ነገር ግን፣ አይቀሬ በሆነው የሰው ልጅ እጣ ውስጥ፣ የእግዚአብሔር ሰው ማረፍን (እረፍትን) እንዲያውቅ፣ እንዲለማመድ የእግዚአብሔር ቃል ያስተምራል። እረፍት ማለት ከመከራ፣ ከችግር ነጻ መሆን ማለት ሳይሆን በመከራና በችግር ውስጥ በማይናወጥ ሰላም፣ እውቀት፣ እምነት ውስጥ መገኘት ነው። ይህ እንዴት ይቻላል? መቼም የሰው ልጅ ችግርን ወይንም የሚገጥመውን መከራ ለማለፍ እና ለመቋቋም የማያደርገው ነገር የለም። ሆኖም በዚህ የመዝሙር ክፍል እንድምንመለከተው ማረፍ የሚመጣው
1. እግዚአብሔርን በማወቅ ነው። እግዚአብሔርን ማወቅ የእውቀት ጉዳይ ሳይሆን ማንነቱን ማወቅና ማመን ነው። ከቁጥር 1 ጀምሮ ዳዊት እግዚአብሔር መጠጊያ ነው፣ ሃይል ነው፣ ረዳት ነው፣ ከፍ ያለ ነው፣ ልዑል ነው ይለናል። እግዚአብሔር ብቻ ነው ብቸኛ ማረፊያ፣ ጉልበት ያለው፣ አቅም ያለው። ይህን ማወቅ ማረፍ ነው።
2. የእግዚአብሔርን ችሎታ ማወቅ። ማረፍ ማለት እግዚአብሔር ሁሉን የሚችል፣ ፈጣን ረዳት፣ ቀስትን መስበር፣ ጦርን መቁረጥ፣ በቃሉ ሁሉን መግዛት ማንቀጥቀጥ የሚችል፣ ሊገለፅና ሊገመት የማይችል ሃይልና ችሎታ በውስጡ ያለ ሃያል አምላክ እንደሆነ ማወቅ ነው። የምናርፈው የእግዚአብሔርን ችሎታ ስናውቅ ነው።
3. እግዚአብሔር አምላክ ነው። እግዚአብሔር አምላክ ነው ማለት የሚያናውጠንን ችግር እና ፈታኝ ነገር ጨምሮ በሁሉ ነገር የበላይ እና የላቀ ሆኖ ያለ ማለት ነው። እግዚአብሔር አምላክ ነው ማለት በሁሉ ነገር ላይ የበላይ፣ ሁሉን የሚያይና የሚቆጣጠር፣ ሁሉ ከእርሱ ስር የሆነ፣ እርሱ ግን ብቻውን ከፍ ያለ ማለት ነው። ማረፍ የሚመጣው እግዚአብሔር አምላክ እንደሆነ ስናውቅ ነው።
4. እግዚአብሔር ታማኝነት ማመን። እግዚአብሔር አምላክ ታማኝ አምላክ ነው። ዳዊት “አምላካችን”፣ “የያዕቆብ አምላክ” እያለ በመዝሙሩ የሚጠራው እግዚአብሔር የሩቅ አምላክ አይደለም። እግዚአብሔር አምላክ ከጥንትም ከአባቶቻችን ዘመን እስከአሁን “ከእኛ” ጋር ነው። የምናልፍበት፣ የከበበን፣ የሚያስጨንቀን ሁሉ “አያስፈራንም፣ አያስደነግጠንም፣ አያናውጠንም” ምክንያቱም ትላንት እንደነበረው ዛሬም እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ነው። የትላንቱ እግዚአብሔር የዛሬም የነገም የከነገ-ወዲያም አምላክ እንደሆነ ስናውቅ ነው የምናርፈው።
ያረፈ ሰው ይጠብቃል። ያረፈ ሰው ሰላሙ የበዛለት ነው። ያረፈ ሰው ለሌላውም ማረፍ ነው።