Saturday, 04 May 2024

እግዚአብሔር ተራ በሚባሉ ቀኖቻችሁም ላይ በሥራ ላይ ነው Featured

Posted On %AM, %11 %041 %2016 %03:%Oct Written by

ሁልጊዜ በዓመቱ መጀመሪያ ላይ እንደማደርገው በሰው ልጆች ታሪክ ሁሉ ውስጥ ከታተሙት መጽሐፍት ታላቅ ከሆነው መጽሐፍ ቅዱስ ባለኝ አመታዊ የንባብ ጉዞዬ ዘፍጥረትን በማንበብ ላይ ነኝ ። አሁን አስራ አምስተኛ አመቴ ላይ ነኝ ። ሙሉ የጎልማሳ ሕይወቴን መጽሐፍ ቅዱስን ሳነብ እና ሳጠና ስላሳለፍኩ ወደጠለቀው ደረጃ የደረስኩ ይሰማኛል ። ምናልባት እራሴን እየካብኩ ነው ።

ይህ መጽሐፍ ያስደንቀኛልም፤ ግራ ያጋባኛልም፤ ደግሞም ትሁት ያደርገኛልም፤ ያበረታታኛልም ። በሕይወት ዘመን ሙሉ ሊገኝ ከሚችለው በላይ ጥበብ በውስጡ አለው ። በግልፅ በሚናገራቸውም ሆነ በማይናገራቸው ነገሮች ይናገረኛል ። በዚህ ወር ላይ የዘፍጥረት መጽሐፍ በእግዚአብሔር የታሪክ መዝገብ ውስጥ የተጻፉ ተራ የሚመስሉ ዓመታ ላይ ስላለ የእግዚአብሔር ሥራ እየተናገረኝ ነው ። 

የዘፍጥረት ተራ ዓመታት 

የዘፈጥረት መጽሐፍ ሰፋ ያለ ጊዜን ይሸፍናል ። የመጽሐፍ ቅዱስ አዋቂዎች በአዳም እና በአብርሃም መኃከል ከ 2000 እስከ 6000 ዓመታት ጊዜ እንዳለ ይናገራሉ (በዘር ግንድ ቆጠራ መኃከል ያለው ጊዜ ተለዋዋጭነት ነው ይህን ልዩነት ያመጣው) ። ይህም ማለት በትንሹ ዘፍጥረት ብቻውን ሌሎች የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ተደምረው ከሚወስዱት ታሪካዊ ጊዜ ጋር ይስተካከላል ። ምንአልባትም ሊበልጥ ይችላል ።

ስለእነዚህ ሺህ ዓመታት የምናውቀው ምን ያህል ነው? ስታስቡት በጣም ጥቂት ብቻ ነው የምናውቀው ። ከአዳም እና ሔዋን ፍጥረት በኋላ (ዘፍጥረት 1፡26-2፡25) ስለ ሰው ልጅ ውድቀት እናነባለን (ዘፍጥረት 3) ቀጥሎ ቃየን አቤልን ስለመግደሉ እናነባለን (ዘፍጥረት 4) ከዛ በመቀጠል ኖህ ጋር እስክንደርስ ድረስ አንዳንድ ታሪኮች ብቻ የገባበት የትውልድ መጽሃፍ ብቻ እናገኛለን ። በአዳም እና በኖህ መኃል ምን ያህል ዓመታት አለፉ (ከዘፍጥረት 2 እስከ 5)?  በትንሹ 1600 ዓመታት ምንአልባትም ከዚያ በላይ ጊዜ ነው ።

በኖህ እና አብርሃም መሀል (ከምዕራፍ 6 እስከ 11) ምእተ አመታት አሉ (በትንሹ 350 ምንአልባትም ከዚያ በላይ የሚሆን) ። ከጥፋት ውሃ ታሪክ በተረፈ መጽሃፍ ቅዱስ ስለእነዚህ ጊዜያት የሚነግረን ስለ ኖህ ልጆች፣ ሌላ ተጨማሪ የትውልድ መጽሐፍት እና ስለባቢሎን ግንብ በጣም ጥቂት ነገሮችን ብቻ ነው ።

ከዛም ስለ አብርሃም፣ ይስሃቅ፣ ያዕቆብ እና የአባቶች አለቃ (ከምዕራፍ 12 እስከ 50) የበለጠ መረጃዎችን ይሰጠናል ። እነዚህ 39 ምዕራፎች 360 ዓመታትን ሲወስዱ ስለእነዚህ ጊዜያት ብዙውን ሳይናገር እንደሚያልፍ ልብ ይሏል።

እግዚአብሔር ጊዜንም ሆነ ሰዎችን አያባክንም

ለስሌት እንዲመቸን አሁን በአዳም እና በአብርሃም መኃከል 2000 ዓመታት አሉ ብለን እናስብ ። በዓመት 365 ቀናት ብንል ወደ 730,000 ይሆናል። በጣም የተወሰኑት ብቻ ታሪካቸው እንዲመዘገቡ እግዚአብሔር የወሰናቸው ቀናት አሉ ።

እግዚአብሔር በቀሩት በእነዚያ ምን እንደተከሰተባቸው በማናውቅባቸው ጊዜያት ደግሞም “ይበሉና ይጠጡ፣ ያገቡና ይጋቡም. . . ይሸጡም ይተክሉም ቤትም ይሠሩ” (ሉቃስ 17፡27-28) በተባሉት ሁሉ ሰዎችስ ላይ ምን እያደረገ ነበር? አንዳንዶችን በከርሰ ምድር ቁፋሮ የተገኙ  የአስደናቂ እና አስፈሪ ዘመናት ታሪክ ውስጥ ምን እየሰራ ነበር? የባከኑ ዓመታት እና የሚጣሉ ሰዎች ናቸው? 

አይደሉም ። እያንዳንዱ 730,000 ቀናት የእግዚአብሔር ልዩ የሆኑ ፣ እጅግ ውድ እና በምንም የማንተካቸው ፍጥረት ናቸው (መዝሙር 118፡24) ። እያንዳንዱም ሰዎች ልዩ የሆኑ ፣ እጅግ ውድ እና በምንም የማንተካቸው የእግዚአብሔር ምስል ያለባቸው ፍጥረቱ ናቸው (ዘፍጥረት 1፡27) ። ምንም ያህል ቢጣመሙ እና ቢበላሹ እያንዳንዳቸው ልዩ ታሪክ ያላቸው በታሪኩ ውስጥ ለመልካም ሆነ ለክፉ ድርሻ ያላቸው (ሮሜ 9፡21) ለእኛ ሳይታወቁ ቢኖሩም ለእግዚአብሔር ግን ትርጉም ያላቸው ሰዎች ናቸው ። የእያንዳንዳቸው መድረሻ ምህረት ይሁን ፍርድ የምድር ሁሉ ፈራጅ ግን በቅን እንደሚፈርድ በእርሱ እንታመናለን (ዘፍጥረት 18፡25) ። ብዙዎች ሕይወታቸውን አባክነዋል ። እግዚአብሔር ግን የእነእርሱን አላባከነውም ።

በእነዚህ ባልተመዘገቡ ጊዜያት እግዚአብሔር ጊዜም ሆነ ሰዎችን እያባከነ አልነበረም ። ሁሉንም ነገር በአንድ ላይ በስልጣኑ ቃል እየደገፈ እያጋጠማቸው ነበር (ቆላስይስ 1፡17 ዕብራውያን 1፡3) ። በእያንዳንዷ ዝርዝር የታሪክ ኩነት እና የሰዎች መስተጋብር ላይ ሲሰራ ነበር (ዮሐንስ 1፡17 ፤ የሐዋርያት ሥራ 17፡26-28) ። ይህንንም ማድረጉ የዘመን ሙላት በደረሰ ጊዜ ወደ ሰዎች ታሪክ እና መስተጋብር እንደ ሁለተኛው አዳም ሆኖ በመግባት በገነት በዚያን አስከፊ እና አስደናቂ ቀን የተፈጠረውን ውድቀት ለመመለስ ያለውን ዓላማ ለመፈጸም ነው (ገላትያ 4፡4-5፤ ሮሜ 5፡17) ። እግዚአብሔር ጠፍቶ ወይንም ርቆ አልነበረም (የሐዋርያት ሥራ 17፡27-28) በጸጥታም አልነበረም (ሮሜ 1፡20) ።

እግዚአብሔር ጊዜአችሁን ሆነ እናንተን አያባክንም

ልዩ ያልሆኑት የዘፍጥረት መጽሐፍ ዓመታት እናንተንም ይናገሯችሁ ። የእግዚአብሔርን እጅ በግልጽ የምታዩባቸው ልምምዶችን እና ክስተቶችን የያዙ እምነታችሁን እና ሕይወታችሁን በቋሚነት እና ሊታወስ በሚችል መልኩ የሚቀርፁ ቀኖች በሕይወታችሁ ውስጥ በጣም ጥቂት የሆኑት ብቻ ናቸው ።

ነገር ግን አብዛኛዎቹ ቀኖቻችሁ ምናልባትም ዛሬን ጨምሮ ለትውስታችሁ ሳይቀሩ ያልፋሉ ። ይሁን እንጂ ዛሬ ምንም ልዩ ባይመስል የማይጠቅም ግን አይደለም ። ልዩ ዋጋውም እጅግ ውድ እና በሌላ ልንቀይረው የማንችለው ነው ።

ዛሬ እግዚአብሔር ስለ በጎ ፈቃዱ መፈለግንም ማድረግንም በእናንተ እየሠራ ነው (ፊሊጲስዩስ 2፡13) ። ዛሬ እግዚአብሔር በእናንተ መልካምን ሥራ የጀመረው እስከ ኢየሱስ ክርስቶስ ቀን ድረስ ሊፈጽመው እየሠራ ነው (ፊሊጲስዩስ 1፡6) ። ለእናንተ ባይታያችሁም ሆነ ባይሰማችሁም፤ እግዚአብሔር ግን ዛሬ እያንዳንዷን የእናንተን እና ሌሎች ብዙ ሺዎች ታሪክን እና የዕለት ተዕለት መስተጋብር ዝርዝር ነገርን እየሠራ ነው ። ለረጅም ጊዜ ስትጸልዩ ለነበረው ፀሎት መልስ ሊያመጣ፣ ለእናንተ የማይቻል የሚመስለውን በር ይከፍት ዘንድ ፣ የጠፋውን ወደ ቤት ሊመልስ ፣ ልባቸው የደነደኑ ወዳጆቻችሁን ሊያድን ፣ ከመከራ ሊያድናችሁ ወይንም ለሌላ ሰው የሚደንቅ ያልታሰበ የጸጋ መንገድ ሊያደርጋችሁ እየሰራ ነው። 

እግዚአብሔር የሠራት ቀን ይህች ናት ሐሤትን እናድርግ፥ በእርስዋም ደስ ይበለን (መዝሙር 118፡24)። ለእናንተ አቅዶታል ። አላማ አለው ። ቀናችሁ ላይ ምንም ነገር ቢሆን በሁሉ አመስግኑ (1 ተሰሎንቄ 5፡18) ። እግዚአብሔር የሚያባክነው ቀን ስለሌለ እናንተንም አያባክናችሁም። ብትወዱትና ብታምኑት ዛሬ ተራ የሚመስሉት ነገሮች ድንቅ የሆነ መልካም ነገርን እንዳደረጉላችሁ አንድ ቀን ታያላችሁ። (ሮሜ 8፡28)


እግዚአብሔር የሚያባክነው ቀን ስለሌለ እናንተንም አያባክናችሁም።


 

Originally Posted at DesiringGod.org, Translated by Joshua Terefe


 

Last modified on %PM, %10 %879 %2016 %23:%Dec
Jon Bloom

Jon Bloom serves as author, board chair, and co-founder of Desiring God. He is author of three books, Not by Sight, Things Not Seen, and Don’t Follow Your Heart. He and his wife live in the Twin Cities with their five children.

https://twitter.com/Bloom_Jon

ላለፈ ሕይወታችሁ ባሮች አይደላችሁም

ክርስትና፣" ለውጥ ይቻላል" ማለት ነው። ጥልቅ የሆነ መሠረታዊ ለውጥ። ቀድሞ ልበ ደንዳኖች እና ደረቅ ልቦች ከነበራችሁ አሁን ልበ ሩህሩህ መሆን ትችላላችሁ። ...

John Piper - avatar John Piper

ጨርሰው ያንብቡ

የክርስቶስ ጠባሳዎች

“እጆቼን እና እግሮቼን ተመልከቱ፡እኔው ራሴ ነኝ ደግሞም ንኩኝ እና እዩ ይህንንም ብሎ እጆቹን እና እግሮቹን አሳያቸው” ሉቃ 24፡39 ...

Genaye Eshetu - avatar Genaye Eshetu

ጨርሰው ያንብቡ

 

The views and opinions expressed on Daily Injera are solely those of the original authors and our contributors. These views and opinions do not necessarily represent Daily Injera or our Staff.

Newsletter

Subscribe to our newsletter. Don’t miss any article, devotionals or wallpapers.

We do not spam!

You're automatically subscribed to bi-weekly articles and daily devotionals. You can customize your subscription settings here.