ቀድሞ ለእግዚአብሔር ከሚሆን ማንኛውም አይነት ፍቅር ሞተን ግራ ከሚያጋባው ዕውርነታችን ስር ተቀብረን ነበር (ኤፌሶን 2፡1) ፤ ነገር ግን እግዚአብሔር . . . ። ቀድሞ ለእራሳችን ክብር እና የራሳችን ጌታ ለመሆን ባለን ምኞት ተታልለን ነበር፤ ቀድሞ በአየር ላይ ሥልጣን ባለው አለቃ ሳናውቅ እንመራ ነበር (ኤፌሶን 2፡2) ነገር ግን እግዚአብሔር . . . ። ቀድሞ በሥጋችን እና በአዕምሮአችን የስሜት ማዕበል እንግልት እየተነዳን ለሥጋችን ምኞት ተገዢዎች ነበርን (ኤፌሶን 2፡3) ነገር ግን እግዚአብሔር . . . ። ቀድሞ የእግዚአብሔር ጠላቶች ነበርን (ሮሜ 5፡10) እንጠላው ነበር (ሮሜ 1፡30) የቁጣ ልጆች ነበርን። ነገር ግን እግዚአብሔር . . . ።
ነገር ግን እግዚአብሔር በምሕረቱ ባለ ጠጋ ስለ ሆነ ከአዕምሮ በላይ የሆነ ፍቅሩን ያሳይ ዘንድ ከእግዚአብሔር ተለይተን የሞተነውን፣ እግዚአብሔርን የማንፈልገውን፣ ከእግዚአብሔር ጋር የምንፎካከረውን፣ እግዚአብሔርን የምንጠላውን አጥንታቸው የደረቁ የቁጣ ልጆችን “በሕይወት ኑሩ” (ሕዝቅአል 37፡5) አለን። ለእውነተኛ ውበት፣ ለእውነተኛ ክብር፣ ለእውነተኛ ተስፋ፣ ለእውነተኛ ደስታ እና ፍስሐ ኑሩ አለን! ለእግዚአብሔር ኑሩ አለን (ገላትያ 2፡19) እናም ለዘለዓለም ኑሩ አለን (ዮሐንስ 6፡58)!
ይህንንም ያሳካው ከእግዚአብሔር ተለይተን እንድንሞት ያደረገውን፣ እግዚአብሔርን እንዳንፈልግ የሚያደርገውን፣ ከእግዚአብሔር ጋር እንድንፎካከር የሚያደርገውን፣ እግዚአብሔርን እንድንጠላ የሚያደርገውን፣ የእግዚአብሔርን ቁጣ የሚያስነሳውን ይህን ኃጢያታችንን ሕይወት በሆነው ልጁ ላይ (ዮሐንስ 14፡6) አድርጎ ገደለው (ሮሜ 5፡8)። ስለዚህ እኛ በእርሱ ሆነን የእግዚአብሔር ጽድቅ እንሆን ዘንድ ኃጢያትን የማያውቀው እርሱ — ጻድቁን ለኃጢያተኞቹ — ስለእኛ፤ የእኛ ኃጢያታችን ሆነልን (2 ቆሮንቶስ 5፡21፤ 1 ጴጥሮስ 3፡18)። ለዘለአለም መኖር እንችል ዘንድ ይህን አደረገ (ዮሐንስ 3፡16) ።
እነዚህ “ነገር ግን እግዚአብሔር” የሚሉ ሦስት ቃላት በእግዚአብሔር ጸጋ ብቻ እንደዳንን ይነግሩናል። የሞቱ የቁጣ ልጆች በሕይወት ያሉ የእግዚአብሔር ልጆች ብቻ ሳይሆን የሆኑት ለእርሱም ነው።
በእነዚህ ሦስት ቃላት ፌሽታን አድርጉ። አሁን ካላችሁበትና አስክትሞቱ ባላው ጊዜ ውስጥ የሚፈጠርን ጣፋጭ ሆነ መራራ ክስተት እግዚአብሔር ለበጎ ነገር ይቀይረዋል። (ሮሜ 8፡28) ወደፊትም በእርሱ ዘንድ ባለው ዘላለማዊ ሕይወታችሁ የምታሳልፉት የከበረ ደስታ (መዝሙር 16፡11) “ነገር ግን እግዚአብሔር” ከሚሉት ከእነዚህ ሦስት ቃላት የሆነ ነው።
Originally Posted at DesiringGod.org, Translated by Joshua Terefe