Thursday, 23 May 2024

በላብህ እደር

Posted On %AM, %01 %360 %2018 %10:%May Written by

በ9ኛው ክፍለ ዘመን የሰራተኛው መደብ የቀን የስራ ሰዓትን ስምንት ሰዓት ለማድረግ ትግል ያደርጉ ነበር። ለዚህም ምክንያት የሆናቸው በቀን አስር ብሎም አስራ-ስድስት ሰዓታትን ያለዕረፍት መስራታቸው፤ ብሎም ደህንነታቸውን ባልተጠበቀ መልኩ የነበረ መሆኑ እና ለብዙዎች ህልፈትና ጉዳት ምክንያትም የነበረ በመሆኑ ጭምር ነበር።በዚህም ወቅት የሶሻሊዝም ርዕዮት አዲስና በሰራተኛው መደብም ቀልብን ሳቢ ሆኖ የነበረበትም ወቅት ለመሆን ችሏል።ይህንንም (የሶሻሊዝም) ርዕዮት የሰራተኛው መደብ የበለጠ በማናፈስ ከካፒታሊዝም ርዕዮት የመውጣትና የሰራተኛውን መደብ ገዢነት የማረጋገጥ ፍላጎቱን መጠቀሚያ አረገው።በዚህም ትግል ከተቀዳጁት ቀደምት ድሎቻቸው መካከል እ.ኤ.አ በ1884 በሀገረ አሜሪካ በቺካጎ ግዛት ብሄራዊ ስብሰባ ላይ በህገ-መንግስቱ ላይ የቀን የስራ ሰዓትን ስምንት ሰዓት አድርጎ በ ሜይ 1 ታወጀ።

ይህን ታሪክ በማንበብ ላይ ሳለሁ አንድ ነገርን ታዘብኩ፤ በዚህ ቀን ላይ ስራ ተዘግቶ የሰራተኛ ቀን ተብሎ ይከበራል፤ ይገርማል! ሁላችን በዚህ ቀን ስራ አለመኖሩ አንዳች የደስታ ስሜትን ይፈጥርብናል።ለምን ግን ስል አሰብኩ፤ ውስጤም በሰአቱ ያሰበውን መለሰልኝ፤ አብዛኛው ህዝብ ስራውን አይወደውም። ኧረ እንደውም ስራም አይወድም። ስራን ከአዳም ጥፋት በኋላ የመጣ የጥፋቱ ዕዳ ይመስለዋል። ለዚህም ይመስለኛል ሰው የዕረፍት ቀኑን ቁጭ ብሎ 'ሚቆጥረው። በዚህም ቀን ላይ ስራ እንደሌለው እንጂ ቀኑን ለምን ምክንያት እንደምናስበው ማሰብ አይፈልግም።ለምን ግን ስራውን ጠላው? ብዙ ምክንያት ይነሳ ይሆናል፤ የሚከፈለው ደመወዝ በቂ አለመሆን፣ ከቅርብ አለቃው ጋር ያለው መጥፎ ግንኙነት፣ ሌላም ሌላም ልንል እንችላለን። እሱ ሳይሆን ነጥቤ ለምን ሰው ከስራው ይልቅ የዕረፍት ቀኑን እንዲቆጥር፣ ከስራው ይልቅ መቀመጡን እንዲያስብ ሆነ? እውነት ሰርቶ ስለደከመው ይሆንን? እጠይቃለሁ! 

ወደኋላም ብዙ ተጓዝኩና ሰው ሰርተህ ብላ የተባለው መቼ ይሆንን? ስራስ ከምን ጀመረ? ስል አሰብኩ ይህን የሚያስረዳኝን ፍለጋ ሳስብ ከማላቃት ሉሲና አርዲ ይልቅ የሰው ልጅ ጅማሮ እስከ መርሁ ተፅፎ ይገኝበታል ብዬ በማምነው በቅዱስ መጽሃፍ የሰውን የመጀመሪያውን የሰራተኝነት ትዕዛዝን ለማየት መግለጥ ጀመርኩ። በዘፍጥረት 3:17 ላይ ቆም ብዬ ማየት ጀመርኩ። እንዲህም የሚለውን የአምላክን ትዕዛዝ ለሰው ልጅ ሲያወርደው ተመለከትኩ “ምድር ከአንተ የተነሣ የተረገመች ትሁን፤ በህይወት ዘመንህም ሁሉ በድካም ከእርስዋ ትበላለህ” ይላል። ስራው የሚያዝናናው ሰው ያን ያህል ያለ አይመስለኝም፤ ለዚህም ምክንያቱ በዘመንህ ሁሉ በድካም ከእርስዋ ትበላለህ ስለተባለ ነው መሰለኝ። ግን ሰራተኛ መሆን ወይስ በስራው መድከሙ እና አለመርካቱ ነው? እውነት የሰው ልጅ ከፈጣሪው ትዕዛዝ በመውጣቱ የደረሰበት ቁጣ ነውን? የፍጥረት በኩር አዳም ያቺን የተረገመች ፍሬ ባይበላስ ኖሮ ምን መስሎ ይሆን የሚኖረው ስል አሰብኩ። እውነት የሰውን ልጅ ፈጣሪ ምንም የማይሰራ ቁጭ ብሎ የሚበላ አርጎ ነበር እንዴ የፈጠረው? ፈጣሪያችን ባህሪው ምን ነበር? ስል ጠየኩ። ይህንንም አይ ዘንድ ዘፍጥረት 1:1 ተመለከትኩ እንዲህ ይላል “በመጀመሪያ እግዚአብሄር ሰማይንና ምድርን ፈጠረ” ይላል። ፈጣሪያችንም ለካ ትጉ ሰራተኛ ነው። ከመግዛት ጀመረ አይልም፤ ወይም የሰውን ልጅ ፈጥሮ አሰራው አይልም ራሱ ከስራ ነው የጀመረው፤ ስለዚህ ፈጣሪ የሰውን ልጅ ሰራተኛ አርጎ ነበር የፈጠረው ማለት ነው።ፈጣሪም ከባህሪው ውስጥ ሰራተኝነት አንዱ ነው።

ደግሞም አዳም ከቁጣም በፊት ሰራተኛ ነበር፤ ከቁጣም በኋላ ያው ነው የቀጠለው። ነገር ግን ምድር ከመረገሟ የተነሳ ምድር ላይ ሰርቶ መኖር ድካም የሞላበት ሆነበት እንጂ።ሰው ሁሉ ሰራተኛ መሆን ከሰው ልጅ ውድቀት በኋላ የመጣ አርጎ ማሰቡ ተገቢም አይደለም።ይህቺ ምድር ፍሬን ትሰጠው ዘንድ ሰራተኛ መሆኑ ግድ ነው። ይህን ስል ግን እንደነዚህ ባሉ ቀናት ብሎም በሰንበት ለሰው ልጅም የተገባውን ዕረፍት ይወስድ ዘንድ የፈጣሪም ሃሳብ ነው።ዘፍጥረት 2:2 “እግዚአብሔርም የሰራውን ሥራ በሰባተኛው ቀን ፈጸመ፤ በሰባተኛውም ቀን ከሠራው ሁሉ ዐረፈ” ይላል። የሰው ልጅ እንደሚገባው ሰርቶ ያርፍ ዘንድ የተገባው እንደሆነ ይህ ክፍል ያመለክተናል፤ ጥፋቱ ሰው ከስራው ይልቅ እረፍቱን አጥብቆ መናፈቁ ላይ ነው።በየሰበብ አስባቡም ከስራው አንዳይቀር ሃላፊነት የሚሰማው እንዲሆን ይጠበቅበታል። በስራዎቹም ቀናት ላይ ለሰው ሲል እንዳይሰራም ይጠንቀቅ። በቆላስያስ 3:23 እንዲህ ይላል “ለሰው ሳይሆን ለጌታ እንደምታደርጉ፤ የምታደርጉትን ሁሉ በትጋት አድርጉት” ይላል። በስራችን ላይ መለገም ሀጢያትም ጭምር ነውና ይህን ቀን ስናስበው ቀኑ መልሶ እንዳይኮንነን እንትጋ። ባልሰራነው ስራ ምስጋናን ከመቀበል እንቆጠብ፤ በወር የምንወስደው ደመ-ወዝ የስራችን ውጤት ይሁን። ስራን ውሎ ለመግቢያ ሳይሆን ሀገር ትውልድን ለመስሪያነት ይዋል። ሳትሰራ መብላት፣ ባቋራጭ መክበርን አትናፍቅ። በላብህ እደር፣ ከማንም የማታንስ መሆንህን አውቀህ እነ እከሌ እዚህ የደረሱት አሰርተው ነው፣ የጊዜው ሰው ስለሆኑ ነው፣ ቤተሰቡ አውርሶት ነው እንጂማ ይሄን ሁሉ ከየት አመጡት በሚል የሰነፎች ወሬ ራስህን አትጥመድ፤ ይልቅ ስራና ከማንም እንደማታንስ አሳያቸው። ስራህ ጽድቅን የተሞላ ይሁን፤ ያለህን ይዘህ አመስጋኝ ሁን፤ ያኔ የታመንክለት አምላክ ቤትህ በበረከቱ ይሞላልሃል ያለህ ሲበቃህ ትመለከታለህ። ትጉ ሰራተኝነትን ከንብ ብርቱነትንና ህብረትን ደግሞ ከጉንዳን እንማርላቸው። 

ክብረት ይስጥልኝ!!

Last modified on %PM, %01 %716 %2018 %19:%May
Misgana Kibret

Misgana Kibret, a contributor writer at Daily Injera has BSC in Database Management and currently studies Christian Leadership. Misgana regularly writes on his personal blogs.

misganasview.blogspot.com

ምስጋና ለመስጠት 32 ምክንያቶች

እንግሊዛዊው ፓስተር እና የመጽሐፍ ቅዱስ ተንታኝ ማቲው ሄነሪ (1662-1714) ከመሞቱ 2 ዓመት በፊት ስለ ጸሎት መጽሐፍ ጽፎ ነበር። ለጸሎት የሚሆን መንገድ...

Donny Friederichsen - avatar Donny Friederichsen

ጨርሰው ያንብቡ

ወደ እግዚአብሔር መቅረብ (ክፍል 2)

ወደ እግዚአብሔር ከመቅረብ የሚከለክሉን ሦስት ነገሮች 1. ኩነኔ እና ኃፍረት  “እንግዲህ በእምነት ከጸደቅን በእግዚአብሔር ዘንድ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶ...

Michelle Zombos - avatar Michelle Zombos

ጨርሰው ያንብቡ

 

The views and opinions expressed on Daily Injera are solely those of the original authors and our contributors. These views and opinions do not necessarily represent Daily Injera or our Staff.

Newsletter

Subscribe to our newsletter. Don’t miss any article, devotionals or wallpapers.

We do not spam!

You're automatically subscribed to bi-weekly articles and daily devotionals. You can customize your subscription settings here.