Saturday, 20 July 2019

አምላክ ተዛመደን

Posted On %AM, %09 %041 %2017 %03:%Jan Written by

የሳሎን ማዕዘን ላይ የሚቀመጡ አረንጓዴ ዛፍ መሰል ፕላስቲኮች ከነአብረቅራቂ ጌጦቻቸው ሳይመጡ በፊት የዚህን ህጻን ልደት የሚያስታውሱኝ ነገሮች እምብዛም ናቸው። እነዚህ በመብራት የተሽቆጠቆጡ “ባዕድ” የገና ወቅት መለያዎች ከተማዋን አጥለቅልቀው ሳይ ድብልቅ ስሜት ይሰማኛል፡-አንድም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የልደቱ ወቅት መቃረቡን ሲያመላክቱኝ፤በሌላ በኩል ከህጻኑ ልደት ጋር ያላቸውን ግንኙነት ባለመረዳቴ “እንግዳነታቸው” ይሸተኛል።

“ዓለሙ ሁሉ ተከትሎት ስለሄደው” ጎልማሳ ሳስብ ከብዙሀኑ የተለየ ስሜት ይሰማኛል። ብዙዎች አዘውትረው ስለወጣትነት ዘመኑ ሲያስቡ፤ህፃንነቱ ይናፍቀኛል። ሰርክ ስለአምላክነቱ ሲያወሩ ፤ ሰውነቱ ይጎላብኛል። አሊያም በተዐምራቱ እየተገረሙ ሲመሰክሩለትና ሲያሞካሹት፤ድካሙ እና ዝቅ ማለቱ ያስደምመኛል።

እነሆ ይህ ዓለማትን በቃሉ እንዳፀና የማምነው አምላክ በግርግም ከተወለደ ሁለት ሺህ አመታት ያህል አለፉ ተባልን፤ግን ከየትኛውም ሰው በላይ እለት እለት አጠገባችን ያለ ያህል እስኪሰማን ድረስ ጉልህ አሻራዉን ትቶ ሄደ-ምን አይነት ድንቅ ነገር ነው?

የህፃኑን ዝቅ ብሎ መምጣት የሚያወሱ ምስሎችም ሆኑ ስብከቶች ብዙ አይደሉም። እኔ ግን ይህ ወቅት በመጣ ቁጥር ግርግም ውስጥ ከደሀ ቤተሰቦች የተወለደ ህፃን ተኝቶ ይታየኛል። ብዙ ምስሎች እንደሚያሳዩን በአንድ ጽድት ያለ የግርግም ማእዘን፤ንጹህ ጭድ ላይ በተቀመጠ ድንክ አልጋ እያበራ የተኛ ህጻን አይታየኝም። በዙሪያውም እናቱ እና አባቱ በደስታ ተውጠው፤ጸዳል በዙሪያቸው ፈንጥቆም አላስተውልም።ከዚህ ይልቅ ወደ እውነታው ልቀርብ እፈልጋለሁ። የበጎች ኮረኮር ምናልባትም የከብቶች ፅዳጅ በሞላው ደብዛዛ ግርግም ውስጥ በጨርቅ የተጠቀለለ ህጻን ሲያለቅስ፤በምጥ እና ማረፊያ በማጣት የተንገላታች ሚስኪን ኮረዳ እና ለቤተ አዝማዱ ምን ብሎ ምላሽ እንደሚሰጥ እያሰበ የሚጨነቅ ጎልማሳ።

ለብዙዎች ለመውደቃቸው እና ለመነሳታቸው ምክንያት የሆነው ህጻን ከቶውኑ ብርሀን ወደሌለባት ወደዚች ምድር ሊዛመደን መጣ። በጣም ዝቅ ብሎ፤ “አምላክ በስጋ ቢወለድ”ሊደረግለት ይገባዋል ብለን ከምናስበው የመሳፍንት እና የልዑላን አቀባበል ይልቅ የእረኞችን ታዳሚነት መርጦ ወደዚች ዓለም ገባ።

ለምን? ብዬ አስባለሁ። ለምን እንዲህ ተዛመደን? ለምን በቤተ መንግስት አልተወለደም? ለምን ልዑላን አልዘመሩለትም?? እርግጠኛውን መልስ አላውቀውም። ግን ምናልባት የእየሱስ አምላክነት ፈጽሞ ሳይዘነጋ ሊቀጥል የቻለው በዚህ “ከተጠበቀው እና ሊሆን ይገባዋል” ተብሎ ከታሰበው አይነት የወጣ ማንነት ስለነበረው ይመስለኛል። በድህነት ተዛመደን ፤ በማጣት፣ በመጨነቅ እና በመታወክ ህመማችንን ተካፈለ። ይነግሳል ተብሎ ሲጠበቅም እየሩሳሌም እያየችው ተሰቀለ፤ግን ጥቂቶች እያዩት ከሞት ተነስቶ አረገ።

“በእውነትም አምላክ ነው!” እንድንል ከሚያደርጉን ነገሮቹ ይልቅ “ግን እሱ አምላክ ነው?” ብለን እንድንጠራጠር በሚመስል ሁኔታ አምላክ በግርግም ተዛመደን። እንጃ ይህ የጥርጣሬ ሸለቆ እምነታችን የፀናበት አለት ይሆንን?

ክርስቶስ እንኳን ተወለድክልን!!!

Written by Wongel Alemayehu

እናትነት ትልቅ ኃላፊነት ነው

እናትነትን ለመግለፅ አንድ ቃል መምረጥ ቢኖርብኝ “መለወጥ” የሚለውን ቃል እመርጣለሁ። ስራ የበዛባት እናት እያንዳንዱ ቀኗ ቢታይ ብዙ ስራዎችን ትሰራለች። በ...

Rachel Jankovic - avatar Rachel Jankovic

ጨርሰው ያንብቡ

መጽሐፍ ቅዱስን ለማንበብ የሚረዱ ሁለት ጠቃሚ መንገዶች

መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ ጠቃሚ እንደሆነ የሚያስረዱ ምክንያቶችን መናገር ላያስፈልጋችሁ ይችላል። ጠቃሚ መሆኑን ግን ጠንቅቃችሁ ታውቃላችሁ። ትንሽ ማበረታቻም ሊያ...

Andy Naselli - avatar Andy Naselli

ጨርሰው ያንብቡ

 

The views and opinions expressed on Daily Injera are solely those of the original authors and our contributors. These views and opinions do not necessarily represent Daily Injera or our Staff.

Newsletter

Subscribe to our newsletter. Don’t miss any article, devotionals or wallpapers.

We do not spam!

You're automatically subscribed to bi-weekly articles and daily devotionals. You can customize your subscription settings here.