Monday, 15 July 2024

ከታላቁ የወንጌል ሰባኪ ዶ/ር ቢሊ ግራሃም (1918-2018) ሕይወት የምንማራቸው 5 ነገሮች (በተለይ ለወጣቶች) Featured

Posted On %AM, %22 %916 %2018 %00:%Feb Written by

ታዋቂው አሜሪካዊ የወንጌል ሰባኪ ዊልያም ፍራንክሊን ግራሃም ወይም በአጭሩ ቢሊ ግራሃም በ99 አመታቸው ዜና እረፍታቸው በትላንትናው ዕለት (የካቲት 14) ማለዳ ከሳውዝ ካሮሊና ግዛት ከመኖርያ ቤታቸው ተሰምቷል። ይህ መረጃ እንደወጣ ሁለት ወዳጆቼ በሰአታት ልዩነት ደውለው ሲነግሩኝ እጅግ ነበር ያዘንኩት። ደግሞ በአካል አገኛቸው ዘንድ ምኞቴ እንደነበር ወዳጆቼ ስናገር ሰምተውኛል። እኔ በግሌ ከጽሁፍ ለጥቂት ወራት ርቄ የነበረ ቢሆንም የእርሳቸውን ሞት ስሰማ ግን ዝም ማለት አልሆነልኝም።

በዶ/ር ቢሊ ግራሃም ሞት የአለማችን መሪዎች እና ታዋቂ ሰዎች ከአሁኑ የአሜሪካ ፕሬዘደንት ዶናልድ ትራምፕ እስከ ቀድሞው ፕሬዘደንት ባራክ ኦባማ ድረስ የተለያዩ ሰዎች እንዲሁም የቤተ ክርስቲያን መሪዎች የተሰማቸውን ሃዘን እና ቢሊ ግራሃም በአለም ላይ ያሳደሩት መልካም ተጽዕኖ በማንሳት እያወደሷቸው ይገኛሉ።

በእ.ኤ.አ 1918 በኖርዝ ካሮሊና የተወለዱት ዶ/ር ቢሊ ግራሃም ጌታን እንደግል አዳናቸው የተቀበሉት እ.አ.አ በ1934 በ16 አመታቸው በድንኳን ውስጥ በተደረገ የመነቃቂያ ፕሮግራም ሲሆን በ1938 ለወንጌል አገልጋይነት ጥሪን ከእግዚአብሔር ተቀብለዋል። ከዚያም በቦብ ጆንስ ዩኒቨርሲቲ ብሎም በፈሎሪዳ ባይብል ኢንስቲትዩት ትምህርታቸውን ከወሰዱ በኋላ ከፍ ላለ ትምህርት ወደ ዊተን ኮሌጅ አቀኑ። ታዲያ በዚሁ በዊተን ኮሌጅ እያሉ ነው የቀጣይ የሕይወት ዘመን አጋራቸው የነበረችውን ሩት ቤልን (እ.አ.አ ከ1920-2007) የተተዋወቁት። ወንጌላዊ ቢሊ ግራሃም በደቡብ መጥምቃውያን ኮንቬንሽን (በአሜሪካ ትልቁ የወንጌላዊያን ቤተ ክርስቲያን) በወንጌል ሰባኪነት ተሹመው አገልግሎታቸውን ጀመሩ።

ወ/ዊ ቢሊ ግራሃም በ50 አመት አገልግሎታቸው 185 ሃገራት በመዘዋወር ከ200 ሚልዮን ለሚበልጡ ሰዎች የምስራቹን ወንጌል ሰብከዋል። LifeWay የተባለ ድርጅት እንዳጠናው በእርሳቸው አገልግሎት ከ 2.5 ሚልዮን ሰዎች በላይ ሰዎች ወደ ጌታ መጥተዋል። ከዚህም በላይ በኖሩበት ዘመን ሁሉ ወ/ዊ ቢሊግራሃም ከ2.2 ቢሊዮን በላይ የሆኑ ሰዎችን በተለያየ መንገድ በወንጌል ደርሰዋል። ይህም ብዙዎችን በወንጌል በመድረስ በታሪክ ታላቁ ወንጌላዊ ያሰኛቸዋል።እ.አ.አ. በ1960 በጃሆንሆይ ዘመን ወደ ኢትዮጵያ ምድር መጥተው ነበር። በሀይለስላሴ ስታዲዮም አስር ሺህ ህዝብ በተገኘበት ወንጌሉን ሰብከው ነበር። በራሳቸው እጅ የተጻፈው የግል ታሪካቸው እንደሚያስረዳውም ከሕዝቡ ግማሽ የሚደርሰው ወደ ኋላ ለምክር እና ለጸሎት ወደ ኋላ ቀርቶ ነበር።

ይህ ብቻም አይደለም በአሜሪካ ታሪክ ብዙ ፕሬዘደንቶችን በማገልገል ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛሉ። ለብዙ ፕሬዘደንቶች ወንጌልን በመስበክ ተጽእኖ ከመፍጠራቸው የተነሳ "የአሜሪካ መጋቢ" የሚል ስያሜን አግኝተዋል። በአንድ ወቅት የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዘደንት ጆርጅ ደብሊው ቡሽ ከመጠጥ እና ከሌሎች አላስፈላጊ ነገሮች የራቁት በቢሊ ግራሃም ምክር እንደሆነ ተናግረዋል።

ወ/ዊ ቢሊ ግራሃም ወንጌል ሰባኪነትን እንድወድ ያደረጉኝ ታላቅ የእግዚአብሔር ሰው ነበሩ። ያደግሁት እና ሙሉ ጊዜዬን ሰጥቼ ያገለገልሁት በመጥምቃዊት ቤተ ክርስቲያን እንደመሆኑ ወንጌላዊ ቢሊ ግራሃም ለእኔ ትልቅ መቀጣጠያ ነበሩ። የእርሳቸው 28 ደቂቃ ስብከት አንድ ስታዲየም የሚሞላ ሕዝብ ወደ ክርስቶስ ሲያመጣ ማየት ለእኔ ከምንም በላይ ቃሉ ዛሬም እንደሚሰራ ፣ መንፈስ ቅዱስ ዛሬም ሕይወትን እንደሚቀይር ያጸናልኝ ነበር። ከዚህም በላይ ቢሊ ግራሃም ለሁሉም ክርስቲያኖች ብዙ ትምህርት እንደሚሰጡ አምናለሁ።

እኔ በግሌ በተለይ የዚህ ዘመን ወጣት አገልጋዮች ከእርሳቸው ልንማራቸው እንችላለን ያልኳቸውን አምስት ነገሮች እንደሚከተለው ዘርዝሪያለሁ።

1. የወንጌል ሰባኪነትን

ከወንጌላዊው ምን እንማራለን? ወንጌል ሰባኪነትን! ዶ/ር ቢሊ ግራሃም ለነፍሳት መዳን የነበራቸው ልብ እጅግ የሚያስገርም ነበር። የወንጌል ጥሪ የተቀበሉበትን ወቅት ሲያስታውሱ ‹‹በመጋቢት 1938 በአንድ ምሽት ሰማዩት ትኩር ብዬ እመለከት ነበር። ውስጤን አንድ ሃይል ሲጫነኝ ተሰማኝ። ተንበርከኩ ፣ አለቀስኩ ‹ጌታ ሆይ የወንጌል ሰባኪ እንድሆን ከፈለግህ ይኸው እሆናለሁ!› ብዬ ጸለይኩ።›› 

ቢሊ ግራሃም የመጀመሪያ የወንጌል የሰበኩት 100 ሰዎች በተገኙበት ስበሰባ ላይ ነበር። በዚያ ስብከታቸውም 32ቱ ወደፊት ወጥተው ጌታን ለመቀበል ፈቃደኛ ሆነው ነበር። ቢሊ ግራሃም ከምንም በላይ የወንጌል ሰባኪነታቸውን ይወዱት ነበር። የእርሳቸውን መሞት የዘገቡ ታላላቅ አለማችን መገናኛ ብዙሃን ‹‹ታላቁ ወንጌላዊ ሞቱ›› ሲሉ ከስማቸው በፊት ‹‹ወንጌላዊ›› የምትለዋ መጠሪያ ትልቅ ትርጉም አላት። አለም በምን መጠሪያ ይሆን እኛን የሚያስታውሰን? (ግን በመጀመሪያ ያስታውሰናል ወይ?)

‹‹አንተ ግን በጊዜውም ያለ ጊዜውም ጽና፤ የወንጌል ሰባኪነትንም ስራህ አድርግ›› (2 ጢሞ 4፡2)

2. ለአንድነት መስራትን

ዶ/ር ቢሊ ግራሃም ከሚታወቁበት እንዱ እና ዋነኛው ባህሪያቸው ለአንድነት ባላቸው ጽኑ ፍላጎት ነው። ጥቁር እና ነጭ ተከፋፍሎ በነበረበት ጊዜ አንድነትን በመስበክ ከእነ ቄስ ዶ/ር ማርቲን ሉተር ኪንግ ጋር በጋራ የሰሩ ነበሩ። አለም በምዕራብ እና በምስራቅ ርዕዮት አለም ተከፍሎ በነበረበት በዚያ ዘመን ከሶቪየት ዩኒየን እስከ ኖርዝ ኮርያ በመሄድ ወንጌልን የሰበኩ የወንጌል አርበኛ ነበሩ። ከአራት መቶ አመታት በላይ የዘለቀውን የፕሮቴስታንቶች እጅግ ከመስመር ያለፈ መከፋፈል በመቃወም በወንጌላውያን አማኞች ስራ ለአንድነት በመጥራት ዓለምን ዳግም ለወንጌል የቀሰቀሱ የኢቫንጀሊዝም ዋነኛ አቀንቃኝ ነበሩ።

ወ/ዊ ቢሊ ግራሃም በገዛ ሃገራቸው እንኳ በፖለቲካ ላይ የአንድ ወገንን አቋም አያንጸባርቁም ነበር። ዛሬ ከሪፐብሊካኑ ጋር ከሆኑ ነገ ደግሞ ዴሞክራቱ ቤት ውስጥ  እራት ይበላሉ። ሁሉንም ለማቀራረብ የሚተጉ ሰው ነበሩ። የወንጌል ‹‹ክሩሴድ›› (በነገራችን ላይ ይህንን ቃል ለጀማ ስብከት የተጠቀሙት የመጀመሪያው ሰው እሳቸው ነበሩ) ሲያዘጋጁ እንኳን ካቶሊኮችንና ሌሎች ቤተ ክርስቲያን አባላትን በክብር እንግድነት ይጋብዙ ነበር። ለአንድነት የነበራቸው ፍላጎት ግን ዋጋ ሳያስከፍላቸው አላለፈም። በተለያዩ ጊዜያት የተለያየ ስም ተሰጥቷቸው አልፏል። የትጋታቸው ውጤት ግን ዛሬ ላይ በዘር እና በቆዳ ቀለም ክፍፍል ለምትታመሰው አሜሪካም ብትሆን በመከፋፈል ውስጥ ላለነው ለእኛው ክርስቲያኖች ትልቅ ትምህርት ሰጥቶ አልፏል። ዛሬ ማን ይሆን የሚያስከፍለውን ዋጋ በመክፈል ለአንድነት የሚተጋው?

3. ጨዋ ክርስቲያናዊ ኑሮን

ዶ/ር ቢሊ ግራሃም ከሚታወቁበት አንዱ ነገር ‹‹የቢሊ ግራሃም መመሪያ›› የሚባለው ነው። ‹‹የቢሊ ግራሃም መመሪያ›› በሌላኛው መጠሪያው ‹‹ሞዴስቶ ማኒፌስቶ›› በተለይ በተለይ ለታዋቂ ሰዎች እና ለብዙ የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች የጠቀመ መመሪያ ነው። ሕጉ ይህ ነው፡-

‹‹ ሚስትህ ካልሆነች ሴት ጋር በማንኛውም አጋጣሚ ብቻህን አብረህ አትታይ! ››

ወ/ዊ ቢሊ ግራሃም ይህንን መመሪያ ያወጡበት ምክንያት ለምንም መሰናከያ እንዳይሆኑ እና በእርሳቸው የጥንቃቄ ጉድለት የወንጌል አገልግሎታቸው ላይ ጥላሸት እንዳይኖረው ነው። ስለዚህም እስከ እለተ ሞታቸው ድረስ ይህንን መመሪያ ጠብቀው እንደኖሩ ይነገራል። ይህንን መመሪያ በቅርቡ የአሁኑ አሜሪካው ምክትል ፕሬዘደንት የሆኑት ማይክ ፔንስም እንደሚመሩበት ገልጸዋል። ቢሊ ግራሃም ከዚህም በዘለለ ከገንዘብ እና ከሕዝብ ጋራ ባላቸው ግንኙነት ግልፅ በመሆን የማይታሙ ነበሩ። ብዙዎች በዚህ ማንነታቸው ያደንቋቸዋል። ይህ ለዚህ ዘመን ላለን ወጣቶች ትልቅ ትምህርት ይመስለኛል። ግልጽነት እና ጥንቃቄ ባህላችን ማድረግ ይሁንልን።

4. የቡድን ስራን

ዶ/ር ቢሊ ግራሃም ግለሰባዊነትን የሚያራምዱ ሰው አልነበሩም። የቡድን ሰው ነበሩ። ከእርሳቸው ጋር ለ50 አመት አብረዋቸው ያገለገሉ ሰዎች አሉ። ወንጌላዊው በሕብረት ስራ ያምናሉ። ለምሳሌ እርሳቸው ሲሰብኩ የእርሳቸው ረዳት በመሆን ከትምህርት ቤት ጀምሮ ጓደኛቸው የነበረው ቲ ደብሊው ዊልሰን እንዲሁም መዝሙር በመዘመር ደግሞ ታዋቂው ጆርጅ ቤቨርሊ ሼ ከጎናቸው በመቆም ያግዟቸው ነበር። 

በአንድ ወቅት ለአሜሪካ ስላበረከቱት ትልቅ አገልግሎት ኮንግሬሽናል የወርቅ የክብር ሜዳልያ ሲሸለሙ ባደረጉት ንግግር ላይ ‹‹ይህ ሜዳልያ ለእኔ አይደለም። ይህ ሜዳልያ ለቡድናችን ነው። ከቡድኔ ጋር ለአርባ አምስት አመታት አብረን ነበርን። እያንዳንዱ አጠገቤ ባይኖሩ ሕይወቴ እንዲህ አይሆንም ነበር። ስለዚህም ላመሰግናቸው እወዳለሁ›› ብለው ነበር።

ስማ አንተ ኢትዮጵያዊ! በቡድን ስራ ታምናለህ? ወይስ ብቻህን ትሮጣለህ? ካሰብክብት ሩጫም የቡድን ስራ መሆን ይችላል። ካላመንህ እ.አ.አ 2008 ቤጂንግ ኦሎምፒክ ሃይሌ ፣ ስለሺን እና ቀነኒሳን መመልከት ነው። አገልግሎትም የቡድን ስራ ሲሆን ውጤታማ ይሆናል። 

5. ትህትናን

ሌላው የመጨረሻው ከቢሊ ግራሃም ሕይወት እንማረዋለን ብዬ ማስበው ትህትናን ነው። ቢሊ ግራሃም እጅግ በጣም ትሁት ሰው ነበሩ። በእያንዳንዱ ንግግራቸው ውስጥ ራሳቸውን እንዴት እንደ ተራ ሰው እንደሚመለከቱ ማስተዋል ይቻላል። በሕይወታቸው ማብቂያ ወራት በየቀኑ ለሚከታተላቸው ዶ/ር ‹‹እባክህን አንድ ውለታ ብቻ ዋልልኝ›› እንዳሉት ይነገራል። እርሱም ምን እንደሚፈልጉ ሲጠይቃቸው ‹‹ስሞት በቀብሬ ቀን የእኔን ስም አትጥሩ። ስለእኔ አታውሩ። ስለ ጌታዬ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ አውሩ›› 

ይህ ለወንጌል ያለ ፍቅር ብቻ አይደለም። ትልቅ ትህትናም ነው። ወንጌል ሰባኪያን ነን የሚሉ ብዙዎች ናቸው፤ ትህትና ግን የላቸውም። ዶ/ር ቢሊ ግራሃም በኖሩበት ዘመን ሁሉ ፍጹም አልነበሩም። በአደባባይም የሚታወቁ ስህተቶችን ሰርተዋል። ነገር ግን ትህትናቸው ስህተታቸውን ሁሉ ሸፍኖላቸዋል። የወንጌል ሰባኪያን ዛሬ ራሳችንን የምናየው እንዴት ነው? በታንክ እና በመትረየስ እንደሚታጀቡ የሃገር መሪዎች ወይስ ተራ እንደሆኑ እንደ እግዚአብሔር ወንጌል ሰባኪያን? ከቢሊ ግራሃም ትሀትናን እና ራስን ዝቅ አድርጎ ክርስቶስን ማሳየትን እንማራለን!

በመጨረሻም እኚህ የእግዚአብሔር ሰው ወደ ጌታ መሄደቸው እጅግ ቢያስከፋኝም (በተለይ ደግሞ ሳላገኛቸው!) አሁን በዚህ ጊዜ በሰማይ እየተደረገላቸው ያለውን አቀባበል ሳስበው እቀናለሁ። ‹‹ሰማይ እኔን እንዴት ይሆን የሚቀበለኝ?›› ብዬ እንድጠይቅ ይጋብዘኛል። ከቢሊ ግራሃም የምንማራቸው እነዚህን ብቻ አይደለም። ሌሎችም ብዙ ነገሮች አሉ:: እነርሱን በጊዜ ሂደት የማቀርብ ይሆናል። እስከዚያው ግን ከላይ እንዳየነው እንደዚህ ታላቅ ወንጌላዊ፣ ለብዙዎች ነፍስ ድነት እና ለአንድነት፣ በጨዋ ክርስቲያናዊ ኑሮ ፣ በቡድን ስራ ፣ በትህትና የጀመርነውን ሩጫ መሮጥ ይሁንልን! አሜን!

Last modified on %PM, %23 %669 %2018 %18:%Feb
Naol Befkadu

Naol Befkadu Kebede (BTh, student of MA in Ministry and Medical Doctorate student at AAU) is the founder and contributor of Lechristian Blog, an online ministry that aims to redeem cultures for the glory of God and to inspire and encourage believers for the completion Great Commission. Naol has authored an Amharic book titled "ተነሺ ፤ አብሪ" (2015) that motivates young believers for a meaningful and radical life. 

lechristian.blogspot.com

እግዚአብሔር እኔ ምን እንደሆንኩ ያስባል?

ሁላችንም ማን እንደሆንን ማወቅ እንፈልጋለን። እራሳችንን ፈልገን ለማግኘት እንጥራለን። ብዙዎቻችን የስብዕና ፈተናዎችን እና ሌላም ግምገማዎችን ወስደናል።  ይ...

Jonathan Parnell - avatar Jonathan Parnell

ጨርሰው ያንብቡ

 

The views and opinions expressed on Daily Injera are solely those of the original authors and our contributors. These views and opinions do not necessarily represent Daily Injera or our Staff.

Newsletter

Subscribe to our newsletter. Don’t miss any article, devotionals or wallpapers.

We do not spam!

You're automatically subscribed to bi-weekly articles and daily devotionals. You can customize your subscription settings here.