ወዲያውኑም አንድ ቃል ወደ ውስጤ መጣ። ነህምያ እና ሕዝቡ ኢየሩሳሌምን እንደገና መስራት እንደጀመሩ እነሳናባላጥ በሰሙ ጊዜ እንዲህ ብለዉ ተሳለቁባቸው “እነዚህ ደካማ አይሁድ ምን እያደረጉ ነው? ቅጥራቸውን መልሰው ሊሰሩ ነውን? መስዋዕት ሊያቀርቡ ነውን? በአንዲት ጀንበር ሠርተው ሊጨርሱ ነውን? እንደዚያ ተቃጥሎ የፍርስራሽ ክምር የሆነውን ድንጋይ ነፍስ ሊዘሩበት ይችላሉን?” ነህምያ 4፡2።
በርግጥም ከተማይቱ የፈረሰችበትን መጠን ላየ ሰው ቅጥሩ ሊታደስ ከተማይቱም እንደገና ልትታነፅ ትችላለች ብሎ ማሰብ ዘበት ነበር። በእግዚአብሔር ዘንድ ግን እንዲህ አልነበረም። እግዚያብሔራዊው መልስ ’አዎ ይቻላል‘ ሆነ። ለኔም በጊዜው የመጣልኝ መልስ ‘ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር የለምና አዎ ተቃጥሎ የፍርስራሽ ክምር የሆነው ድንጋይ ነፍስ ሊዘራበት ይችላል፣ አዎ ተስፋ የተቆረጠበት ነገር እንደገና ሊታደስ ይችላል’ የሚል ነው።
ዛሬ በሚያጋጥሙን ነገሮች ልባችን ዝሎና ተስፋ ቆርጠን ወደኋላ እንዳንመለስ እግዚአብሔር የገባልንን እንዲህ ያለውን ህያው ተስፋ አጥብቀን እንያዝ። በዙሪያችን ያለው ነገር ሁሉ ተስፋ የሚያስቆርጥ ቢሆንም እንኳን ይህ በእግዚአብሔር ላይ ተስፋ እንድንቆርጥ በቂ ምክንያት አይደለም። በእውነት እግዚአብሔር ከአእምሮአችን በላይ ትልቅ ነው፣ ለእኛም የገባው ተስፋ በሰው አእምሮ ከመገመትና ከመወሰን ያልፋል። ‘ነፍሴ ሆይ ለምን ትተክዢያለሽ? ለምንስ በውስጤ ትታወኪያለሽ? ተስፋሽን በአምላክሽ ላይ አድርጊ አዳኜና አምላኬን ገና አመሰግነዋለሁና’ መዝሙር 42፡5-6።