ሁል ጊዜ ግን እንደዚያ አይደለም። አንዳንድ ጊዜዎች አሉ፤ የምወዳቸው፤ አስደናቂ ደስታ እና ነፃነት ያለባቸው። ለሳምንታት አሁን እንደዚህ ባለ ወቅት ውስጥ አለው። መጽሐፍ ቅዱስ ለማንበብ እና ለመጸለይ ጊዜ መውሰድ ታላቅ ደስታ ሆኖልኛል። በአሁኑ ጊዜ ታዲያ በመጽሐፍ ቅዱስ ስለመደሰት ወደሚያወሩ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ተስቤአለሁ። በመዝሙር 19 ደግሞም ስለዚህ ታላቅ የእግዚአብሔር ስጦታ ዳዊት ያለውን ደስታ በአግራሞት ስመለከት ነበር። የእግዚአብሔር ቃልን ጥቅም በብዛት ከዘረዘረ በኋላ እንዲህ ይላል፣
ከወርቅና ከክቡር ዕንቍ ይልቅ ይወደዳል
ከማርና ከማር ወለላም ይጣፍጣል።
ባሪያህ ደግሞ ይጠብቀዋል
በመጠበቁም እጅግ ይጠቀማል።
የእግዚአብሔር ቃል እጅግ ውድ እንደሆነ ዳዊት ይነግረናል። ዳዊት በሀገሩ ላይ ንጉሥ ነው እናም ወደ ሀብቷ ሁሉ ሊደርስ ይችላል፣ ነገር ግን ከሁሉ ይልቅ ከሚበልጥ የእግዚአብሔር ቃል ጋር ሲወዳደሩ ምንም አንዳልሆነ አየ። የሌሎች ሰዎች መሻት እራሳቸውን በወርቅ ማበልጸግ ሲሆን የእርሱ መሻት ግን መጽሐፍ ቅዱስን በመጠቀም በእግዚአብሔር ጥበብ እራሱን ማበልጸግ ነው።
የእግዚአብሔር ቃል አስደሳች እንደሆነ ዳዊት ይነግረናል። ከማር ይልቅ የሚጣፍጥ ተፈጥሮአዊ ነገር ይኖራል ብዬ አላስብም፤ ይሁን እንጂ ዳዊት የእግዚአብሔር ቃል ከማርና ከማር ወለላም ይጣፍጣል ብሎ ያውጃል። ማር አይንን እንደሚያበራ የእግዚአብሔር ቃልም ነፍስን ያበራል።
የእግዚአብሔር ቃል ጠባቂ እንደሆነ ዳዊት ይነግረናል። በቃሉ ውስጥ የተገለጠው የእግዚአብሔር ጥበብ ከኃጢያት እና መዘዞቹ እንደሚያስጠነቅቀው እና እንደሚጠብቀው ያውቃል።
የእግዚአብሔር ቃል ማትረፊያ እንደሆነ ዳዊት ይነግረናል። የአግዚአብሔር ቃል ማስጠንቀቅ ብቻ ሳይሆን ትርፍም አለው። የእግዚአብሔርን ጥበብ የሚጠብቁ ደግሞም ሕጉን የሚታዘዙ ከእግዚአብሔር ጋር አካሄድን በማድረግ የሚመጣን ጥቅም ሁሉ ይቀበላሉ። ከሁሉ የሚበልጠውን ሽልማት ይቀበላሉ እርሱም በየቀኑ ከእግዚአብሔር ጋር ደግሞም በእግዚአብሔር ውስጥ መሆናቸው ነው።
የእግዚአብሔር ቃል እጅግ ውድ ፣ አስደሳች ፣ ጠባቂ እና ማትረፊያ ነው። እንዴት ያለ ስጦታ ነው!
Originally Posted at Challies, Translated by Joshua Terefe