Tuesday, 22 October 2024

ሀዘን ላይ ያሉ ሰዎች በበዓል ጊዜ እንድታውቁላቸው የሚፈልጓቸው ነገሮች

Posted On %AM, %14 %334 %2017 %10:%Apr Written by

በአላት በደረሱ ቁጥር በሄድንበት ቦታ ሁሉ የምናገኛቸው ሰዎች ደስተኞች መሆን እንዳለብን ይነግሩናል። 

ይሁን እንጂ ወዳጆቻቸውን በቅርቡ ላጡ ሰዎች በዓሉ ሊደሰቱበት የሚገባቸው ነገር መሆኑ ቀርቶ እስኪያልፍ የሚጓጉት ነገር ሊሆንባቸው ይችላል። ለበአሉ ታላቅ ደስታን እና ትርጉምን መስጠት የሚችሉት ባህሎች እና ትዕይንቶች፣ የምንወደው ሰው ይህን ደስታ አብሮን ይካፈል ዘንድ አለመቻሉን በሚያስታውሱ አስጨናቂ ትውስታዎች ይዋጣሉ። ብዙዎች እነዚህ የበአል ወቅቶች እስኪያልፉ ድረስ ሊደበቁባቸው የሚችሉበት ጸጥ ያለ ቦታ ባገኝ ብለው ይመኛሉ።

ምንም እንኳን በሀዘን ላይ ባሉ ሰዎች ዙሪያ ያለን ሰዎች የደረሰባቸውን ሀዘን ልንጠግን ባንችልም በአል በደረሰ ወቅት በተለየ ስሜት ሀዘን ወደሚሰማቸው ሰዎች በመቅረብ ግን መጽናናትን ልናመጣ እንችላለን። በሀዘን ላይ ያሉ ሰዎች ቢያንስ 5 እውነቶችን እንድናውቅ ይፈልጋሉ።


ወዳጆቻቸውን በቅርቡ ላጡ ሰዎች በዓሉ ሊደሰቱበት የሚገባቸው ነገር መሆኑ ቀርቶ እስኪያልፍ የሚጓጉት ነገር ሊሆንባቸው ይችላል። 


1. በደስታ ቀኖች ጭምር የዚያ ሰው መጉደል ጎልቶ ሊሳልባቸው ይችላል።

ሴት ልጃችን ሆፕ ከሞተች ከአጭር ጊዜ በኋላ ለበአል ዕረፍት ወደ አንድ ቦታ ልንሄድ ዝግጅት እያደረግን እያለ ከአንድ ጓደኛዬ ጋር ያወራነው ትዝ ይለኛል። “በጣም ደስ የሚል ጊዜ ይሆናል!” አለች። በሙሉ ልቤ ከእርሷ ጋር መስማማት ይጠበቅብኝ እንደነበረ ተሰምቶኛል።

እንዴት ማስረዳት እንዳለብኝ ያልተረዳሁት ነገር የቤተሰባችሁን አንድ አባል ስታጡ ልዩ የሚባሉ ጊዜያት እንኳን በሚያም ሁኔታ ያልተሟሉ መሆናቸው ነው። አንድ ሰው ጎድሏል። ልዩ ቀኖች እና አስደሳች ትእይንቶች ሳይቀሩ በሀዘን የተለወሱ ናቸው። በምትሄዱበት ቦታ ሁሉ ይህ ሀዘን አብሯችሁ ይሄዳል።

2. ማሕበራዊ ሁኔታዎች ከባድ ናቸው

በሀዘን ላይ እያላችሁ ብዙ ሕዝብ ማየት ለምን እንደሚከብድ ሊገባኝ ባይችልም፣ በጣም ከባድ ነው። እጅግ ወሳኝ ነገር በተከሰተ ጊዜ አጭር ወሬ እንኳን ማድረግ ልንሸከመው ከምንችለው በላይ ነው። አዳዲስ ሰዎችን መተዋወቅ ስለቤተሰብ ጥያቄዎች እንዲነሱብን ማድረጉ አይቀሬ ነው። የትዳር አጋራችሁ ሲሞት በጥንዶች ወደተሞላ ክፍል ውስጥ ለብቻችሁ መግባት ወይም አንድ ልጅ ሞቶባችሁ በህጻናት ወደተሞላ ዝግጅት ስትሄዱ፤ ስላጣችሁት ነገር ነፍስን የሚያደቅቅ ማስታወሻ ሊሆንባችሁ ይችላል። 

በሀዘን ውስጥ ያሉን ሰዎች ወደ በዓል ዝግጅታችሁ ጠርታችሁ ከሆነ ለመመምጣት የሚከብዳቸው እንደሆነ ቢሰማቸውና መቅረት እንኳን ቢፈልጉ አሊያም ለአጭር ጊዜ ብቻ መቆየት ቢችሉ እንደምትረዷቸው አስታውቋቸው።

ወደ አንድ ዝግጅት ልትሄዱ ከሆነ፣ በሀዘን ላይ ያለው ሰው አብሯችሁ መሄድ ይችል እንደሆነ ጠይቁ። በዝግጅቱም ስፍራ ለእርዳታ ከአጠገባቸው አትለዩ። በማህበር በዓላት ላይ ሀዘን ላይ ያለ ሰው ሲገጥማችሁ ይወዱት ስለነበረ ስለሞተባቸው ሰው አሁንም እንደምታስቡ አሳውቋቸው። ከዚያ ሰውም ጋር የነበራቸውን ትውስታ ማውራት እንዲችሉ ጋብዟቸው። የሞተውን ሰው ስም ለመጥራት አትፍሩ። በሀዘን ላይ ላለው ሰው ነፍስ የማከሚያ ዘይት ነው።

3. የሩቅ ዘመድ የማይመች እና ቀላል ያልሆነ ስሜት ሊፈጥር ይችላል። 

ብዙውን ጊዜ ሀዘን የማይመችን ስሜት ይፈጥራል፤ በተለይም ቅርብ ከሆንናቸው ሰዎች ጋር። 

እኔ እና ባለቤቴ ልጆቻቸውን ላጡ ጥንዶች ወጣ ብለው መዝናናት የሚችሉበት ሽርሽር በሳምንቱ መጨረሻ ላይ እናዘጋጃለን። እናም ታዲያ በበዓላት ላይ ከቤተሰብ ጋር መሆን ከባድ የሚያደርገው በእነዚህ ጥንዶች ዘንድ የሚነሳው የወሬ ርዕስ ነው። አንዳንድ የቤተሰቡ አባላት ለረጅም ጊዜ በሀዘን ላይ እንደተቀመጡና የሀዘን ልብሳቸውን ደግሞ ማውለቅ አለባቸው ብለው እንደሚያስቡ ያውቃሉ። ሌሎች ደግሞ ስለሞተው ሰው ወሬ መጀመር ይፈልጋሉ፤ ነገር ግን እንዴት ማድረግ እንደሚችሉ እርግጣኛ አይደሉም። ብዙውን ጊዜ የሚሆነው የሞተው ሰው ስም ፈጽሞ አለመነሳት ነው። በሀዘን ላይ ላለው ሰው ታዲያ ከቤተሰቡ ውስጥ እንደተሰረዙ ሊሰማው ይችላል።

ወደ ቤተሰብ ሕብረት ለበዓሉ የሚሄድ በሀዘን ላይ ያለ ሰውን ታውቃላችሁ? ከቤተሰብ ጋር በሚሆኑ ጊዜ ስለሚጠብቁት ነገር ልትጠይቋቸው ትችላላችሁ። የሚወዱት ሰው በሆነ መንገድ እንዲታሰብ ፍላጎቱ ካላቸው፤ ላይደረግ የሚችልበትን አጋጣሚ ከመፍራት አንጻር፤ ቤተሰቦቼ እንዲሁ ያውቃሉ ብሎ ከመጠበቅ ይልቅ መጽናናትን ሊያመጣላቸው የሚችለውን ነገር በግልፅ ለቤተሰቦቻቸው መናገር ይችሉ ዘንድ ደብዳቤ እንዲጽፉ ልታግዟቸው ትችላላችሁ።

4. እንባ ችግር አይደለም

ለብዙዎቻችን ሀዘን ባልጠበቅናቸው ጊዜያት በሚመጡ እንባዎች ውስጥ ተገልጦ እናገኘዋለን። ሀዘን ላይ ያሉ ሰዎች በዙሪያቸው ያሉ ሰዎች እንባቸውን ሊፈታ እንደሚገባ ችግር እንደሚቆጥሩ ይሰማቸዋል። እንባ ማለት እነዚህ ሰዎች ሀዘናቸውን መሸከም አቅቷቸዋል ብለው እንደሚያስቡ ይሰማቸዋል። ነገር ግን የምንወደውን አንድ ሰው የማጣታችን ታላቅ ሀዘን በእንባ መውጣት ትርጉም የሚሰጥ ነገር ነው። እንባ ጠላታችን አይደለም። እንባ የእምነት ማጣትን አያመላክትም። እንባዎች የጉዳታችንን ጥልቅ ህመም አጥበው የሚያወጡ ከእግዚአብሔር የተሰጡ ስጦታዎች ናቸው።


እንባ ጠላታችን አይደለም። እንባ የእምነት ማጣትን አያመላክትም። እንባዎች የጉዳታችንን ጥልቅ ህመም አጥበው የሚያወጡ ከእግዚአብሔር የተሰጡ ስጦታዎች ናቸው።


ሀዘን ላይ ያሉ ሰዎች ከእናንተ ጋር ሲሆኑ በእንባቸው ሀፍረት ሊሰማቸው እንደማይገባ ማሳወቅ ብሎም ከእናንተ ጋር አብረው እንዲያለቅሱ ቦታ መስጠት ትልቅ ስጦታ ነው። የበለጠው ስጦታ ደግሞ ወዳጃቸውን ስላጡ የእራሳችሁን እንባ አውጥታችሁ ማልቀሳችሁ ነው። እንባችሁ የሞተውን ሰው ዋጋ ያንጸባርቃል። ይህንን ሰውም በመናፈቅ ውስጥ ብቻቸውን ላለመሆናቸው ማረጋገጫ ትሰጧቸዋላችሁ።

5. የገና በዓል መልካም እንደሚሆን ማሰብ ከባድ ሊሆን ይችላል።

“ኦ ቅዱስ ሌት” በሚለው መዝሙር ላይ “ግሩም ተስፋ ነፍሳችንን የሚያረካ ደስ ይበለን” ብለን እንዘምራለን። በዙሪያችሁ የሚገኙ ሀዘን ላይ ያሉ ሰዎች በዚህ ዓለም ውስጥ የሕይወት እና ሞት አድካሚነት ይሰማቸዋል በዙሪያቸውም ያሉ ሰዎች እንዴት ሀሴትን ማድረግ እንደቻሉ ያስገርማቸዋል። የክርስቶስ እውነተኛነት ወደ ብቸኝነታቸው እና ሀዘናቸው ዘልቆ መግባት እጅግ ሚፈልገት ነገር ነው። ልንሰብካቸው ባንፈልግም እራሱ እግዚአብሔር ነጻ ሊያወጣን በክርስቶስ መምጣቱ ውሰጥ ያለውን ደስታ እና መጽናናት ለማካፈል ግን አጋጣሚዎቹን ሁሉ እንመለከታለን።

በእንጨት ግርግም ውስጥ የጀመረው የኢየሱስ ሕይወት በእንጨት መስቀል ላይ ያበቃል። ይሁን እንጂ ጣዕም ያጣ ትርጉም የለሽ ሞት አይደለም። በአዲስ ትንሳኤ ሕይወት የሚቀጥል ሞትን የሚያሸንፍ ሞት ነበር። የዕብራውያን ጸሐፊ ሲያብራራ “እንግዲህ ልጆቹ በሥጋና በደም ስለሚካፈሉ፥ እርሱ ደግሞ በሞት ላይ ሥልጣን ያለውን በሞት እንዲሽር፥ ይኸውም ዲያብሎስ ነው፥ በሕይወታቸውም ሁሉ ስለ ሞት ፍርሃት በባርነት ይታሰሩ የነበሩትን ሁሉ ነጻ እንዲያወጣ፥ በሥጋና በደም እንዲሁ ተካፈለ።” (ዕብራውያን 2፡14-15) ሞት ብዙ ሀዘንን ለማምጣት አሁን ያለው ኃይል ለዘላለም እንዲህ ሆኖ አይቀጥልም። ክርስቶስ መጀመሪያ በመጣ ጊዜ ሞትን ሲያሸንፍ የጀመረው ሥራ በዳግም መምጣቱ ወደ ሙሉነት ይደርሳል።

በልደት ጊዜ ትልቁ ተስፋችን በዚህም ወቅት ሀዘን ላይ ላሉት ይህን ተስፋ ለማካፈል ተስፋችን ይህ ነው፤ እርሱም ከእዚህ አልፎ አዲስ እና ታላቅ ማለዳ መኖሩ ነው። ሕጻን ሆኖ የመጣው  በእኛም ምትክ በመስቀል ላይ የሞተው ክርስቶስ አንድ ቀን መንግሥቱን ሊጠቀልል ይመጣል። ይህንንም ሲያደርግ “እንባዎችንም ሁሉ ከዓይኖቻቸው ያብሳል፥ ሞትም ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፥ ኀዘንም ቢሆን ወይም ጩኸት ወይም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፥ የቀደመው ሥርዓት አልፎአልና ብሎ ሲናገር ሰማሁ።” (ራዕይ 21፡4)

 

Originally Posted at DesiringGod.org, Translated by Joshua Terefe


Last modified on %PM, %13 %643 %2017 %17:%Sep
Nancy Guthrie

Nancy Guthrie offers companionship and biblical insight to the grieving through Respite Retreatsthat she and her husband, David, host for couples who have faced the death of a child, through the GriefShare video series, and through books such as What Grieving People Wish You Knew About What Really Helps (and What Really Hurts).

www.nancyguthrie.com/

የሚያበረቱ 10 የመፅሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች

በመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ጥናት የምናሳልፈው ጊዜ ውድ እና ያልባከነ ጊዜ ነው። ረጃጅም ክፍሎችን እያጠናችሁ ቢሆን ወይንም ለአንድ ኃጢያት የሚሆን የውጊያ ጥቅስ አ...

David Mathis - avatar David Mathis

ጨርሰው ያንብቡ

ጣፋጭ ወይንስ መራር ቅድስና?

ጄሪድ ዊልሰን በ አንድ መጽሐፉ ላይ ሲጽፍ “ቅድስና እንድታጉረመርሙ ካደረጋችሁ እያደረጋችሁት ያለው ነገር ልክ አይደለም” ይላል። 

Tony Reinke - avatar Tony Reinke

ጨርሰው ያንብቡ

 

The views and opinions expressed on Daily Injera are solely those of the original authors and our contributors. These views and opinions do not necessarily represent Daily Injera or our Staff.

Newsletter

Subscribe to our newsletter. Don’t miss any article, devotionals or wallpapers.

We do not spam!

You're automatically subscribed to bi-weekly articles and daily devotionals. You can customize your subscription settings here.