ውብ ማለዳ ነበር-በተራራማዋ የወይራ ዛፎች ኮረብታ ደብረ ዘይት። ክርስቶስ በዚች ኋላ ቀር መንደር ውስጥ በሚገኝ መቅደስ የሰንበት ትምህርቱን እያስተማረ ነበር።ህዝቡ ከዚህ “ድኩም” ሰው የሚወጡትን አስደናቂ ቃላት ሊሰሙ ታድመዋል። ይህ መቅደስ ከትምህርቱም ሌላ አመንዝራን፣ ከሳሽን እና አምላክ መሆኑና አለመሆኑ የሚፈተን ጎልማሳን አስተናግዶ ነበር። በዚህች ውብ ማለዳ በሆነው ትእይንት እኔን የምታመለክት- አመንዝራ የመኖሯን ያህል አምላክን በአካል የወከለ ኢየሱስ መኖሩን አምናለሁ።
ይህን ማመን በአፋችን እንደምናወራው ቀላል አይደለም። በዚያ ዘመን ኖረን ቢሆን ኖሮ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን ልናምን እስኪሳነን አሁን እንደምናወራለት ጀብደኛ አልነበረም(የሚራብ፣የሚደክም፣የሚያለቅስ፣የሚመታ በመጨረሻም የሚሰቀል “መሲህ” ሆኖ መምጣቱ አንዳንዴ በዘመኑ የነበሩ ወገኖቹን ለማሰናከል የታሰበ እስኪመስል ድረስ ኢየሱስን ተራ ሰው ያደርጉታል። ድካሙ እና “ሰው”ነቱ የአደባባይ ሲሆን፤ጥቂቶች የመሰከሩለት ከሞት የመነሳት ጀብዱው ግን እምነት በሚባል መንፈሳዊ መነጽር ብቻ ሊታይ የሚችል ድብቅ መሆኑ ከዘመኔዎቹ ጋር እልህ የተጋባ ያስመስለዋል።)
በዚያች ውብ የትምህርት ማለዳ በምንዝር የተያዘችው ሴት ልብሶቿ እስኪቀደዱ እየተጎተተች ስትገባ አዳራሹ ውስጥ የተፈጠረውን ዝምታ እና በፈተናቸው ከባድነት የተማመኑትን ፈሪሳዉያን ኩራት መሳል ሁለቱም ቀላል ነበሩ። በአጭሩ በምንዝር እጅከፍንጅ መያዟ ተገልጾ “አንተስ ምን ትላለህ?” ወደሚለው ጥያቄ ዞሩ። “ዉገሯት” ቢል የሀጢያተኞች ወዳጅ አድርጎ ራሱን የሚስለው ክርስቶስ በነሱ ዘንድ ያለውን ዋጋውን ሊያጣ ነው። “አትውገሯት” ቢል ከአይሁድ ብሎም ከ ሙሴ ህግ ሊፋረስ ነው። “አንተ ግን አምላክ ብትሆን ምን ትላለህ?” አይነት ነው ጥያቄው። ክርስቶስ ግን ዝቅ ብሎ በጣቶቹ ጻፈ። በወንጌላት እንደሰፈረልን ክርስቶስ የጻፈበት ብቸኛ ቦታ ነው- ታዲያ ምን ብሎ ይሆን የጻፈው?
ደጋግመው በነዘነዙት ጊዜ ይጽፍ የነበረውን አቋርጦ የመለሰላቸው መልስ ግን ለዚያች አመንዝራ ብቻ ሳይሆን በህግ በተከሰስን ጊዜ ለሁላችንም የተመለሰው መልስ ስለመሆኑ እርግጠኛ ነኝ። “ከእናንተ ሀጢያት የሌለበት አስቀድሞ በድንጋይ ይውገራት” አላቸው። ለእኔ ይህ የአዲስ ኪዳን ማስጀመሪያ መለከት ነው። በህግ እና በእግዚአብሔር መካከል ያለውን ልዩነት በግልጽ የሚያሳይ ስፍራ ነው።ህጉም፤ ሰጪው ክርስቶስም አመንዝራነት ሀጢያት መሆኑን አልካዱም። ዳሩ ህግ ለተላላፊው ቅጣትን ሲያሰፍር ክርስቶስ ግን ደካማነታችንን በማየቱ ምህረትን ይሰጣል። ከቅጣት ይልቅ ምህረት የበዳይን ልብ ያቀናል።
ክርስቶስ ግን ይህን ተናግሮ ከሳሾቿም፤ወጋሪዎቿም ሆነው የመጡት ሰዎች ማንም ባያያቸውም ቅሉ ሀጢያተኞች መሆናቸውን ነግሮ ካሳፈረላትም በኋላ በጣቶቹ ይጽፋል-ዝቅ ብሎ አቧራ የጠጣውን በጥርብ ድንጋይ የተሰራ የመቅደሱን ወለል በጣቶቹ እየጠረገ። ምን ብሎ ይሆን የጻፈው?... የሁሌም የአግራሞት ጥያቄዬ።
ምናልባት፤እንደው ምናልባት ለእነዚያ ግብዝ ህግ አዋቂዎች “አብሯት ያመነዘረውን ረስታችሁት ነው ወይስ ከእናንተ አንዱ ነው?” ይሆን ያላቸው????