደሚጠላቸውና እንደሚጸየፋቸው ያስባሉ። እንዲህ አይነቱ ሃሳብ ሰዎችን የሱሱ ባሪያ አድርጎ ለማኖር ሰይጣን ይጠቀምበታል። በፖርኖግራፊ ሀጢያት መውደቅን ተከትሎ ሰይጣን ሁልጊዜ እዛው ተብትቦ ሊያስቀረን ይጥራል። ይህም ራሳችንን እንድንጠላ፤ እግዚሐብሄር ለእኛ ግድ እንደማይለውና ሩቅ እንደሆነ እንድናስብ እና ተስፋ ቢስነት እንዲሰማን ሀሳባችንን በመያዝ ይተጋል። ሁሌም ቢሆን ውድቀትን ተከትሎ ዋና ጠላታችን ማን እንደሆነ ማወቁ ተገቢ ነው። በጥፋታችን ማዘናችን ተገቢ ቢሆንም እንደ ይሁዳ ወደ ከፋ እርምጃ የሚወስድ መሆን የለበትም። (ማቴ 27:4-5 ) ራሳችንን በመጥላት ውስጥ ዋዥቀን ራሳችንን የመቅጣት አዝማሚያው ቢኖረንም መውሰድ ያለብን እርምጃ በእግዚአብሄር ፊት እንደዳዊት በንስሃ መደፋት ነው (መዝ 51:1-10) በእኛ እና በሐጥያታችን መካከል ልዩነት አለ። እግዚአብሔር ኃጥያትን ይጠላል፤ ኃጥያተኛውን ግን ይወዳል። እናት የልጅዋ ልብስ ቢቆሽሽ ለልጅዋ ያላት ፍቅር እንደማይቀየር እግዚአብሔርም ለእኛ ያለው ፍቅር አይቀየርም። ከዚህ ህይወት ወጥታቹ ወደ እርሱ ለመምጣት ብትወስኑ እጆቹን ዘርግቶ ይቀበላችኋል። በቀራንዮ ላይ የፈሰሰው የኢየሱስ  ደም ከኃጥያታቹ ሁሉ እንደሚያነጻቹ አምናቹ በእግዚአብሔር ፊት ንስሐ ግቡ። “የልጁም የኢየሱስ ክርስቶስ ደም ከኃጢአት ሁሉ ያነጻናል” (1ዮሐ 1:7) የኢየሱስ ክርስቶስ ደም ስለ አለም ሁሉ ስለፈሰሰ በእግዚአብሔር ፊት ይቅር የማይባል ኃጥያት የለም።

2. አምናቹ ጸልዩ

የሰው ልጅ በራሱ ጥረት ከኃጥያት መውጣት አይችልም። የእግዚአብሔር ጸጋ ሲያግዘው ግን የማይቻለውን ችሎ በቅድስና አሸብርቆ መኖር ይቻላል። እስከ ዛሬ በግል ጥረታቹ ከዚህ ሱስ መውጣት ስላልቻላቹ ተስፋ ቆርጣቹ ሊሆን ይችላል። ጸጋው ግን ጣልቃ ገብቶ አዲስ ህይወት ሊሰጣችሁ ይችላል። ይህ ደግሞ የሚሆነው “እኔ ደካማ ስለሆንኩ የሚረዳኝ ጸጋ ይሰጠኝ” ብሎ በጸሎት እግዚአብሔርን በመለመን ነው። በፀሎት ትጉ (ኤፍ 6:18) መውጣት እንደሚቻል አለማመን በራሱ ሰንሰለት ነው። የእግዚአብሔር ጸጋ ታሪክን እንደሚቀይር ከዚህ ህይወት መውጣት እንደሚቻል እመኑ። ምክንያቱም ከኃጥያት አስወጥቶ ቅዱስ የሚያደርግ ሰዎችን ሁሉ የሚያድን የእግዚአብሔር ጸጋ ተገልጧልና። ( ቲቶ 2:11-13) 

3. ሀሳብን በሀሳብ ተዋጉ

የፖርኖግራፊ ኃጢያት ስርወ-መሰረቱ ሀሳብ አንደመሆኑ ሀሳብን ልንዋጋው የምንችለው በሌላ ሀሳብ በመተካት ብቻ ነው ። አዕምሮእችንን በእግዚብሄር ሀሳብ ለመሙላት ደግሞ ዕለት ዕለት የእግዚአብሄርን ቃል በማንበብ እና በፀሎት ጊዜ ማሳለፍ ያስፈልጋል። ደስታችንን በእግዚአብሄር ስናገኝ በሀጢያት የምናገኘውን ጊዜያዊ ደስታ እየተፀየፍን እንሄዳለን። 

4. ለምን እንደምታዩ እወቁ

አንዲት እህት ከ4አመት በፊት አስገድዶ መደፈር ደርሶባት ነበር። ለሊት ስትተኛ ያለፈችበት እየታወሳት ትጨነቅ ነበር። ከዚህ ስቃይ ማምለጫ ያደረገችው ፖርኖግራፊ መመልከት ነበር። ለዚህች እህት ፖርኖግራፊ መመልከት የችግሩ መገለጫ እንጂ ዋናው ችግሩ እንዳልነበር ነው። ከዚህች እህቴ ጋር ጊዜ ወስደንም ስናወራ አሰቃቂ ከሆነ ጉዳት በኋላ ሰዎች የሚኖራቸው የስነ ልቦና መቃወስ /Post Traumatic Stress Disorder/ እንዳለባት ማረጋገጥ ችያለሁ።

ፖርኖግራፊ መመልከት ሰዎች በህይወታቸው ያልፈቱት የውስጣዊ ችግር መገለጫ ሊሆን ይችላል። ጊዜ ወስዳቹ በሕይወታቹ የሚያስጨንቃችሁን ነገር፤ ያለፋችሁበትን ታሪክ ለመለየት ሞክሩ። ችግሩን በውስጣችንን ተጭኖ ለማስቀረት (repress) ለማድረግ መሞከር ወደ ባሰ ችግር ይወስዳልና ችግሩን ተጋፍጣቹ መፍትሄ ለመስጠት ሞክሩ።

5 .ቀስቃሽ ነገሮችን ለዩ።

ከዚህ በታች ያሉትን ጥያቄዎች ለራሳቹ መልሱ።

በብዛት ፖርኖግራፊ የምታዩት የትኛው ሰአት ላይ ነው?

ለመጨረሻ ጊዜ ፖርኖግራፊ ያያችሁት መቼ ነው?

ፖርኖግራፊ ከመመልከታቹ በፊት ምን አይነት ስሜት (mood) ላይ ነበራችሁ?

ቀስቃሽ ነገሮቻቹ ምንድን ናቸው? ስሜትን የሚያነሳሱ የሙዚቃ ክሊፖች ወይንስ ፊልሞች? አንዲት እህቴ ፖርኖግራፊ ይዘት ያላቸውን ነገሮች የምታገኘው ከፌስ ቡክ ላይ ነበር። ከዚህ ህይወትም ሙሉ ለሙሉ መውጣቷን እስክታረጋግጥ ድረስ ፌስቡክ መጠቀሟን አቆመች። ከዚህ በፊት የሰበሰባችሁት ፊልምና ማንኛውም ነገር አሁኑኑ አስወግዱ። ለዚህ ዓላማ የምታገኙአቸው ሰዎች ካሉ ግንኙነታቹን አቋርጡ።  ኢንተርኔት መጠቀም ማቆም ካለባቹ አድርጉት። ግድ መጠቀም ካለባችሁም ሰዎች በተሰበሰቡበት ቦታ ተጠቀሙ። ወይም እንደ ‘Covenant eyes’* ወይም ‘ X3watch’* ያሉ ፕሮግራሞችን ተጠቀሙ ከሕይወታቹ የሚበልጥ ምንም ነገር የለምና!

ወደ ፖርኖግራፊ የሚገፋፋቹ ጭንቀት ከሆነ ከጭንቀት መውጫ ሌሎች መንገዶችን ፍጠሩ። ስሙን ሳልጠቅስ ታሪኩን እንዳጋራ የፈቀደልኝን የአንድ ወንድም ሕይወት ላንሳ፤ “ከሚስቴ ጋር ባለን ህይወት ደስተኛ አይደለሁም። እቤት መሄዴን ሳስብ ጭንቀት ይወረኛል። መደበሪያዬ ፖርኖግራፊ ሆኖ ለዘመናት ኖርኩኝ። የትዳሬን ችግር መፍታቴ ከፖርኖግራፊ ሱስ አስመለጠኝ”።

የእናንተን ቀስቃሽ ነገርን ጻፉት።

6. ታገሉ!

ከዚህ ሱስ መውጣት ሂደት ነው። ለማቆም ከወሰናቹ በኋላ እንኳን መላልሳችሁ ልትወድቁ ወይም እስከ ዛሬ ያያችሁት ምስል ሀሳባችሁ ላይ እየመጣ ልትጨነቁ ትችላላቹ። ይሄ ማለት ከዚህ ህይወት አልተላቀቃችሁም ማለት አይደለም። ቡና ለረጅም ጊዜ ጠዋት መጠጣት የለመደ ሰው እንደሚያዛጋው ማለት ነው እንጂ! አዕምሮአችን ወደ ቀደመው ቦታ እስኪመለስ ከማንኛውም ሱስ ስንወጣ የምናልፍበት ጤናማ ሂደት ነው። ዋናው በጦርነቱ ተሸንፎ እጅ አለመስጠት ነው። ጸንታቹ ከታገላቹና የሚፈልገውን እስከነሳችሁት ድረስ ሱሱ በእናንተ ላይ ያለውን አቅም ያጣል። ከመገባችሁት ግን ያድግና ይውጣቹሃል።

7. ስሜቶቻችሁን ተቆጣጣሩ

ፖርኖግራፊ ማየት ሶስት ደረጃዎች አሉት። እነሱም ስሜት /Emotion/፣ ሐሳብ/Thought/ እና ተግባር/Action/ናቸው። ስሜት የምንለው የመጀመሪያው ደረጃ ጭንቀት፣ መከፋት ወይንም ፖርኖግራፊ የማየት ፍላጎት ሊሆን ይችላል። ይህን ተከትሎ ነው ፖርኖግራፊ የማየት ሐሳብ የሚመጣው። መጨረሻ ላይ ሁሉም ወደ ተግባር ይቀየራል። ስለዚህ ራሳችሁን መቆጣጠር የምትችሉት በሃሳብ ደረጃ ሳለ ሳይሆን ገና ስሜት ሲሰማቹ ነው። አንዲት እህቴ ‘እንዲህ አይነት ስሜት ሲሰማኝ ከቤት ወጥቼ መዝሙር እየሰማሁ የእግር ጉዞ ማድረግ እጀምራለሁ ይሄም በጣም ጠቅሞኛል’ ስትል ልምዷን አጋርታኛለች። አንድ ወንድሜ ደግሞ እንዲህ አይነት ስሜት ሲሰማው ስፖርት እንደሚሰራ አጫውቶኛል። ይህ ስሜት ሲሰማቹ ምን ብታደርጉ ጥሩ ነው? 3 ነገሮችን ጻፉና የሚስማማችሁን ነገር አድርጉ።

8. ብቸኝነትን አስወግዱ

ለረጅም ሰአት ብቻችሁን ላለመሆንና ጊዜያችሁን ከቤተሰብና ከወዳጆቻችሁ ጋር ለማሳለፍ ሞክሩ። በተቻለ መጠን ቀናችሁን በተሻለና ትርጉም ሊሰጥ በሚችል ነገር ላይ አውሉት። እንደ ስፖርት መስራት መጽሐፍትን ማንበብ ወደ ቤተ ክርስቲያን መሄድ ያሉ ልምዶችን አዳብሩ። እስኪ ከዛሬ ጀምሮ ልታዳብሩት የምትችሉት 5 ልምምዶችን ጻፉ።

9. ተስፋ አትቁረጡ

ከዚህ ህይወት ለመውጣት በምታደርጉት ጥረት ውስጥ መውደቅና መነሳት ሊያጋጥማቹ ይችላል። ተስፋ ሳትቆርጡ ከስህተታቹ ተምራችሁ እንደ አዲስ በብሩህ ተስፋ ነገን አሻግራቹ ተመልክቱ።

10. ግልጽ ሁኑ

ይሄን ጽሁፍ ሳዘጋጅ እስከዛሬ ድረስ በዚህ ሱስ የተጠቁና ያማከርኳቸውን ሰዎች ከዚህ ሱስ እንድትወጡ ያስቻላችሁን ነገር ግለፁልኝ ስል ጠይቄ ነበር። በሁሉም ውስጥ ያገኘሁት 2 ሀሳብ ነው። አንደኛው የእግዚአብሔር እርዳታ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በችግሩ ላይ በግልጽነት ማውራቴ የሚል ነበር። ብዙ ሰው በጉዳዩ ላይ ማውራት ስለሚያሳፍረው እርዳታም ለማግኘት ይቸገራል። ከዚህ ህይወት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለመውጣት ከፈለጋቹ ሊረዳቹ ለሚችል ለአንድ ሰው በግልጽ ችግራችሁን መናገር ይኖርባችኋል። በመናገራቹ ብቻ፤ ሚስጥር ያረጋችሁትን ነገር ወደ ብርሃን በማውጣጣቹ ይህ ኃጢያት በእናንተ ላይ ያለውን አቅም ያጣል። ስትደክሙ የሚያማክራችሁ ፤ መቆማችሁን ሁሌ ሚከታተል አንድ ሰው ማረጋቹሁ ፀንታችሁ እንድትቆሙ ብርታት ይሰጣችኋል። ይሄንን ምክር ሰጥቼው የተቀበለ አንድ ወንድም ችግሩን ለጓደኛው አካፈለው። መጥፎ ስሜት ሲሰማው ይደውልና እባክህን እየተቸገርኩ ስለሆነ ጸልይልኝ ይለዋል። ልታማክሯቸው የምትችሉ ሶስት ሰዎችን ጻፉና በማስተዋል እና በፀሎት ታግዛችሁ አንዱን ምረጡ።

ጽሁፌን በጌታችን ኢየሱስ ቃል ልደምድም።

እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ፥ ወደ እኔ ኑ፥ እኔም አሳርፋችኋለሁ”።ማቴ 11:28

ለጊዜው አበቃሁ። 

ዲያቆን ኤርሚያስ ኪሮስ


Download the series in PDF (166KB)


* Covenant Eyes እና X3 Watch፣ማንኛውንም ፖርኖግራፊ ነክ ምስሎች ወይንም ፅሁፎችን ብሎክ በማድረግ፣ ከዚህ ሱስ እንድንወጣ የሚረዱን፣ ለሞባይልና ለኮምፒውተር የተዘጋጁ የሶፍትዌር ፕሮግራሞች ናቸው። 


በፖርኖግራፊና ግለ ወሲብ/Masturbation/ ሱስ ተይዛቹ የምትጨነቁ ወገኖቻችን በማንኛውም ጊዜ ልንረዳቹ ዝግጁ ነን። በ+251945000005 ላይ በኢትዮጵያ ሰዓት አቆጣጠር ከጠዋቱ 4 ሰዓት ጀምሮ እስከ ምሽቱ 4 ሰዓት ድረስ ይደውሉልን። ከኢትዮጵያ ውጭ ከሆኑ በቫይበር፣ በቴሌግራም፣ በኢሞ፣ በዋትስአፕ እና በላይን ሊያገኙን ይችላሉ።

Last modified on %PM, %22 %545 %2018 %15:%Sep
Ermias Kiros

Ermias Kiros has a bachelors degree in theology and social anthropology, and he is currently doing his Masters in Counseling Psychology. Currently, he works as inspirational public speaker and counselor.

https://www.facebook.com/ermias.kiros.1

አንቀፅ 17፣ ነፃነት/ባርነት — ከአድዋ - ጎልጎታ

ይህ ታሪክ ከተፈፀመ እነሆ በዛሬዉ 122ኛ ዓመቱን ይዟል። ይህ ቀን ለአሁኗ ኢትዮጵያ ማንነቷን ያስጠበቀችበት፣ ከባርነት ራሷን ነፃ ያደረገችበት ቀን ነው። ከመ...

Misgana Kibret - avatar Misgana Kibret

ጨርሰው ያንብቡ

የእግዚአብሔርን የጸጋ ግምጃ ቤት ክፈቱ

ያጣችሁት ነገር ላይ ዓይንን እንደመጣል እምነትን የሚያደክም ነገር የለም።  እንደተረዳሁት ከሆነ ዓይኖቼን በቁሳዊ ማጣቶቼ ላይ ፣ በሌሉኝ ጥንካሬዎች እና በሌ...

Jon Bloom - avatar Jon Bloom

ጨርሰው ያንብቡ

 

The views and opinions expressed on Daily Injera are solely those of the original authors and our contributors. These views and opinions do not necessarily represent Daily Injera or our Staff.

Newsletter

Subscribe to our newsletter. Don’t miss any article, devotionals or wallpapers.

We do not spam!

You're automatically subscribed to bi-weekly articles and daily devotionals. You can customize your subscription settings here.