እንደ ሰውየው እና እንደሁኔታው ዓይነት ደግሞ እጅግ ከእነእርሱ ያነሳችሁ አሊያም ጊዜአቸውን እያባከናችሁ እንደሆነ ሊሰማችሁ ይችላል። በመጀመሪያችሁ በእዚህ ቅርርብ እነእርሱን መማረክ እንዳለባችሁና እናንተን የሚያዩበት መነፅር ደግሞ በእዚህ የመጀመሪያ ግንኙነታችሁ ላይ ሊወሰን እንደሚችል ሊሰማችሁ ይችላል። እንደዚህ በሚሆንበት ጊዜ ከእናንተ ጋር ወዳጅነት ሊመሠርቱ በሚመጡበት ጊዜ ልታቀርቡላቸው ከምትችሉት ነገር ይልቅ ስለሰራችኋቸው ጥፋቶች እንድታስቡ ያደርጋችኋል።
መልካም ወዳጅነት ካለን ሰው ጋር ግን ሲሆን ለመቅረብ ብዙም አንቸገርም።ጥሩ ስሜት በማይሰሙን አሰቀያሚ ቀኖቻችን ሳይቀር ከእነእርሱ ጋር ምቾት ይሰማናል። በቀላሉ ወደ እነእርሱ ቀርበን በልባችን ውስጥ ስላለው ነገር በነፃነት ልናናግራቸው እንችላለን።
እዚህ ምድር ላይ ያሉ ሰዎችን ቀርበን የምንገናኝበትን መንገድ በሰማይ ያለውን አምላካችንን ቀርበን የምንገናኝበት መንገድ ጋር ሊዛመድብን ይችላል። ሩቅ እንደሚኖር ባዳ ለእኛ ጊዜ የሌለው ጉዳዮቻችንን ከመስማት ይልቅ በሌላ ሥራ እንደተጠመደ አድርገን ምናስበው ከሆነ ወደ እርሱ ስንቀርብ በታላቅ ጥንቃቄ ይሆናል አልያም ወደ እርሱ ላንቀርብ እንችላለን። የልባችንን ሊሰማ ፍቃደኛ ልብ እንዳለው እና ጓደኛችን አድርገን ብናየው በተለየ መልኩ ወደ እርሱ እንቀርባለን።
እግዚአብሔር ወደ እርሱ እንድንቀርብ ይፈልጋል። ወደ እኛ መቅረብ ይችል ዘንድ ወደ እርሱ እንድንቀርብ ይፈልጋል። የመጀመሪያውን እርምጃ እንድንወስድ እየጠበቀን ነው። ምን እንደተከሰተ አስቀድሞ ስለሚያውቅ ልንነግረው ስላለው ነገር አይፈራም። ይሁን እንጂ ቀድመን መንፈስ ቅዱስ ጋር ስለሆነ የምንደርሰው ከእርሱ ጋር ምቾት እንዲሰማን ይፈልጋል።
እግዚአብሔር ፍቅር እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል። ወደ እግዚአብሔርም የምንቀርብበት መንገድ ደግሞ ስለዚህ እውነት ባለን መረዳት ላይ የተመሠረተ ነው። ወደ ፍቅር እንዴት መቅረብ እንችላለን? እንዲህ መሆኑ ወደ እርሱ እንድትቀርቡ ያደርጋችኋል ወይንስ ርቃችሁ እንድትቆሙ? የዚህ ሁሉ መሠረት ፍቅር ለእኛ ምን እንደሚመስል እና ስለ ፍቅር ያለን መረዳት ነው።
1 ቆሮንቶስ 13 "ፍቅር ታጋሽ ነው" ይላል። እኛ ከምንታገሠው በላይ አብልጦ ይታገሠናል። ፍቅር ቸርነትን ያደርጋል፤ ክፉ አይደለም! ጨቋኝ አይደለም! በኃጢያታችን እንኳ እያለን ለእኛ ቸር ነው። (ሮሜ 5፡8 “ነገር ግን ገና ኃጢአተኞች ሳለን ክርስቶስ ስለ እኛ ሞቶአልና እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን የራሱን ፍቅር ያስረዳል”።) ይሄ የእርሱ ቸርነት ነው። ፍቅር አይቀናም። ቅንአት እኛ የምንፈልገው ነገር ያላቸውን ሁሉ እንድንጠላ ያደርጋል። እግዚአብሔር ግን መሻታችንን ስናገኝ ደስ ይለዋል። ሃሳቡ የልባችንን መሻት መስጠት ነው። ምዕራፉ ፍቅር ምን እንደሆነ ሊያስረዳን ይቀጥላል። ፍቅሩ ያለ ገደብ ይወድደናል።
ስለዚህ ንጹህ ፍቅር ወደሆነው ወደ እግዚአብሔር ስንቀርብ መጽሐፍ ቅዱስ የሚከተሉትን ቀላል መመሪያዎች ይሰጠናል።
ዕብራውያን 4፡12-16
“የእግዚአብሔር ቃል ሕያው ነውና፥ የሚሠራም፥ ሁለትም አፍ ካለው ሰይፍ ሁሉ ይልቅ የተሳለ ነው፥ ነፍስንና መንፈስንም ጅማትንና ቅልጥምንም እስኪለይ ድረስ ይወጋል፥ የልብንም ስሜትና አሳብ ይመረምራል፤ እኛን በሚቆጣጠር በእርሱ ዓይኖቹ ፊት ሁሉ ነገር የተራቆተና የተገለጠ ነው እንጂ፥ በእርሱ ፊት የተሰወረ ፍጥረት የለም። እንግዲህ በሰማያት ያለፈ ትልቅ ሊቀ ካህናት የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ስላለን፥ ጸንተን ሃይማኖታችንን እንጠብቅ። ከኃጢአት በቀር በነገር ሁሉ እንደ እኛ የተፈተነ ነው እንጂ፥ በድካማችን ሊራራልን የማይችል ሊቀ ካህናት የለንም። እንግዲህ ምሕረትን እንድንቀበል በሚያስፈልገንም ጊዜ የሚረዳንን ጸጋ እንድናገኝ ወደ ጸጋው ዙፋን በእምነት እንቅረብ”።
በመጀመሪያ ይህ ክፍል ስለ እግዚአብሔር ቃል ይናገራል። የሀሳባችን እነዲሁም የልባችን መርማሪ እንደሆነ ይናገራል። በመቀጠልም ወደ ቅዱስተ ቅዱሳኑ ሊገባ ስለተቻለው የብሉዩን ኪዳን ሊቀ ካህን ስለተካው የአዲሱ ኪዳን ሊቀ ካህን ደግሞ ይናገራል። ኢየሱስ በመስቀል ላይ ሲሞት ሁላችንም ወደዚያ ቅዱስ ስፍራ መግባት እንችል ዘንድ መጋረጃው እንደተቀደደ ይነግረናል።
ኢየሱስ በነገር ሁሉ የደረሱብንን ነገሮች ይረዳናል። ስላለብን ውጊያ ጥልቅ የሆነ መረዳት አለው። ሊማልድልንም ከአባቱ ጋር ተቀምጧል። ወደ ዙፋኑ በድፍረት እንድንቀርብ እየጋበዘን ነው። አትፍሩ እያለን ነው። ምን እንደሆነ አስቀድሜ አውቃለሁ! ቃሉን ስታነቡ ስላላችሁበት ሁኔታ እውነቱን በልባችሁ በተረዳችሁ ጊዜ ስላስፈለጋችሁ እርዳታ የሚሆን ጸጋ እና ምህረት ልሰጣችሁ በእጄ አለኝ። ሲፈርድባችሁ የነበረው እርሱ እንጂ እኔ አይደለሁም። ወደ ፍርድ ዙፋን ሳይሆን ወደሚረዳችሁ የጸጋ ዙፋን ነው እየቀረባችሁ ያለው።
“ቃሉን የሚሰማ የማያደርገውም ቢኖር የተፈጥሮ ፊቱን በመስተዋት የሚያይን ሰው ይመስላል፤ ራሱን አይቶ ይሄዳልና፥ ወዲያውም እንደ ምን እንደ ሆነ ይረሳል። ነገር ግን ነጻ የሚያወጣውን ፍጹሙን ሕግ ተመልክቶ የሚጸናበት፥ ሥራንም የሚሠራ እንጂ ሰምቶ የሚረሳ ያልሆነው፥ በሥራው የተባረከ ይሆናል” (ያዕቆብ 1፡23-25)።
እንደ ክርስቲያኖች በምንኖረው ነሮ ለሚኖረን ውጊያ የእግዚሐብሔር ቃል ወሳኝ መሣሪያ ነው። የልባችንን ድካም እና ስህተቶች እየገለጠ በአሸናፊዎች ወገን እንድንሆን ያደርገናል። የእግዚአብሔር ቃል በሚገልጥልን ነገሮች ምን እንደምናደርግ ግን ምርጫው የእኛ ነው። እንደዚያ መልኩን አይቶ እንደሚሄደው ደግሞም እንደማይቀየረው ሰው መሆን ሊያምረን ይችል ይሆናል። ነገር ግን በተለወጥን ጊዜ ነፃነት እና በረከትን እናገኛለን።
ስለ እግዚአብሔር ቃል አላማ ያለን መረዳት ልክ ያልሆነ ከሆነ እንዲቀይረን ስፍራ ላንሰጠው እንችላለን። የተሳለ ስለሆነ ሊወጋን ይችላል። ነገር ግን በልባችን ውስጥ የተጋለጠውን ኃጢያት ማሸነፍ እንችል ዘንድ ጸጋውን እና ምህረቱን እንዲያሳየን ከእርሱ ሳይሆን ወደእርሱ የመሸሽ መብት አለን።
ኢየሱስ “የመቤዣ ዋጋችሁን ከፍያለሁ። በመስቀል ላይ ስሞትላችሁ ዋስ ሆኛችኋለሁ ስለዚህ ወደ እኔ ኑ! ስለ ትህትናችሁ ማበረታቻ ጸጋን ልሰጣችሁ እፈልጋለሁ። በእፍረታችሁ ፈንታ ምህረትን ልሰጣችሁ እፈልጋለሁ።” እያለን እንደሆነ ልናስብ እንችላለን።
ወደ እግዚአብሔር ስንቀርብ እና ወደ መገኘቱ አንድ እርምጃን ስንወስድ ትቶን ወደኋላ አያፈገፍግም ደግሞም እንዳንመጣ አይከለክለንም። ይልቁንም ወደ እኛ ይጠጋል የበለጠ ወደ እኛ ይቀርባል። እጆቹን ዘርግቶ ወደ ምቹው እቅፉ ይቀበለናል። ትዕቢተኛን ይቃወማል ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል። ወደ እግዚአብሔር ስንቀርብ “ጌታ ሆይ ታስፈልገኛለህ። ይህንን በእራሴ ማድረግ አልችልም” እያልን ነው። ወደ እርሱ ስንቀርብ ትሑታን እየሆንን ነው። የዚህን ጊዜ በፍቅሩ ይዳስሰናል።
ወደ እግዚአብሔር መቅረብ (ክፍል 2)
Translated by Joshua Terefe