Monday, 15 July 2024

መጽሐፍ ቅዱሳችንን ችላ ምንልባቸው ምክንያቶች

Posted On %AM, %11 %041 %2016 %03:%Oct Written by

የእያንዳንዱ ክርስቲያን መጽሐፍ ቅዱስ ከመነበብ ብዛት ያረጀ፤ በየቦታው የተሰመረበት፤ በተለያዩ ቀለማት የተፃፉ መንፈሳዊ ሃሳቦችን የያዘ ማስታወሻ አብሮት ያለ ደግሞ ይመስለናል። ይህ ግን በአብዛኛው ልክ አይደለም። ብዙ ክርስቲያኖች ዕለታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ልምድ ውስጥ መግባት ይከብዳቸዋል። መጽሐፍ ቅዱስ የማላነበው:- 

. . . ጠቃሚ መስሎ ስለማይታየኝ” 

. . . ጊዜ ስለሌለኝ”

. . . ዘወትር እሁድ ቤተ-ክርስቲያን ስለምሄድ” 

. . . ስለማይገባኝ” 

ለሚሉት 4 የተለመዱ መጽሐፍ ቅዱሳችንን ችላ ምንልባቸው ምክንያቶችን ጆን ፓይፐር እንደሚከተለው ምላሽ ሰጥቶባቸዋል።

ምክንያት 1:- ”መጽሐፍ ቅዱስ የማላነበው ጠቃሚ መስሎ ስለማይታየኝ ነው።”

ይሄ የተለመደ ውጥረት ነው። ብዙ ክርስቲያኖች መጽሐፍ ቅዱሳቸውን ችላ የሚሉት በቀን ተቀን ሕይወታቸውና ሥራቸው ላይ ጥቅም ያለው ስለማይመስላቸው ነው። ታዲያስ መጽሐፍ ቅዱስ ማንበብ ያለብኝ ለምንድን ነው? በዚህ ጉዳይ ላይ አንድ የማውቀው ነገር ሲኖር የማላውቀውም ነገር ደግሞ አለ። የማውቀው ነገር መጽሐፍ ቅዱስ ለዚህ ሰው የዕለት ተቀን ሕይወቱ እና ሥራው አስፈላጊ እንደሆነ ሲሆን የማላውቀው ደግሞ በሕይወቱ እና በሥራው ላይ የግል ዓላማዎቹ ምን እንደሆኑ ነው። ይህንንም ማወቅ አስፈላጊ የሚያደርገው ለሕይወታችን እና ለሥራችን ያለን ዓላማ ከ መጽሐፍ ቅዱስ ጋር ተቃራኒ ከሆነ መጽሐፍ ቅዱስን በምናነብበት ጊዜ የሚያናድድ፤ የሚወቅስ ወይንም አሰልቺ ስለሚሆንብን ነው። ይህም የሚሆነው የመጽሐፍ ቅዱስ አስተምህሮ ከምንሄድበት አቅጣጫ በተቃራኒ እየሄደ ስላለ ነው። 


ለሕይወታችን እና ለሥራችን ያለን ዓላማ ከ መጽሐፍ ቅዱስ ጋር ተቃራኒ ከሆነ መጽሐፍ ቅዱስን በምናነብበት ጊዜ የሚያናድድ፤ የሚወቅስ ወይንም አሰልቺ ይሆንብናል።


ለዚህ ሰው የቀን ተቀን ሕይወቱ መጽሐፍ ቅዱስ አስፈላጊ እንደሆነ አውቃለሁ። እርሱ ላይመስለው ይችላል። እኔ ግን አስፈላጊ እነደሆነ አምናለሁ። መጽሐፍ ቅዱስ ሲናገር “እንግዲህ የምትበሉ ወይም የምትጠጡ ብትሆኑ ወይም ማናቸውን ነገር ብታደርጉ ሁሉን ለእግዚአብሔር ክብር አድርጉት” 1 ቆሮንቶስ 10፡31 ይላል። ደግሞም ሲናገር “ለሰው ሳይሆን ለጌታ እንደምትገዙ በትጋትና በበጎ ፈቃድ ተገዙ፤ ባሪያ ቢሆን ወይም ጨዋ ሰው፥ እያንዳንዱ የሚያደርገውን መልካም ነገር ሁሉ ከጌታ በብድራት እንዲቀበለው ታውቃላችሁና።”  ኤፌሶን 6፡7-8 ይላል። ለዚህ ለሥራ መጠየቅ ያሉብን 10 ያቄዎች ነዚሁ:-

ጥያቄ 1:- በሥራ ቦታችሁ ላይ ለማማረር ወይንም ለማጉረምረም ተፈትነው ያውቃሉ? ፊልጵስዩስ 2፡15-16 ከማጉረምረም ውጪ የሆነ ሕይወት እንዴት መኖር እንደምንችል በግሩም ሁኔታ ያሳየናል።

ጥያቄ 2:- በሥራ ቦታችሁ ላይ  የእናንተ ያልሆነውን ለመውሰድ ተፈትናችሁ ታውቃላችሁ? መጽሐፍ ቅዱስ ስለመመኘት፤ ስስት፤ መስረቅ እና ክርስቶስ ይበቃኛል በማለት ስለሚመጣ የልግስነት ነፃነት ብዙ የሚናገረው ነገር አለ። 

ጥያቄ 3:- በሥራ ቦታችሁ ላይ በፍርሃት ወይንም በጭንቀት ተፈትናችሁ ታውቃላችሁ? መጽሐፍ ቅዱስ ለስሌሌሎች ነገር የሚያወራውን ያህል ስለፍርሃት ይናገራል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በብዛት ካሉ ትዕዛዞች አንዱ “አትፍራ” የሚለው አንዱ ነው። በሥራ ቦታው ላይ ፍርሃት ላለበት ለማንኛውም ሰው መጽሐፍ ቅዱስ ጠቃሚ ነው።

ጥያቄ 4:- በአንዳንድ ነገሮች ዙሪያ ለመጎረር ወይንም የሰውን አትኩሮት ወደራሳችሁና ወደ ሥልጣናችሁ ለመሳብ ተፈትናችሁ ታውቃላችሁ? መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ትዕቢትና ስለ ትህትና ከሰዎችም ጋር ባለን ግንኙነት ላይ ስላለው ውጤት በጥበብ የተሞላ ነው።

ጥያቄ 5:- በሥራ ቦታችሁ ላይ ሰዎችን ለመቆጣት ተፈትናችሁ ታውቃላችሁ? የንዴት ችግር አለባችሁ? ቁጡ በመሆናችሁ ምክያት የሻከሩ ግንኙነቶች አላችሁ? መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ቁጣ ማንኛውም አይነት ሥነ-ልቦና ከሚለው በላይ በጠለቀ መንገድ ይፈታዋል።

ጥያቄ 6:- በሥራ ቦታችሁ ላይ አቋራጮችን ለመጠቀም፤ ከስራ ሰዓት ቀድሞ ለመውጣት፤ አርፍዶ ወደ ሥራ ለመግባት ወይንም በግማሽ ልብ ሥራን ለመስራት ተፈትናችሁ ታውቃላችሁ? መጽሐፍ ቅዱስ ስለሥራችን ጥራትም አስፈላጊ ነው።

ጥያቄ 7:- በሥራ ቦታችሁ ላይ በወሲባዊ ምኞት ተፈትናችሁ ታውቃላችሁ? መጽሐፍ ቅዱስ ይህን በተመለከተ ጤነኛ የሆነ ምልከታ ሰጥቶ በሚገባው ቦታ ያስቀምጠዋል።

ጥያቄ 8:- በሥራ ቦታ ላይ አንድ ሰው ክፉ ነገር ስለተናገራችሁ አሊያም የሥራ ዕደገት ስላመለጣችሁ ተከፍታችሁ እና ቂም ይዛችሁ ታውቃላችሁ? መጽሐፍ ቅዱስ ቂምን እንዴት ማስወገድ እንዳለብን በቂ የሆነ ትምህርት ይሰጠናል። 

ጥያቄ 9:- በሥራ ቦታችሁ ላይ መሆን ከሚገባችሁ በታች ያላችሁ እንደሆናችሁ እንዲሰማችሁ የሚያደርግ ወይንም እራሳችሁ ካስቀመጣችሁት የስኬት ደረጃ በታች ስለወረዳችሁ የጥፋተኝነት ስሜት ተሰምቷችሁ ያውቃል? መጽሐፍ ቅዱስ ለጥፋተኝነት ስሜት የሚያቀርበውን መፍትሄ ተቀበሉ።

ጥያቄ 10:- በሥራ ቦታችሁ ላይ የምታስቡላቸው፤ ወደ ሲዖል እንዳይወርዱ የምትፈልጓቸው ያልዳኑ ሰዎች አሉ? ሕይወታቸውን ለማዳን ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጪ እርዳታ ከየት ታገኛላችሁ? ይህንንም ለማድረግ ድፍረቱን እና ጥንካሬውን እንዲሁም ጥበብን ከየት ታገኛላችሁ?

መጽሐፍ ቅዱስ ለአንድ ሰው ሕይወቱና ሥራው አስፈላጊ ነው። የሁሉ ነገር ግን ዉሉ ግን ይህ ነው። የዓለምን ሁሉ ታላቅ ሃብት ማየት ይፈልጋል ወይ? ኢየሱስን ለማወቅና ከምንም ነገር በላይ በእርሱም ለመደሰት ይፈልጋል ወይ? ሰዎችን አብዝቶ ይወዳል ወይ? ኢየሱስንስ ባለማወቃቸው ያለእርሱም ለዘላለም የጠፉ ስለመሆናቸው ከልቡ ያዝናል ወይ? ጥያቄው ይህ ነው። ኢየሱስ በዚህ ሰው ሕይወት የበላይ ከሆነ፤ ፍላጎቱ ከምንም በላይ እርሱን ማወቅ ከሆነ፤ ፍላጎቱ በእርሱ መደሰት፤ እርሱን ከምንም በላይ አጥብቆ መያዝ ከሆነ፤ ፍላጎቱ ወደዚህ ልምምድ የሚቻለውን ያህል ሰው መሳብ ከሆነ እንግዲያው ያለ መጽሐፍ ቅዱስ መኖር አይችልም። በዓለም ላይ ካሉ መጽሐፎች ሁሉ ዋነኛው ነውና።

ምክንያት 2፡“መጽሐፍ ቅዱስ የማላነበው ጊዜ ስለሌለኝ ነው።”

ይሄም የተለመደ ክርስቲያኖች የሚገጥማቸው ችግር ነው። ብዙውን ጊዜ የዚህ አይነቱ ጥያቄ ልጆች ከሚያሳድጉ እናቶች ይመጣል። ለዚህም መልስ እንዲሆን ፓስተር ጆን ባል ሚስቱን በማገልገል ያለውን ሚና እንዴት መወጣት እንዳለበት የሚከተሉትን ስድስት ምክሮች ይለግሳል።

አንድ:- ልጆች ከቁጥጥር ውጪ ሆነው እንዳያስቸግሩ ነገር ግን ታዛዥና ራሳቸውንም እንዲገዙ በቤት ውስጥ የሥነ-ስርዓት ደንቦች ተግብሩ። ቀኑ እንደሚገባ እንዲሄድ ከባለቤትህ ጋር በመሆን ልጆች የሚተኙበትንና ምግብ የሚበሉበትን ጊዜ ከፋፍላችሁ ወስኑ። እንደሚመስለኝ ከሆነ ብዙ ወላጆች ልጆቻቸው የቤቱን ድባብ እንዲቆጣጠሩት ይፈቅዳሉ። ይሄ ግን በብዙ ጎኑ ልክ እንዳልሆነ ይሰማኛል። ስለዚህ አባት ከሚስትህ ጋር በመተባበር ቋሚ የሆነ የየዕለት ተግባር በመወሰን ልጆች ለእርሷም ሆነ ለአንተ እንዲገዙ ማድረግ አለብህ።

ሁለት:- ከልጆችህ ጋር በየዕለቱ የምትጫወትበትን ጊዜ መለየት አለብህ። ይህ እድሜአቸው በተቀየረ ቁጥር እንደሚቀየር ግልጽ ነው። ይሁን አንጂ ባለቤትህ ነፃ በምትሆንባቸው ጊዜያት ሙሉ ሃሳብህን ለልጆችህ በየዕለቱ መስጠት አለብህ። እኔና ቤተሰቤም ለብዙ ዓመታት ያደረግነው ይህንኑ ነው።

ሦስት:- ለግማሽ ቀን ወይንም ሙሉ ቀን የሚሆን ለብቻዋ እረፍት የምታደርግበት ጊዜ አመቻችላት። ከሕያው አምላክ እግዚአብሔር ጋር ጊዜ እንድታሳልፉ በየተራ ጊዜ ውሰዱ። ለልጆቹ የሚመችን ጊዜ መምረጥ ትችላለህ።

አራት:- የእግዚአብሔርን ቃል ጣምና ክብር አብራችሁ በመፈለጋችሁ ከምታየው ተምሳሌት የተነሳ የእግዚአብሔርን ቃል ፍላጎት በውስጧ እንዲጨምር በእግዚአብሔርን ቃል ምራት።

አምስት:- ከልጆቻችሁ ጋር የምታሳልፈውን ጊዜ ትርጉሙ እንዳይጠፋባት ከእግዚአብሔርን ቃል የበሰሉ ነገሮችን ንገራት።

ስድስት:- ፀልይላት። በእግዚአብሔር ቃል መደሰት የምትችልበት መነሳሳትና ልምድ ይኖራት ዘንድ ፀልይላት።

ምክንያት 3፡“መጽሐፍ ቅዱስ የማላነበው ዘወትር እሁድ ቤተክርስቲያን ስለምሄድ ነው።”

ብዙ ክርስቲያኖች መጽሐፍ ቅዱስን ቸል የሚሉበት ሦስተኛው ምክንያት በየሳምንቱ የሚሰሙት ስብከት በቂ ስለሚመስላቸው ነው። የፓስተሮች ሥራ መጽሐፍ ቅዱስን እራሳቸው ከተረዱ በኋላ ለእኔ ደግሞ በሳምንት አንድ ቀን ማስረዳት አይደል? የፓስተር ጆን ምላሽ ይህንን ይመስላል:-

ፓስተር በነበርኩበት ጊዜ ሰዎች ስብከቴን ሲሰሙ ደስ ይለኛል። ነገር ግን አዚህ ጋር አንድ አሳሳቢ ስህተት አለ። የእግዚአብሔርን ቃል በየሳምንቱ በኃይል እየመጣ ካለ ርሃብን ማጥገብ ብቻ ሳይሆን ርሃብንም ይቀሰቅሳል። የማገለግላቸው ሰዎች መጥተው “ከስብከትህ የተነሳ የእግዚአብሔርን ቃል አናነብም” ቢሉኝ ታላቅ ውድቀት ይሰማኝ ነበር።

ስብከት ብቻ በቂዬ ነው ብሎ ለሚል ሰው የሚከተሉትን ጥያቄዎች መልሼ እጠይቀዋለሁ:- የሚያስፈልግህ ያ ብቻ ነው? እሁድ የበላኸው ምግብ ሰኞ ላይ ጣዕሙ የማይታወቅህ ለምንድን ነው? እዚህ ጋር ሁለት ጉዳዮች ያሉን ይመስለኛል።

1. መጽሐፍ ቅዱስ ምን ያህሉ ነው የሚያስፈልገን?

2. መጽሐፍ ቅዱስ ምን ያህሉን ነው የምንፈልገው?

እስቲ ሁለተኛውን ጥያቄ እንመልከት። በሳምንት አንድ ቀን ለምን አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ብቻ ከሌላ ሰው ለመስማት ትፈልጋላችሁ? ይሄ ምን እንደማለት መሰላችሁ “ከአንዲት ልጅ ፍቅር ይዞኛል። እናም የምወዳት ልጅ በየቀኑ ደብዳቤ ትጽፍልኛለች። እኔ ደግሞ በሳምንት አንድ ቀን አንድ ሰው አንብቦ ምን እንዳለች እንዲነግረኝ እፈልጋለው።” በየቀኑ ከሚጻፉልህ የፍቅር ደብዳቤዎች ውስጥ  በሳምንት አንዱን ብቻ ለማንበብ መፈለግ ችግር እንዳለ ነው የሚያሳየው።

ለእግዚአብሔር ህዝቦች መጽሐፍ ቅዱስ ከምንም ጋር የማይስተካከል የፍቅር ደብዳቤ ነው። “ቃልህ ለጕሮሮዬ ጣፋጭ ነው ከማርና ከወለላ ይልቅ ለአፌ ጣፈጠኝ” መዝሙረ ዳዊት 119፡103 ይህን መዝሙር ለጻፈው ሰው ሰኞ፤ ማክሰኞ፤ ረቡዕ፤ ሐሙስ፤ አርብ እና ቅዳሜ ምንም አያስፈልገኝም ፤እሁድ ላይ አንድ ማንኪያ ማር መውሰዴ ከበቂ በላይ ነው ማለት ትርጉም የማይሰጥ ንግግር ነው። ነገር ግን እንዲህ ይላል “አቤቱ፥ ሕግህን እንደ ምን እጅግ ወደድሁ! ቀኑን ሁሉ እርሱ ትዝታዬ ነው።” መዝሙረ ዳዊት 119፡97 “ከወርቅና ከክቡር ዕንቍ ይልቅ ይወደዳል ከማርና ከማር ወለላም ይጣፍጣል።” መዝሙረ ዳዊት 19፡10 “እርስዋንም እንደ ብር ብትፈላልጋት፥ እርስዋንም እንደ ተቀበረ ገንዘብ ብትሻት የዚያን ጊዜ እግዚአብሔርን መፍራት ታውቃለህ፥ የአምላክንም እውቀት ታገኛለህ።” ምሳሌ 2፡4-5

ታዲያ ለምን ይህን የሚመስል ውበት በሳምንት አንድ ጊዜ ብቻ ለመመልከት ትፈልጋለህ? ይህን ጣፋጭ ማር በሳምንት አንድ ጊዜ ብቻ መቅመስ፤ ከፍቅረኛችሁ የተላከውን ይህን ደብዳቤ በሳምንት አንድ ጊዜ ብቻ ማንበብ ለምን ትፈልጋለህ?

ከልምድ ከታሪክና ከመጽሐፍ ቅዱስ መናገር የምችለው ነገር እያንዳንዱ ክርስቲያን በሳምንት ከአንድ ምግብ በላይ እንደሚያስፈልገው ነው። ይህ ነገር በሰውነታችን ላይ አይሰራም፤ በመንፈሳዊ ሕይወታችንም እንዲሁ። በሳምንት አንዴ የምሰማው ስብከት በቂዬ ነው ብሎ ለማለት ፈተናዎቹ መቼም ቢሆን አያቋርጡም። ጥርጣሬ ሁል ጊዜ ያጠቃናል። ሰይጣን ከመጠን በላይ ሰራተኛ ነው። መከራዎች ከባድ ናቸው። ግጭቶች ብዙ ናቸው። ስሜቶቻችን የተረጋጉ አይደሉም። እምነት ተስፋ እና ፍቅር አደጋ ላይ ናቸው ። እኔ ይህን ላደርገው አልችልም። ሌላም ሊያደርገው የሚችል ሰው አለ ብዬ አላስብም።

ምክንያት 4፡“መጽሐፍ ቅዱስ የማላነበው ስለማይገባኝ ነው።”

በመጨረሻም መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብና መረዳት እንዲሁ ከባድ ለሚሆንባቸው ሰዎችስ? እንደዚህ ለሚሉ መጽሐፍ ቅዱስን ለማንበብ የሚሞክሩ አንባቢያን ፓስተር ጆን እነዚህን ምክሮች ይሰጣል።

አንድ፤ ልታነቡት የምትችሉት የተለያዩ እንደ “አዲሱ መደበኛ ትርጉም” ወይንም “ለማንበብ ቀለል ባለ አማርኛ የቀረበ” እንደሚሉት አይነት ትርጉሞች ይኑሯችሁ።

ሁለት፤ የቤተክርስቲያኒቱ መጋቢ ዘወትር እሁድ ከመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችን የሚያስረዳበት ቤተክርስቲያን ይኑራችሁ።

ሦስት፤ ጥሩ የማጥኛ መጽሐፍ ቅዱስ ይኑራችሁ። ከጥሩ ማጥኛ መጽሐፍ ቅዱስ ህዳግ ላይ ብዙ ጥያቄዎችን ሊመልሱ የሚችሉ ማስታወሻዎች አሉ።

አራት፤ በዝግታ እና በጥንቃቄ አንብቡ። አንዳንድ ክፍሎችን በማስታወሻ ለመጻፍ ሞክሩ። ረጃጅም የብሉይ ኪዳን መጽሐፍትን ማለቴ ሳይሆን ግር የሚላችሁ ከወንጌላት ወይንም ከመልዕክት መጽሐፍቶች ዉስጥ ግር የሚላችሁ አንድ ዘለላ ጥቅስ ወይንም አንቀጽ ካለ እርሱን በማስታወሻ ላይ ጻፉት።

አምስት፤ እግዚአብሔር ብርሃንን እንዲሰጣችሁ ጸልዩ። እግዚአብሔር ልጁን ማሳወቅ ይወዳል። የሕይወቱን ዋጋ ከፍሎ ወደዚህ የላከው እንዲታወቅና እንዲወደድ ስለሚፈልግ ነው። በልጁ እና በቃሉ የሰጠውን ብርሃን ከናንተ ሊደብቅ ፍቃደኛ አይደለም። 


እግዚአብሔር ብርሃንን እንዲሰጣችሁ ጸልዩ። እግዚአብሔር ልጁን ማሳወቅ ይወዳል። የሕይወቱን ዋጋ ከፍሎ ወደዚህ የላከው እንዲታወቅና እንዲወደድ ስለሚፈልግ ነው። በልጁ እና በቃሉ የሰጠውን ብርሃን ከናንተ ሊደብቅ ፍቃደኛ አይደለም። 


 

Originally Posted at DesiringGod.org, Translated by Joshua Terefe


 

Last modified on %AM, %10 %970 %2017 %01:%Jan
Tony Reinke

Tony Reinke is a staff writer for Desiring God and the author of three books: 12 Ways Your Phone Is Changing You (2017), Newton on the Christian Life: To Live Is Christ (2015), and Lit! A Christian Guide to Reading Books (2011). He hosts the popular Ask Pastor John podcast, and lives in the Twin Cities with his wife and three children.

twitter.com/TonyReinke

የእግዚአብሔር ሞራላዊ (ግብረ ገባዊ) እና ሉአላዊ ፍቃዶች

የእግዚአብሔርን ሞራላዊ (ግብረ ገባዊ) እና ሉአላዊ ፍቃዶች መለየት እንድትችሉ ልረዳችሁ እፈልጋለሁ። ቀጥሎ ባሉት ሁለት ሃሳቦች መሀከል ያለውን ተቃርኖ መረዳት...

John Piper - avatar John Piper

ጨርሰው ያንብቡ

ድክመታችሁን ለእግዚአብሔር ስጡት

እንደምን አላችሁ? ጥፋተኛ ብሆንም እነዚህ ቃላት እንደ ጥያቄ ሳይሆን እንደ ሠላምታ ሲቀርቡልኝ ትንሽ ይረብሸኛል። ተጨባጭ መልስ ሳንፈልግ “እንዴት ናችሁ?” ...

Steven Lee - avatar Steven Lee

ጨርሰው ያንብቡ

 

The views and opinions expressed on Daily Injera are solely those of the original authors and our contributors. These views and opinions do not necessarily represent Daily Injera or our Staff.

Newsletter

Subscribe to our newsletter. Don’t miss any article, devotionals or wallpapers.

We do not spam!

You're automatically subscribed to bi-weekly articles and daily devotionals. You can customize your subscription settings here.