Tuesday, 20 April 2021

ኢየሱስ ቢሆን ምን አያደርግም ነበር? (ወቅታዊውን የሃገራችን ሁኔታ በተመለከተ)

Posted On %PM, %14 %806 %2018 %21:%Mar Written by

አሁን ሃገራችን ስላለችበት ሁኔታ ሳስብ አንድ ነገር ትዝ አለኝ።

ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ የኖረበት ዘመን (የመጀመርያው ክፍለዘመን) ላደገበት የአይሁድ ማህበረሰብ የመረጋጋት እና የሰላም ጊዜ አልነበረም። አይሁዶች በሮም ተገዝተው የነበረበት፣ በዚህም ምክንያት ከዚህ አገዛዝ ነጻ ለመውጣት እየታገሉ የነበረበት ጊዜ ነበር። በዚህም ምክንያት አይሁድ ራሳቸው በዚህ ሃሳብ ተከፋፍለው ነበር። ቀናተኛዎቹ (“Zealots”) የተባሉት የአይሁድ ክንፍ በጦርነት ትግል ሮምን ለመጣል የተነሱ እና ሽምቅ ውጊያ የሚያደርጉ ነበሩ። ፈሪሳውያኑ ደግሞ ሁሉን “አስማምተው” ለመኖር የሚሞክሩ ነበሩ። እንዲሁም ከማህበረሰቡ ተገልለው በበረሃ የሚኖሩ (የመነኑ) የአይሁድ ሰዎችም ነበሩ።

ጌታ ኢየሱስ እንደ አንድ ወጣት እነዚህ ሶስት አማራጮች ነበሩት። ሮምን ለመታገል ሽምቅ ውጊያ ውስጥ መግባት (ቀናተኞች) ፣ የሕግ ሊቅ ሆኖ ራስን ከሮም አገዛዝ ጋር አመቻችቶ መኖር (ፈሪሳውያን) አልያም ከሁሉም በመራቅ በምድረ በዳ መኖር (መናኞች)። ኢየሱስ ሶስቱንም ለመሆን አልወደደም!

“ኢየሱስ ቢሆን ምን ያደርግ ነበር?”

በ1980ዎቹ በአሜሪካ በአንዲት ቤተ ክርስቲያን ባሉ ወጣቶች አንድ እንቅስቃሴ ተጀምሮ ነበር። ወጣቶቹ እየበዛ ካለው የአለም ክፋት አንጻር ክርስቲያናዊ ኑሮ እና ምላሽ እንዴት መሆን አለበት ከሚል መነሻ ወደ አንድ ሃሳብ ይደርሳሉ። ሃሳቡም “ሁሉም ክርስቲያኖች በእያንዳንዱ ሁኔታ ፣ ውሳኔ እና አጋጣሚ ላይ ለክርስቲያናዊ ኑሮም ሆነ ምላሽ ለመስጠት ‹ኢየሱስ ቢሆን ምን ያደርግ ነበር?› ብለው ራሳቸውን መጠየቅ አለባቸው” የሚል ነበር።

እነዚህ ወጣቶች ትክክለኛ ሃሳብ አስበው ነበር። በእነርሱ የተጀመረው እንቅስቃሴም አለምን አጥለቅልቆ “ኢየሱስ ቢሆን ምን ያደርግ ነበር?” በእንግሊዘኛው ደግሞ “What would Jesus do?” ወይም በአጭሩ “WWJD” የሚል ጽሁፍ ያዘለ ቲሸርት እና የአንገት ብሎም የእጅ ማስጌጫ በአለም ላይ በክርስቲያኖች ዘንድ እጅግ ተፈላጊ ለመሆን በቃ። እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ወደ 14 ሚልዮን ይህንን ጽሁፍ ያዘሉ ቲሸርቶች እና ማስጌጫዎች እንደተሸጡ ሰምቻለሁ። ይህ እንቅስቃሴ የብዙዎችን ሕይወት በመለወጥ በአለም ላይ ተጽዕኖ አሳድሯል። ክርስቲያኖች በእያንዳንዱ አጋጣሚ እና ከእያንዳንዱ ውሳኔያችን በፊት “ኢየሱስ ቢሆን ምን ያደርግ ነበር?” ብለን በመጠየቅ ከቅዱስ ቃሉ ጋር በማዛመድ የክርስቶስን እርምጃ ብንራመድ በእርግጥ ዛሬም አለምን መቀየር እንችላለን።

የዛሬው ጽሁፌ ሃሳብ በዚሁ ላይ በመመስረት አሁን በሃገራችን እየታየ ካለው የፀጥታ አለመረጋጋት እና ከታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አንጻር እንደ አንድ ክርስቲያን ይህንኑ ጥያቄ እንድንጠይቅ ነው። ነገር ግን እኛ ጥያቄያችንን ትንሽ ቀየር እንድናደርገው ፍቀዱልኝ። እንዲህ ብለን እንጠይቅ “ኢየሱስ ቢሆን (እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ክርስቲያን) በዚህ ወቅት ምን አያደርግም ነበር ?”

ኢየሱስ ቢሆን ምን አያደርግም ነበር?

መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስ ክርስቶስን “የእምነታችን ጀማሪ እና ፈጻሚ” (ዕብ 12፡2) ይለዋል። ደግሞም ክርስቲያኖች ክርስቶስን ልንመስል እንደተጠራን ይነግረናል (ሮሜ 8፡29) ። ከምንም በላይ “ክርስቲያን” የሚለው መጠሪያም ለክርስቲያኖች የዋለው እንደ ክርስቶስ ስለኖሩ ነበር (ሐዋ 11፡26) ። ክርስቲያን በምንም ሁኔታ ውስጥ የክርስቶስን ሕይወት በምድር ላይ እንዲገልጥ የተጠራ ነው። “በምንም” ሁኔታ ውስጥ የሚለውን ልብ እንበል!

ሃገራችን ኢትዮጵያ አሁን እያለፈችበት ያለው ጎዳና እጅግ የሚያሳስብ እና ሁላችንም ለጸሎት ወደ አብ የጸጋ እና የምህረት ዙፋን የሚጠራ መሆኑ የታወቀ ነው። እጅግ ብዙ ልብ የሚሰብሩ ነገሮችን ዕለት ዕለት በማህበራዊ ሚድያውም ሆነ በዜና አውታሮች እየሰማን እንገኛለን። የኢትዮጵያ ክርስቲያኖች በዚህ ከባድ ጊዜም ቢሆን ታዲያ የክርስቶስን ምሳሌ ይዘን እንድንራመድ የእግዚአብሔር ቃል ግድ ይለናል።

መግቢያው ላይ አስቀድመን እንዳየነው ክርስቶስም የኖረበት ዘመን መጠኑ እና ሁኔታው ይለያይ እንጂ ያለመረጋጋት ዘመን ነበር። ስለዚህም በወንጌላቱ የሰፈረውን የክርስቶስን ሕይወት ብናጠናና በተለይ በዚህ ጊዜ እንደ ክርስቲያን ማድረግ ያለብንን እና የሌለብን ነገር ጠንቅቀን እንድናውቅ ይረዳናል። እኔም ኢየሱስ ቢሆን የሚከተሉትን አምስት ነገሮች እንደማያደርግ /እንደማይሆን/ ከወንጌሉ ተምሬያለሁ። እነዚህ አምስቱ ክርስቶስ በዚህ ጊዜ ቢኖር የማያደርጋቸው ነገሮች ምንድናቸው?

1) ኢየሱስ ቢሆን ... ስለ ሰዎች (ስለ ሃገሩ) ግድየለሽ አይሆንም ነበር!

“እርሱም መልሶ፡- ከእስራኤል ቤት ለጠፉት በጎች በቀር አልተላኩም አለ።” ማቴ 15:24

አለምን ሊያድን የወረደው የስላሴ አንድ አካል የአብ አንድያ ልጅ መድኃኒታችን ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር ላይ የተልዕኮው መዳረሻው ለነበረው ማህበረሰብ ግድ የለሽ አልነበረም። የእስራኤል መጥፋት፣ የእስራኤል መበተን ፣ የእስራኤል መጎዳት ፣ የእስራኤል መጎሳቆል ግድ ይለው ነበር። ምንም እንኳ አጠቃላይ ተልዕኮው አለምን የማዳን ቢሆንም የራሱን ሕዝብ ገሸሽ አድርጎ ግን አልነበረም።

በትንቢቱም የተባለው “እስራኤልን የሚጠብቅ መስፍን” (ማቴ 2፡5-6) ነበር። ደግሞም የተሰጠው መጠሪያ “የእስራኤል ንጉስ”  (ማቴ 27፡42) እንደነበር አይዘነጋም። በተወለደባት አገር የተጠራ ደግሞም ስለ ሕዝቡ ግድ የለሽ ያልነበረ ነበር።

ጌታ ኢየሱስ በዛሬይቱ ኢትዮጵያ ተወልዶ ቢሆን ኖሮ ጌታ ኢየሱስ ስለ ኢትዮጵያ ሕዝብ ግድ የለሽ አይሆንም ነበር። ውጭ ውጭ በማሰብ የሃገሩን ጉዳይ አይዘነጋም ነበር። ወይንም እንዳንዳንድ ክርስቲያኖች ቃሉን በተሳሳተ መንገድ በመተርጎም “ሃገሬ በሰማይ ነው” በማለት በምድር ላይ የሚኖሩ ቤተ ዘመዶቻውን እንደሚዘነጉት አይዘነጋም ነበር።

ለሰማይ ለሰማይ ደግሞ ከክርስቶስ በላይ ማን ሰማይን ያውቀው ኖሯል? ያውም ሰማየ ሰማያትን አቋርጦ የመጣው ክርስቶስ ስለኖረበት ሕዝብ የሚያስብ እና ግድ የሚለው ከሆነ እኛ ምን ያህል ግድ ሊለን ይገባል? እጅግ በጣም!

2) ኢየሱስ ቢሆን ... በማንም ላይ ሰይፍ አያነሳም ነበር!

“በዚያን ጊዜ ኢየሱስ እንዲህ አለው። ሰይፍን የሚያነሱ ሁሉ በሰይፍ ይጠፋሉና ሰይፍህን ወደ ስፍራው መልስ” ማቴ 26፡52

ጌታ ኢየሱስ የሰይፍ ጠላት ነበር። ሰይፍን በፍቅር በማሸነፍ ያምን ነበር። ሰይፍን የሚያነሱ በሰይፍ እንደሚጠፉ በግልጽ ያስተምር ነበር። ዛሬ መንግስት በሕዝብ ላይ ሕዝብ በሕዝብ ላይ ሕዝብ በመንግስት ላይ ሰይፍ በሚያነሱበት ዘመን ኢየሱስ ቢኖር ኖሮ ... ሰይፍ አያነሳም ነበር።

ጌታ ኢየሱስ የሰው ጠላት አልነበረውም። ሰዎች ጠላት ቢሆኑ እንኳን እርሱ በፍቅሩ ሊያሸንፋቸው ሙሉ መንገድ ተጉዞ በደጃቸው ቆሞ በራቸውን በፍቅር ትርታ ያንኳኳል እንጂ ሰይፍን አያነሳም! ሰይፍ ባነሱበት ላይ ራሱ ጌታ ኢየሱስ ሰይፍን በማንሳት ምላሽ አልሰጠም። እውነተኛ ፍቅር፣ እውነተኛ ግድ የሚለው ፍቅር እንዲህ ነው!

የክርስቶስ ሰይፍ በሁለት ምላስ የተሳለ የፍቅር ቃል ነው (ዕብ 4፡12) ። እርሱ አጥንትን እና ጅማትን እስኪለይ ድረስ ሰውን ይማርካል። የወንድምን አንገት አይቀላም። ሕዝብን ከሕዝብ ለበቀል አያጫጭርም ። ኢየሱስ ቢሆን ሰይፍ አያነሳም!

ክርስቲያን የሃገራችን መሪዎች እንዲሁም ሕዝቦች ይህንን የኢየሱስን መርህ ቢከተሉ ፍቅር እንዴት አብልጣ ትነግስ ነበር!

3) ኢየሱስ ቢሆን ... ሰይፍ ሲነሳ ዝም አይልም ነበር!

“ሰይፍን የሚያነሱ ሁሉ በሰይፍ ይጠፋሉና ሰይፍህን ወደ ስፍራው መልስ” ማቴ 26፡52

ኢየሱስ ሰይፍ የማያነሳ ብቻ አልነበረም። ሰይፍ ሲነሳም ደስ አይለውም ነበር። ሰይፍን ወደ ስፍራው እንዲመለስ ይናገር ነበር። ልብ እንበል ኢየሱስ ሰይፍን ለማስቆም ሰይፍ አላነሳም። ኢየሱስ ሰይፍን ለማስቆም ሰላማዊ መንገድን ነበር የተጠቀመው።

ይህንን የክርስቶስን የ“ሰይፍህን መልስ” አካሄድ ብዙዎች አዋጭ ሆኖ አላገኙትም። ከዚህም የተነሳ “ሰይፍን በሰይፍ” ብለው የተላለቁ ሚልዮኖችን ማን በቆጠራቸው? በተቃራኒው ደግሞ “ሰይፍህን መልስ” አካሄድ የሄዱ እንደ ቄስ ዶ/ር ማርቲን ሉተር ኪንግ አይነቶቹ አለምን በሰላማዊ መንገድ ለውጠዋል።

ኢየሱስ ቢሆን ሰይፍ በወንድሞቹ ላይ አይደለም በሚጠሉት ላይ እንኳ ሲነሳ ዝም አይልም። “ሰይፍ ይመለስ!” ይላል። ዋጋ ሊያስከፍል ይችላል። ደካማ ሊያስብል ይችላል። ፍቅር ግን ቢሞትም እንኳ ይነሳል። ሰይፍ ግን ይመለስ!

ጌታ ኢየሱስ ዛሬ በሃገራችን ሕዝብ በሕዝብ ላይ ፣ ብሔር በብሔር ላይ ፣ መንግስት በሕዝብ ላይ ደግሞም ሕዝብ በመንግስት ላይ ሰይፍ ሲያነሳ ቢያይ ዝም አይልም ነበር! ፍቅር በሞላበት ድምጹ “ሰይፍህን መልስ!” ይል ነበር እንጂ እንዳላየ እንዳልሰማ አይሆንም!

4) ኢየሱስ ቢሆን ... ወገንተኛ አይሆንም ነበር!

“እላችኋለሁም ብዙዎች ከምሥራቅ እና ከምዕራብ ይመጣሉ ከአብርሃምና ከይስሃቅ ከያዕቆብም ጋር በመንግስተ ሰማያት ይቀመጣሉ” ማቴ 8፡11

ጌታ ኢየሱስ የሮምም ፣ የፈሪሳዊም፣ የቀናተኛም ወገንተኛ አልነበረም። ኢየሱስ የአይሁድ ንጉስ የሆነው ሮምን በጉልበት ገልብጦ አልነበረም። ክርስትና የሮምን ግዛት ያጥለቀለቀው በቄሳር ላይ የጦር ሰራዊት አዝምቶ አልነበረም! በአጠቃላይ የቀናተኞቹን መንገድ አልተከተለም!

ደግሞ ዛሬ የምናወራለት ጌታ አሸናፊ የነበረው እንደፈሪሳውያን በማመቻቸመችም አልነበረም! የሮም መጠቀሚያ እንዲሆን ራሱን አሳልፎ አልሰጠም። የማንም ቡድን አባል አልነበረም። ጌታ ኢየሱስ በዚህ ጊዜ በሃገራችን ቢኖር የማያደርገው ነገር ቢኖር የማንም ቡድን አባል አለመሆንን ነው። ቡድንተኝነት ተልዕኮውን በአጭሩ ያስቀረው ነበር። ስለዚህም ቡድን ከመያዝ ይቆጠብ ነበር።

ክርስትና አለምን ያጥለቀለቀው የአንድ ቡድን ሃይማኖት ስላልነበር ነው። የድሃውም የሃብታሙም፣ የተራው ሰውም የባለስልጣኑም ፣ የምስራቁም የምዕራቡም ፣ የጥቁሩም የነጩም ደግሞም የሁሉም ብሔር (ማቴ 28፡19-20) እንዲሆን ጌታ ኢየሱስ አስቀድሞ ቡድንተኛ ባለመሆን ምሳሌ አሳይቶ ነበር ያለፈው።

ዛሬም በሃገራችን ቢኖር ከሰሜኑም ፣ ከምዕራቡም ፣ ከምስራቁም ፣ ከደቡቡም ጋር አብሮ እንደሚቆም አምናለሁ። እርሱ ከብሔር ብሔር ጀርባ እንደሚቆም አምናለሁ። ሁሉንም በፍቅር እንደሚያስጠጋም አምናለሁ። ያውም ለዘመናት በፍቅር ፣አብሮ በመኖር እና በመቸቻል በምትታወቀው ሃገራችን ጌታ ኢየሱስ የመዋደድ ደጀን እንጂ የመከፋፈል ምክንያት እንደማይሆን አምናለሁ።

5) ኢየሱስ ቢሆን ... መልዕክቱን አይለውጥም ነበር!

“ጲላጦስም እንግዲያ ንጉስ ነህን? አለው። ኢየሱስም መልሶ እኔ ንጉስ እንደሆንሁ አንተ ትላለህ። እኔ ለእውነት ልመሰክር ስለዚህ ተወልጃለሁ ስለዚህም ወደ ዓለም መጥቻለሁ፤ ከእውነትም የሆነ ሁሉ ድምጼን ይሰማል አለው።” ዮሐ 18፡37

ሌላው ዋነኛው ከክርስቶስ የምናየው ጠንካራ አቋም ቢኖር መልዕክቱን እንደማይለውጥ ነው። በጲላጦስም ፊት ሆነ በሸንጎው ፊት እንዲሁም በሕዝቡ ፊት ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ ነበር። ዛሬ የተናገውን ነገ አይቀይረውም። አይሁድ በሮም ጭቆና ስለደረሰባቸው ስብከቱን ሁሉ ስለሮም አላደረገውም። አስቀድሞ የመጣበት አላማ አለ። አስቀድሞ ያነገበው መልዕክት አለ። እርሱን እስከፍጻሜው ያደርሳል እንጂ መሃል ላይ በሚነሱ ጉዳዮች ሲል መልዕክቱን አይቀይርም።

ስለ አይሁድ ስቃይ ግድ ሳይለው ቀርቶ አይደለም። ወይም በሮማውያን ጨቋኝ አገዛዝ ሳይበሳጭ ቀርቶም አልነበረም። ነገር ግን ከእነዚህ ሁሉ ይበልጥ ለአይሁድም ለሮምም አስፈላጊ የሆነ መልዕክትን ስለያዘ ነበር። መልዕክቱም ራሱ ክርስቶስ ነበር!

ኢየሱስ ክርስቶስ ብቸኛው እውነት ነው። በሃጢአት ወደቀው ሰው ወደ አብ የሚደርስበት ብቸኛው መንገድ ነው። ለክርስቶስ ትልቁ እና ዋነኛው አንገብጋቢው ችግር የሮም መንግስት አልነበረም! ከዚያ ይልቅ ትልቁ ችግር ሐጢአት ነበር። እግዚአብሔር ሲያይ ሮምም ፣ አይሁድም በሃጢአት በሽታ ታመው ነበር። ስለዚህ መድሃኒት የሆነውን አንድያ ልጁን ላከው። ኢየሱስ ይህንን መልዕክት ይዞ ነው የተወለደው። ይህንን መልዕክት እስከፍጻሜው ደግሞ በማድረስ መድኃኒት ሆኖልናል።

ዛሬም በኢትዮጵያ ቢኖር ጌታችን መልዕክቱን አይቀይርም ነበር። የመንግስትም የሕዝቦችም ችግር ኃጢአት ነው። ሰው ሁሉ በኃጢአት በሽታ ታሟል። አንድ መፍትሄ ያስፈልገዋል። አንድ አዳኝ ያሻዋል። እርሱም ራሱ ጌታ ኢየሱስ ነው። እኛስ እንደክርስቶስ የወንጌል መልዕክታችንን አሁንም በዚህ ጊዜ እያሰማን ይሆን ወይስ ርዕሳችንን ቀይረናል?

ከእነዚህ አምስት ነጥቦች ብዙ እንደተማርን አስባለሁ። ከክርሰቶስ ሕይወት መማር እዚህ ጋር አያበቃም። የህይወት ዘመን ጉዞ ነው። ይህንን በልባችን በማሳደር በተግባር ማሳየት ይሁንልን። አሜን!

Last modified on %AM, %15 %307 %2018 %09:%Mar
Naol Befkadu

Naol Befkadu Kebede (BTh, student of MA in Ministry and Medical Doctorate student at AAU) is the founder and contributor of Lechristian Blog, an online ministry that aims to redeem cultures for the glory of God and to inspire and encourage believers for the completion Great Commission. Naol has authored an Amharic book titled "ተነሺ ፤ አብሪ" (2015) that motivates young believers for a meaningful and radical life. 

lechristian.blogspot.com

ቤተ-ክርስትያን አሥራት ብታወጣ ምን ሊሆን ይችል ነበር ?

በአሁኑ ጊዜ ያለችው ቤተ ክርስትያን መስጠት ላይ ጎበዝ አይደለችም። ይሄ ዜና ሳይሆን በጥናት የተደገፈ እውነታ ነው።

Mike Holmes  - avatar Mike Holmes

ጨርሰው ያንብቡ

ልጓም የሌለው የምኞት ፈረስ

አንድ ወንድ የሆነችን ልጅ ሰውነት ስለተመኘ ብቻ ሊያገባት ሲፈልግ፣ በዚች ምድር ላይ እንደእርሱ ያለ አፍቃሪ የሌለለ እስኪመስል ድረስ እራሱን “ሮማንቲክ” አድ...

Meskerem Kifetew - avatar Meskerem Kifetew

ጨርሰው ያንብቡ

 

The views and opinions expressed on Daily Injera are solely those of the original authors and our contributors. These views and opinions do not necessarily represent Daily Injera or our Staff.

Newsletter

Subscribe to our newsletter. Don’t miss any article, devotionals or wallpapers.

We do not spam!

You're automatically subscribed to bi-weekly articles and daily devotionals. You can customize your subscription settings here.