Monday, 15 July 2024

የተበታተነው ህልማችሁ እና የተናጋው እምነታችሁ

Posted On %PM, %09 %844 %2016 %22:%Dec Written by

አንዳንድ ጊዜ ህልሞቼ በሚበታተኑበት ወቅት እምነቴ ደግሞ ይርዳል።

በመከራዎቼ መሀል እግዚአብሔር የት ነው ስል አስባለሁ። መገኘቱ አይሰማኝም። ፍርሃት እና ብቸኝነት ይሰማኛል። እምነቴ ይናጋል።

ለረጅም ጊዜ ያመንኩትን እጠራጠራለሁ። በተለይ በፊት የነበረኝ ልምድ ተስፋ ከማደርጋቸው ነገሮች ጋር አልገጥም ሲለኝ እውነታው የቱ ይሆን ስል አስባለሁ።

የእምነቴ መናጋት በጥልቅ ያሳስበኛል። የእግዚአብሔርን መልካምነት ቀምሻለሁ ፤ ከእርሱም ጋር ቅርብ የሆነ ህብረትን አጣጥሜአለሁ ፤ ከ ሩህሩህ እንክብካቤው በታችም አርፌአለሁ። ኃይሉንም ፍቅሩንም አውቄአለሁ። ይሁን እንጂ በመከራዎቼ መሀል ጥያቄዎች እንጂ ምንም መልስ የለኝም።

መጥምቁ ዮሐንስ በእስር በነበረበት ጊዜ ይህ ትግል ገብቶት ነበር። ከማንም ሰው በላይ ኢየሱስ ማን እንደነበረ ያውቅ ነበር። በማህጸን እንኳ ሆኖ ባልተወለደው አዳኝ መገኘት ፊት በነበረ ጊዜ በደስታ ዘሎ ነበረ። ኢየሱስ አገልግሎቱን በጀመረበት ወቅት ፤ ገና ምንም ተአምራትን ሳያደርግ በፊት “እነሆ የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ” (ዮሐንስ 1፡29) ሲል አውጆ ነበር። ኢየሱስን አጥምቆት የእግዚአብሔርም መንፈስ በላዩ ሲወርድ አይቶ በእርግጥም የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ መስክሮ ነበር።  

ይሁን እንጂ የኢየሱስ አገልግሎት ከፍተኛ ደረጃ ላይ በደረሰበት ወቅት፤ “ዮሐንስ በወህኒ ሳለ የክርስቶስን ሥራ ሰምቶ ከደቀ መዛሙርቱ ሁለት ላከና። ‘የሚመጣው አንተ ነህን? ወይስ ሌላ እንጠብቅ?’” (ማቴዎስ 11፡2-3) ብሎ ጠየቀ።

ኢየሱስ መሲሑ እንደነበረ ዮሐንስ እርግጠኛ ነበር። ኢየሱስ ተአምራትን በማድረግ መለኮትነቱን የበለጠ ቢያስረግጥም ዮሐንስ ግን እውነታው የቱ እንደሆነ ሲጠራጠር ነበር።

ለምን?

ያልተሟሉ ተስፋዎች

ዮሐንስ ከመጽሐፍ ቅዱስ የሚያውቀው ለዕውራን ማየትን የሰጠ ፣ ሽባዎችን እንዲራመዱ ያደረገ ፣ ለድሆችም የምስራቹን ዜና የሰበከ በኢሳያስ 61፡1 እንደተነገረው ትንቢት በእስር ያሉትንም መፈታትን እንደሚሰጣቸው ነው። ነገር ግን ኢየሱስ ለዮሐንስ ይህንን አላደረገለትም።

ምንአልባት በዚህን ጊዜ ዮሐንስ የሚያውቀውን ተጠራጥሯል። በእርግጥም ኢየሱስ መሲሑ ከሆነ፣ በምድራዊ መንግስቱ ውስጥ ቦታ ሊኖረው እንደሚችል ዮሐንስ ሊያስብ ይችል ነበር። በምድረበዳ ለጌታ መንገድን በማዘጋጀት በታላቅ የአገልግሎት ጥሪ ጀምሮ ህይወቱ እና አገልግሎቱ ግን በትንሽዬ የእስር ቤት ክፍል ውስጥ ያበቃሉ ብሎ ሊጠብቅ አይችልም ነበር። በተጨማሪም ዮሐንስ ፤ መሲሑ ሊጠፋ በማይችል ዕሳት ፣ በፍርድ ፣ በኃይል እንደሚመጣ ሰብኮ ነበር። ይሄ ሁሉ በእርሱ የሕይወት ዘመን እንደሚሆን ሳይጠብቅ አይቀርም።

እነዚህ ሁሉ ተስፋዎች ግን ከእውነታው ጋር አልገጠሙም። ምንአልባት ይሄ ዮሐንስን እንዲጠራጠር ሳያደርገው አልቀረም። ያልተፈጸሙ ተስፋዎች ብዙውን ጊዜ የዚህ ዓይነት ምላሽን በውስጤ ያጭራሉ። በተለይ ደግሞ ታማኝ በሆንኩባቸው ወቅቶች።

ኢየሱስ ስለዮሐንስ ጥርጣሬ አልፈረደበትም። ይልቁንም ከዮሐንስ የበለጠ ማንም ኖሮ እንደማያውቅ ተናግሮ ነበር። ዮሐንስ ጥያቄዎቹን ለምን እየጠየቀ እንዳለ ይገባዋል። ኢየሱስም የሰጠው ምላሽ ደግሞ ዮሐንስ ቀድሞ የሚያውቀውን የሚያጠናክር ፤ ኢየሱስ መሲሑ መሆኑን ነው።  

በተመሳሳይ ጊዜ ደግሞ የዮሐንስ አገልግሎት እንዳበቃ ኢየሱስ ያውቅ ነበር። በዕብራውያን 11 ላይ እንዳሉት ቅዱሳን ከሩቅ ተሳልሟቸው ያልፋል እንጂ ሁሉም የእግዚአብሔር ተስፋዎች ለዮሐንስ አይደርሱትም ነበር። ከኢየሱስ ጋር አብሮ አያገለግልም ወይንም የእግዚአብሔርን መንግስት መፈጸም አያይም። አንድ ቀን ግን ያያል። አንድ ቀን በእግዚአብሔር ድንቅ ዕቅድ ውስጥ ያለውን ግሩም ስፍራ ያያል። የአሮጌው ኪዳን የመጨረሻ ነብይ የሆነው እርሱን ዓለም ኢየሱስን እንድትቀበል እንዲያዘጋጃቸው እግዚአብሔር እንዴት እንደተጠቀመበት ያያል።

የዚያን ጊዜ ዮሐንስ ሐሴትን ያደርጋል።

አሁን ግን ዮሐንስ ፤ መሲሑ ለህይወቱ ያቀደውን ዕቅድ መቀበል አለበት። እኛ ካሰብናቸው እቅዶች የተለየ ዕቅድ። እውነት ነው ብሎ በሚያውቀው ነገር ላይ ሊመላለስ እንጂ ሁኔታዎቹ ላይ ተተክሎ መቅረት የለበትም። እግዚአብሔር ማን እንደሆነ ሊያስታውስ እና  ከጨለማው እስር ቤት ውስጥ ሆኖ ሊያምነው ይገባል።

ለኔም እንዲሁ ነው።

ዕቅዶቻችሁ ሲፈራርሱ

ዕቅዶቼ ሲፈራርሱና እግዚአብሔር ከህልሞቼ አርቆ በሚወስደኝ ጊዜ በጥልቅ ጥበቡ ላይ መታመን አለብኝ። የመከራ ጽዋዬ ሊይዘው ከሚችለው በላይ የሆነ ሲመስል በማይለካው ፍቅሩ ላይ ላርፍ ያስፈልጋል። ህይወቴ ከቁጥጥር ውጪ እየዞረ ያለ ቢመስል የእግዚአብሔርን ሉአላዊነት ላስታውስ ያስፈልገኛል።

ምን እየሆነ እንዳለ ላይገባኝ ይችላል። ነገር ግን እርሱን ማዋራት ላቆም አልችልም። ወይንም በፍርኃት ከእርሱ ዘወር ልል አልችልም። ማድረግ ያለብኝ ወደ ኢየሱስ ሄጄ አለማመኔን መናገር እና እንዳይ እንዲረዳኝ መጠየቅ ነው።

የዮሐንስ ጥርጣሬዎች ከእኔ ጋር አንድ ዓይነት ናቸው። በእርግጥ እግዚአብሔር ስለእራሱ የሚናገረውን እንደሆነ አስባለሁ። ሁሉም ነገር በቁጥጥሩ ስር እንደሆነ አስባለሁ። የእውነት ይወደኝ እንደሆነ አስባለሁ።

በጥርጣሬ ውስጥ በምሆንበት ጊዜ፣ እግዚአብሔር ዮሐንስን እንደጠራው ሁሉ እውነት ናቸው ብዬ የማውቃቸውን እንዳምን ይጠራኛል። ከመጽሐፍ ቅዱስ እና ከህይወቴ ያየኋቸውን መሠረታዊ መርሆችን እንዳምን ይጠራኛል። እግዚአብሔር ሉአላዊ እንደሆነ። ፍቅር እንደሆነ። ጠቢብ እንደሆነ። ከፍቃዱ ውጪ አንድ ድንቢጥ እንኳን መሬት እንደማይወድቅ እንዳምን ይጠራኛል።

እዚህ ባለኝ ህይወት እግዚአብሔር የሚገጥሙኝን መከራዎች እንዴት እየተጠቀመባቸው እንዳለ አላውቅም። ነገር ግን አንድ ቀን ደስ እሰኝባቸዋለሁ። አሁን ላደርግ የምችለው ሽባዎችን እንዲራመዱ ፣ ዕውሮችን እንዲያዩ ያደረገውን ፣ ከእርሱም ጋር ዘላለምን እንዳሳልፍ በመስቀል ላይ የሞተውን ለእኔ ከሁሉ የተሻለ ነገር መሆኑን ማመን ነው።  

ማሰሪያው እምነት ነው። በየጊዜው የሚለዋወጡትን ሁኔታዎቼን አምናቸዋለሁ? ወይንስ የማይለወዋወጠውን እግዚአብሔርን አምነዋለሁ?

በጽኑው ዐለት በክርስቶስ ላይ እቆማለሁ። ቀሪው መሬት ግን የሚያሰጥም አሸዋ ነው።


Recommended read:

 

(የቀረፁኝ ጠባሳዎች)

እግዚአብሔር በስቃይ ውስጥ እንዴት ይገኛኘናል


 Originally Posted at DesiringGod.org, Translated by Joshua Terefe


 

Last modified on %PM, %10 %916 %2016 %23:%Dec
Vaneetha Rendall Risner

Vaneetha Rendall Risner is a freelance writer and a regular contributor to Desiring God. She blogs at danceintherain.com, although she doesn’t like rain and has no sense of rhythm. Vaneetha is married to Joel and has two daughters, Katie and Kristi. She and Joel live in Raleigh, North Carolina. Vaneetha is the author of the new book The Scars That Have Shaped Me: How God Meets Us in Suffering.

የእግዚአብሔርን የጸጋ ግምጃ ቤት ክፈቱ

ያጣችሁት ነገር ላይ ዓይንን እንደመጣል እምነትን የሚያደክም ነገር የለም።  እንደተረዳሁት ከሆነ ዓይኖቼን በቁሳዊ ማጣቶቼ ላይ ፣ በሌሉኝ ጥንካሬዎች እና በሌ...

Jon Bloom - avatar Jon Bloom

ጨርሰው ያንብቡ

ደስታችሁ ያረፈው በክርስቶስ ጽድቅ ላይ ነው

እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር እንደሆነ መቶ በመቶ ብታምኑ ምን የሚሆን ይመስላችኋል? እንደተቀበላችሁ ብቻ ሳይሆን በክርስቶስ ማንነት እና ሥራ ምክንያት ሙሉ ለሙሉ...

David Mathis - avatar David Mathis

ጨርሰው ያንብቡ

 

The views and opinions expressed on Daily Injera are solely those of the original authors and our contributors. These views and opinions do not necessarily represent Daily Injera or our Staff.

Newsletter

Subscribe to our newsletter. Don’t miss any article, devotionals or wallpapers.

We do not spam!

You're automatically subscribed to bi-weekly articles and daily devotionals. You can customize your subscription settings here.